የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም
ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2005
እስራኤልና ሃማስ የተስማሙበት ተኩስ አቁም እንዲከበር ተጠየቀ ። ጋዛን የሚያስተዳድሩት የሃማስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስማኤል ሃንያ የተለያዩ የፍልስጤም አንጃዎች ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል ። ሃንያ መልዕክቱን ያስተላለፉት በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ሃማስ በፍልስጤም ምድር የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የሚሊሽያ ቡድኖች ተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ በተጣለበት ሃላፊነት መሠረት ነው ። ስምምነቱ ለፍልስጤማውያን እንደ ድል ተቆጥሯል ። አንዳንድ እስራኤላውያን ደግሞ በነታንያሁ ውሳኔ አልተደሰቱም ።
8 ቀናት ከዘለቀው የእስራኤል የጋዛ ድብደባና የፍልሴማውያን የሮኬት ተኩስ በኋላ እስራኤልና ሃማስ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ትናንት ማምሻውን ይፋ የተደረገው ከእየሩሳሌም ወይም ከራማላህ ሳይሆን ከካይሮ ግብፅ ነበር ። የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱ እንደተገለፀም ፍልስጤማውያን ደስታ ፈንቅሏቸው በጋዛ ጎዳናዎች ሲጨፍሩ አምሽተዋል ። ደሰታቸውን ለመግለፅም ከ 1ሺህ ጊዜ በላይ ወደ ሰማይ መተኮሳቸውም ተዘግቧል ። ደሰታቸውን ለመግለፅም እንደ ድል የቆጠሩት የተኩስ አቁም ስምምነት እፎይታን አስገኝቶላቸዋል ። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ መንግስታቸው ስምምነቱን መቀበሉን ሲገለፅ ትንኮሳው ከቀጠለ እስራኤል በዝምታ የምታልፈው አለመሆኑን ተናግረዋል ።
የአሁኑ የስምምነቱ ፣እስራኤል ሰርጎ ገብ እንቅስቃሴን እንዲሁም ግለሰቦችን ለይቶ ማጥቃትን ጨምሮ ከምድር ከአየር ም ሆነ ከባህር ማንኛውንም ትንኮሳና ወደ ግጭት የሚያመራ እርምጃ እንዳትወስድ ይጠይቃል ። ፍልስጤማውያን አንጃዎችም የጓዳ ሰራሽ ሮኬቶች ጥቃትን እንዲያቆሙና ድንበር አካባቢም ከሚፈፅሙት ማናኛውም ጥቃት እንዲቆጠቡ ጥሪ ያደርጋል ። ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም የተስማሙት በግብፅና በአሜሪካን የሽምግልና ጥረት ነው ። ስምምነቱም በመነጋገር በቃል የፀና እንጂ በፊርማ የፀደቀ አይደለም ። ሁለቱም ወገኖች ለተኩስ አቁም የሚያስፈልጉትን ቅድመ ግዴታዎች ካሟሉ ከ 24 ሰዓትት በኋላ በነርሱ ጥያቄ በሃምስና በእስራኤል መካከል ድርድር ሊጀመር ይችላል ። እስራኤል ለምሳሌ ያህል ከጋዛ በኩል ጥቃት መሰንዘሩ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን በፍልስጤም ግዛት የመቆጣጠር ሥልጣን አሁንም ሊኖረኝ ይገባል ነው የምትለው ። ሃማስ ደግሞ እስራኤልና ግብፅ በጋዛ ላይ የተደረገው ከበባ እንዲነሳ እንዲያደርጉ እንዲሁም ሰዎችና እቃዎች ያለ ገደብ እንዲጓጓዙ ነው የጠየቀው ። በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ድርድሩን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ አስተያየት እነርሱን ሊያረካቸው የሚችል ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል ።
« የእስራኤልን ጦር አንፈራም ። ሆኖም ለሞቱትና ለሚፈናቀሉት ልጆቻችን ስንል ነው የተኩስ አቁሙ እንዲደረግ የምንፈልገው ። ለልጆቻችን ስንል ብቻ»
እስራኤልና ፍልስጤማውያንን ለመሸምገል ትናንት እየሩሳሌም ራማላ ና ካይሮ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂለሪ ክሊንተን በሽምግልናው ግብፅ አግዘዋል ። በስተመጨረሻ ከካይሮ ነበር ክሊንተን ወደ አገራቸው ያቀኑት ። እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ የመላክ እቅዷ እንዳለ ነው ። ይሁንና የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኤሁድ ባራክ ተጨማሪ ውጊያ ከእንግዲህ ማካሄዱ ምክንያት ያለው ሆኖ አይታያቸውም ።
«ግቦቻችንን ሙሉ በሙሉ መተናል ። ሃማስና ኢስላማዊ ጂሃድ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ። የሃማስ ወታደራዊ አዛዥ ድሃሽባሪና ሌሎችም ከፍተኛ አዛዦችና የሃማስ አስተሳሰብ አራማጆች እንዲሁም በርካታ አሸባሪዎች ተገድለዋል ። በአጠቃላይ ከ130 በላይ ተገድለዋል ። ከ 900 በላይ ቆስለዋል»
ምንም እንኳን የ 8 ቀኑ ጦርነት ብዙ የሰው ህይወትና ንብረት ቢያጠፋም የተኩስ አቁምን ስምምነቱን ፍልስጤማውያን እንደ ድል ነው የቆጠሩት ። ከፍልስጤም ምድር የሚተኮሱት ሮኬቶች ቴላቪቭና እየሩሳሌምን መድረስ መቻላቸው በፍልስጤማውያን ዘንድ ለእስራኤል መንበርከክ ምክንያት ተደርጎ ነው የተወሰደው ። አንዳንድ እስራኤላውያን ደግሞ ነታንያሁ የተኩስ አቁሙን መቀበላቸውን ከውርደት ቆጥረውታል ። አንዳንድ ወታደሮች ጭምር የነተንያሁ እርምጃ አላስደሰታቸውም ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ