የኤርትራ ገፅታ
በሺ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ሀገራቸውን ጥለው በየጊዜው ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ። ይህንን ፍልሰት የኤርትራ መንግሥት አሁን በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ መቀየር ይፈልጋል።
የተሻለ የወደፊት እድል እጦት
ቀደም ሲል አስመራ ብዙ ህዝብ የሚኖርባት እና የምታብብ መዲና ነበረች። ይሁንና የኤርትራ ከተማ አሁን አሁን ሀገሯን ጥለው በሚሰደዱ ዜጎቿ ሳቢያ ክፉኛ እየተፈተነች ትገኛለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየወሩ 5000 የሚጠጉ ሰዎች ከዚችው የአፍሪቃ ቀንድ ሀገር እንደሚሰደዱ ይገምታል። ለዚህም ስራ አጥነት ፣የገቢ ማጣት እና በሀገሪቱ የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይጠቀሳሉ።
ከቁጥጥር ለመዳን አማራጩ ስደት
በተለይ አዲሱ ትውልድ ቁጥጥር ከተጠናከረበት ስርዓት ነፃ መሆንን ያሻል። በሀገሪቱ ህግ መሠረት አንድ ወጣት 18 ዓመት ሲሞላው ለ 18 ወራት ብሔራዊ አገልግሎት መስጠት አለበት። ይህ እንደየ መስኩ ይለያያል። ከጦር ውትድርና እስከ መምህርነት ወይም በጤናው መስክ መሳተፍን ያካትታል። አብዛኛውን ጊዜ ግን በርካቶች ማገልገል ከሚጠበቅባቸው የጊዜ ገደብ በላይ ለመቆየት እንደሚገደዱ ይናገራሉ።
ከአዳጋቹ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ መላቀቅ
ኤርትራ ስደትን ለማስቆም የሚረዳት ድጋፍ አግኝታለች። የስደተኞችን ፍልሰት ማስቆም የሚፈልገው የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ጥር ወር ለኤርትራ 200 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚለግስ አስታውቋል። ይህም እስካሁን የታየውን የመገለል ፖሊሲ የሚያበቃ ይመስላል። ይሁንና ኤርትራ የሶማሊያን አልሸባብ ቡድንን ትደግፋለች በሚል አሁንም ትተቻለች።
ኢትዮጵያ ፤ ውዝግቡ ቢቀጥልመም ስደተኞችን ማስተናገዷ
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት አሁንም ከፍተኛ ውጥረት ይታይበታል። ኤርትራ 1985 ዓም ነጻነቷን ካወጀች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁለቱ ሀገራት በድንበር ውዝግብ ዳግም ተጋጭተዋል። ኢትዮጵያ በኤርትራ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋት መንግሥት ብሔራዊ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ላደረገበት ርምጃው ዋንኛ ምክንያት ሆኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ማይ ዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ይሰደዳሉ።
የወርቅ ማዕድን
ህገ ወጥ ስደትን ለመታገል ኤርትራ ከአውሮፓ ህብረት በምታገኘው የገንዘብ ድጋፍ ኢኮኖሚዋን ማነቃቃት ትሻለች። በአሁኑ ጊዜ ወርቅ፣ መዳብ እና ዚንክን የማውጣቱ ስራ ተነቃቅቷል። በዚሁ ዓመት ሌላ አዲስ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ለመክፈት እቅድ ተይዟል። ሀገሪቱ እኢአ እስከ 2018 ዓም ድረስም ከአራት ማዕድናት ጥሬ ሀብት ማውጣት ትሻለች። በዓለም ገበያ የጥሬ አላባው ዋጋ ቢቀንስም ሀገሪቱ ተስፋዋን በዚሁ ዘርፍ ላይ አሳርፋለች።
ሀብቱ ለሁሉም አይደለም
በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው የቢሻ ማዕድን ማውጫ እስካሁን በምርት ስራ ላይ የሚገኝ ብቸኛው ማዕድን ነው። ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚጠቁሙት ሰዎች በዚህ ማዕድን ማውጫ በትንሽ ክፍያ ለመስራት ይገደዳሉ። ለበርካታ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ሀገሪቱ አማላይ ሆና አልተገኘችም።
የአዲስ ሀገር ምኞት፤ አሜሪካ
የኤርትራ ኢኮኖሚው አሁንም ገና አዝጋሚ ነው። በዚህም የተነሳ ብዙዎች የወደፊት ተስፋቸው አድረገው የሚቆጥሩት ዩ ኤስ አሜሪካ እና አውሮፓን ነው።