1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤ.ኤን.ሲ መቶኛ ዓመት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2004

«ኤ.ኤን.ሲ ለመማር ዝግጁ የሆነ ድርጅት ነዉ።የዚያኑ ያክል በሕብረተሰቡ ዉስጥ የመሪነት ሥፍራ እንዳለዉም አይዘነጋም።ትሁት እንጂ-ትዕቢተኛ ድርጅት አይደለም።»

https://p.dw.com/p/13geP
ምስል DW


ለዘመናት ያወገዘ፣ የወጋዉ፣ ለመሪ-አባላቱ ገዳይ-አሳሪ አጋዢዎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሰጠዉ ሐያል ዓለም፣ ለአላማዉ ስኬት ከታገለዉ፣ መሪ-አባላቱን ከደገፈዉ አፍሪቃዊ በላይ ከተወዳጀዉ፣ መሪዎቹን ማድነቅ ማንቆለጳጰስ-ከጀመረ አስራ-ሰባተኛ አመቱ።ለጥቂት አባላቱ መበልፀጊያ ከሆነ-ከራረመ።ከደሙ-ከታሰሩለት አንዳዶቹ ጥለዉት ሲሔዱ፣ይጠሉ-ይርቁት የነበሩት ከተጋደሉለት እኩል ማወደስ-ማሞገስ ከጀመሩትም-እንዲሁ።የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት።ኤን.ኤን.ሲ።የትናንቱ ዘፈን-መዝሙር ግን በርግጥ ልዩ ነዉ።
                
መቶ አመት-ካንድ ቀኑ ዛሬ።መቶኛ አመቱ፥ የትግሉ ሒደት፣ የድል ማግስቱ እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።          

                    
የደቡብ አፍሪቃ ሠራተኞች በ1961 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የመቱት የሥራ ማቆም አድማ ከወራት በፊት በሕግ የታገደዉን የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC) መሪዎችን ለማሰር ሰበብ ለሚሻዉ ለነጭ ዘረኞቹ መንግሥት ጥሩ አጋጣሚ ነበር።ነጭ-ፅንፈኛዉ መንግሥት ባድማዉ ማግስት አድማዉን አደራጅታችኋል፥ ያለ ፍቃድ ከሐገር ወጥተሐል ያላቸዉን ኔልሰን ማንዴላንና ተከታዮቻቸዉን ያድን ገባ።

ነሐሴ ገባ።1962 አሰሳ-ዉንጀላዉ ከተጀመረ አስራ-ሰባተኛዉ ወሩ።እና ደርባን ላይ የሆነዉ ሆነ። አሜሪካዊዉ ደራሲ ዊሊያም ብሉም እንደፃፉት ነገሩ-እንዲሕ ነዉ።ደርባን በሚገኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ ቆንስላ ባልደረባነት ሽፋን የሚሰሩት የሲ አይ ኤ ወኪል ዶናልድ ሲ ሪካርድ ጠቀም ያለ-ገንዘብ ከሚከፍሉት የኤ.ኤ.ን ሲ አስመሳይ አባል አጭር መልክት ደረሳቸዉ።አሜሪካዊዉ ሰላይ አጭሯን መልዕክት በጣም አሳጥረዉ ለደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ አዛዥ ሹክ አሏቸዉ።አዛዡ ጊዜ አላጠፉም።ያዘመቱቷቸዉ ፖሊሶችም እንዲሁ።ወደ ደርባን የምትጓዘዉን መኪና-ያዟት።እንደ ሾፌር ጎስቆልቆል ያለዉ የዚያች መኪና ነጂ ትልቁ አሳ ነበር። ኔልሰን ሮሊሕሻሻሕ ማንዴላ።

ማንዴላ በሲ አይ ኤ ጥቆማ ተይዘዉ-ሃያ ስምንት አመታት እስር ቤት ማቀዉ የተለቀቁ ዕለት የደስታ-መልዕክት ለማስተላለፍ የያኔዉን የአሜሪካ ፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ (ቀዳማዊ)ን የቀደመ አልነበረም።«በመፈታትዎ መላዉ የአሜካ ሕዝብ በጣም ተደስቷል» አሉ።የካቲት 11 1990።ማንዴላም መጀመሪያ ከጎበኟቸዉ ሐገራት ቀዳሚዋ አሜሪካን ነበረች።ሐምሌ-1990 ዴትሪዮት።
                 
«እሕቶቼ፥ ወንድሞቼ፣ ወዳጆቼና ጓዶች ደጉን የዲትሮይት እና የማዕከላዊ ምዕራብ ሕዝብን እንዴት ማመስገን እንዳለብኝ እንኳን አላዉቅም።አሁን ብችል ከዚሕ መድረግ ወርጄ ሁላችሁንም ባንዴ ባቅፋችሁ ደስ ይለኝ ነበር።»

ማንደሌላ ከዚያ በሕዋላ ዩናይትድ ስቴትስን በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል።የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎችንና ባለሥልጣናትን አስተናግደዋል።የሁለቱን ሐገራት ወዳጅነት አጠናክረዋል።እስከ ሁለት ሺሕ ስምንት ድረስ ግን የሰላም ኖቤል ተሸላሚዉ፣ የነፃነት አርበኛዉ፣ የመቻቸል፣ የይቅርባይ አብነቱ ኔልሰን ማንዴላ በዩናይትድ ስቴትስ መስገብ በአሸባሪነት እንደተፈረጁ ነበር።

በዚያ በራቀዉ ዘመን ጆን ላንግሊባሌሌ ዱቤ ፈላስፋ፣ ደራሲ፣ ባለ ቅኔ፣ ሶሎሞን ሼኬሾ ፕላትጄ ጋዜጠኛ፣ የሥነ-ልሳን አጥኚ፣ ተርጓሚና ደራሲ፥ ፒክስሌይ ካ ኢሳካ ሴም ተመራማሪ፥ ምሑር እንጂ ፖለቲከኞች  አልነበሩም።

ሴም የብሪታንያ ትምሕርታቸዉን አጠናቀዉ ሐገራቸዉ ሲገቡ ከ1625 ጀምሮ የፀናዉ የነጮቹ የቦር ወይም የአፍሪካነር አገዛዝ በብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ተደፍልቆ፣ እነ ዱቤ፣ እነ ፕላትጄ በነጮቹ ዉጊያ፣ ጦርነት፣ በአገዛዛቸዉ ክፋት የሚሰቃየዉን ሕዝባቸዉን የሚረዱበትን ብልሐት-እያነሱ ሲጥሉ አገኟቸዉ።

ሰወስቱም በርግጥ ጥቁር-አፍሪቃዊ ምሁራን እንጂ እንደ ሻካ፣ እንደ ምዚሊካ፥ እንደ ቦምባዳ ተዋጊ-አዋጊም አልነበሩም።የሕዝባቸዉን መከራ ለማቃለል ግን እዉቀታቸዉን ለፖለቲካ፥ ከሻካ-ምዚሊካ፥ የቦምባን የወረሱትን የሕዝብ-የሐገር ፍቅር ሕዝብን ለማደራጀት ለማዋል አልሰነፉም።ሴም የብሪታንያን እዉቀት-ሥልጣኔን ሊያጋሩት የተመኙለት ሕዝባቸዉን ያገኙት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች የደቡብ አፍሪቃ ሕብረት ባሉት ሥርዓት ሲሰቃዩት ነበር።

«አፍሪቃዉያን ያለፈ ልዩነታችንን ትተን» አሉት ያን ጥቁር ሕዝብ «በአንድ ብሔራዊ ድርጅት አማካይነት ባንድነት መቆም አለብን።»1911

ሰወስቱ ምሑራን አመት አልፈጁም።የደቡብ አፍሪቃዉያን ነባር ተወላጆች ኮንግረስ (SANNC)ን መሠረቱ።አላማቸዉ ኋላ ኤ ኤን ሲ የተሰኘዉ ድርጅት ጥቂት ነጭ አንጋፋ አባላት አንዱ ዴኒስ ጎልድበርግ እንደሚያምኑት ደቡብ አፍሪቃን ለሁሉም ዜጎችዋ እኩል ሐገር ማድረግ ነዉ።
                
«በመጀመሪያ የብሪታንያዎች አገዛዝ ያድረሰዉ የነበረዉ በቀለም ላይ የተመሠረተዉ ጭቆና ኋላ ደግሞ በ1948 በሠፈነዉ ሙሉ ረገጣ ሠራተኛዉ ሕዝብ በጣም ተበዝብዟል።በድሕነት ማቅቋል።ለዚሕም ነዉ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት ደቡብ አፍሪቃ ለነጮችም ለጥቁሮችም ሕዝቦቿ እኩል እንድትሆን ለመታገል የወሰነዉ።»

ደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያዉን ነፃ-ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያስተናገደችበት፣ ማንዴላ የፕዝዳትነቱን፣ ኤ.ኤን.ሲ የገዢ ፓርቲነቱን ሥልጣን የያዙበት አስረኛ አመት በሁለት ሺሕ አራት ሲዘከር በአብዛኛዉ አፍሪቃዉያን ምሑራን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡበት ጉባኤ ተደርጎ ነበር።በጉባኤዉ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ካቀረቡት አንዱ ኬንያዊዉ ፕሮፌሰር ዓሊ ማዙሪይ-ጉባኤዉን እንደተራ አድማጭ ይከታተሉ ለነበሩት ለያኔዉ ፕሬዝዳት ታቦ-ኢምቤኪና ለተከታዮቻቸዉ፥ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች የቀድሞ በዳዮቻቸዉን ለመበቀል እስራሎች ከሚፈፅሙት አይነት ስሕተትና በደል እንዲጠነቀቁ ነበር-የመከሯቸዉ።

እርግጥ ነዉ ጥቁሮች የሚበዙበት ኤ.ኤ,ንሲ ሥልጣን ከያዘ ወዲሕ ጥቁሩ ደቡብ አፍሪቃዊ ነጮቹን ለመበቀል የወሰደዉ እርምጃ የለም።ኤ.ኤን. ሲ የቆመለትን ዓላማም በሆነ-ደረጃ ለግብ ማቃራቡ አላጠራጠረም።ሥልጣን ሲይዝ የገባዉን ቃል-ገቢር አድርጓል ማለት ግን በርግጥ ያሳስታል። እንዲያዉ በ2010 የታተመ አንድ ምፀታዊ የቀልድ ካርቱን ANC የተሰኘዉ የፓርቲዉን ምሕፃረ-ቃል Accomulation: Nepotism:Cronysim የሚሉ ቃላትን የሚወክሉ-ይለዋል።ማጋባስ፥ የወዳጅ-ዘመድ፥ የአምቻ ጋብቻ መጠቃቀሚያ ፓርቲ ነዉ-እንደማለት።

እዚሕ የአማርኛዉ ክፍል ሐላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ እንደሚተቸዉ ደግሞ የጥቁሩን አፍሪቃዊ ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል የተገባዉ ቃል-ዛሬም በአስራ-ሰባት አመቱ ገቢር አልሆነም።ደቡብ አፍሪቃ በምጣኔ ሐብት ከአፍሪቃ የሚስተካከላት የለም።ከጥቁር ሕዝቧ የመካከለኛ መደብ የሚኖረዉ ግን ሰወስት ሚሊዮን ነዉ።ሐምሳ ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝባ አርባ በመቶ የሚሆነዉ ጥቁር የወር ገቢዉ ከሐምሳ ዩሮ ብዙም አይበልጥም።

መሪያ ቤት እንደ ችሎታዉ እራስ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ሥራ እንዲሚያገኝ ቃል ከተገባለት ጥቁር አፍሪቃዊ አብዛኛዉ ዛሬም ቃሉ ገቢር ሲሆን አላየም።

የANC ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙሳና የተዘፈቁ ናቸዉ።ጎልድንበርግ እንደሚሉት ዛሬ ነባሮቹ ታጋዮች ሳይቀሩ ሥልጣን ለመያዝ የሚጣጠሩት ለመክበር ነዉ።
                   
«ድሮ የገለሉትና አሁን የደቡብ አፍሪቃን የፖለቲካ ሥልጣን ከያዙት መካካል ብዙዎቹ በየሥፍራዉ ሥልጣን ላይ የወጡ ሰዎች የሚፈፅሙትን እያደረጉ ነዉ።ይሕ ማለት ሥልጣን የሚፈልጉት ከሥልጣኑ ለሚገኘዉ ጥቅም ነዉ።በዚሕ እኛ ከሌሎቹ የተለየን አይደለንም።ይሕ እንዳይሆን ተስፋ አድርገን ነበር።ግን ሆነ።«

የኤ.ኤን. ሲ መስራቾች ራዕይ-ተስፋ የተቀየረዉ ግን በ1960  ነበር።
              
«በ1960 ሻርቪል ዉስጥ ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ የወጡ ስልሳ ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎች በፖሊስ ተገደሉ።ይሕ ጭፍጨፋ ኤ.ኤንሲ ለሐምሳ አመታት ይከተለዉ የነበረዉን ሰላማዊ የትግል ሥልት እንዲለዉጥ አስገደደዉ።እና ኔልሰን ማንዴላ ሕዝባዊ ጦር የተሰኘዉ የድርጅቱ ወታደራዊ ክንፍ እንዲመሰረት አደረጉ።»     

ኦሊቨር ታምቦ፣ ኔልሰን ማንደላ፣ ዎልተር ሲሲሉ፣ ጎቫን ኢምቤኪ፥ ብጤዎቻቸዉና ተከታዮቻቸዉ  የድርጅቱ መርሕ ከሰላማዊ ትግል ወደ ነፍጥ ዉጊያ፥ ከለዘብተኝነት ወደ ከግራ-ኮሚኒስትነት የመግፋታቸዉ ሰበብ-ምክንያት ጥቁሮችን እንደ እንሰሳ የሚገድል፣ የሚያስር የሚረግጠዉ፣ የነቾቹ አገዛዝ፥ ለአገዛዙ ሁለተንናዊ ድጋፍ ይሰጥ የነበረዉ ከካፒታሊስቱ ዓለም አቋም እንደነበር ድሮም ዘንድሮም ብዙ አላነጋገረም።

ማንዴላ ከእስር በተፈቱ ማግሥት ዋሽግተን ለንደኖችን ለመቆራኘት እንደመቸኮላቸዉ ሁሉ ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ወደ ግራ ገፍተዉ፣ ለአርባ-አመት እንደጠላት ከተዋጋቸዉ ወይም እወጋቸዋለሁ ሲላቸዉ ከነበሩት ሐይላት ጋር በቅፅበት የመወዳጀታቸዉ ጥድፊያ ግን በርግጥ አከራካሪ ነዉ።አንጋፋዉ ድርጅት የድሮ አቋሟን ባጭር ጊዜ ለዉጦ ካዲሱ እንዲገባ ሲጠመዘዝ ነባር አባላቱን ማስደንገጡ፥ እድሜ ልካቸዉን ያሰቡ፥ ያለሙ፥ የተዋጉለት አለማ መና እንደቀረ እንዲቆጥሩት፥ ሌሎቹ ደግሞ በየግል ጥቅማቸዉ ላይ እንዲያተኩሩ ማሳሰቡ አልቀረም።

ኤ ኤን ሲ የሚመራት ደቡብ አፍሪቃ ዛሬ ከነብዙ ችግሮቻ ጋር ጥቁሩ ከነጩ፥ ክልሱ-ከቢጫዉ እኩል የሚኖሩ፥ እኩል የሚኖሩ፥ እኩል የሚመርጡ፥ የሚናገሩባት ሐገር ናት።ባንድ አዉቶብስ እኩል የሚጓዙባት፥ የሁሉም ልጆች ባንድ ትሕምርት ቤት እኩል የሚማሩባት ሐገር ናት።ኤ.ኤን.ሲ ስልጣን የያዘበት አስረኛ አመት ጉባኤ ላይ ጥናዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ኢትዮጵያዊዉ ምሁር የፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ያኔ እንዳሉት ደግሞ ኤ. ኤን.ሲ ለአፍሪቃ ያንን ጉባኤ እንደ ተራ ተሳታፊ ይከታተሉ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤክን አይነት አዲስ መሪዎችን አፍርቷል።

«አዲስ አይነት አፍሪቃዊ መሪ አላችሁ» አሉ ፕሮፌሰር ማሞ-ደቡብ አፍሪቃዉያኑን «ገለፃ-የሚያደርግ ሳይሆን ቁጭ ብሎ የሚያዳምጥ መሪ።» የድርጅቱ መቶኛ ዓመት ትናንት ሲከበር የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ያኮብ ዙማ እንዳሉት ድርጅታቸዉ እንደ ኢምቤኪ ትንች ወቀሳን ለመስማት፥ ሰምቶም ሥልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ የሆኑ መሪዎች ካሉት ደግሞ የመቶ-አመቱ አዛዉንት እራሱን ማረቁ አይገዉም።
         
«ኤ.ኤን.ሲ ለመማር ዝግጁ የሆነ ድርጅት ነዉ።የዚያኑ ያክል በሕብረተሰቡ ዉስጥ የመሪነት ሥፍራ እንዳለዉም አይዘነጋም።ትሁት እንጂ-ትዕቢተኛ ድርጅት አይደለም።»

ወደፊት ይታያል።ለዛሬዉ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

የANC መቶኛ ዓመት ፌስታ
የANC መቶኛ ዓመት ፌስታምስል dapd
Flash-Galerie Friedensnobelpreisträger 1993 Nelson Mandela und Frederik Willem de Klerk
ማንዴላና ደ ክላርክምስል AP

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ