የኢየሩሳሌም ዋና ከተማነት መዘዝ
ዓርብ፣ ኅዳር 29 2010በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከዛሬው የሙስሊሞች የጁማ ስግደት እና ፀሎት በኋላ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻዎቹ በሄብሮን በቤተልሄም እና በረመላሕ ከተሞች ተቃውሞ ሲያሰሙ ከፖሊሲች ጋር ተጋጭተዋል። ሰልፈኞች በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ወታደሮች ደግሞ በአፀፋው አስለቃሽ ጢስ እና የላስቲክ ጥይቶች መተኮሳቸው ተዘግቧል። በጋዛ ጎዳናዎችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የትራምፕን ውሳኔ በማውገዝ ሰልፍ ወጥተዋል። እየሩሳሌም በሚገኘው የአል አቅሳ መስጊድ አካባቢም በሺህዎች የተገመቱ ፍልስጤማውያን ሙስሊሞች ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። በግብጽ ርዕሰ ከተማ ካይሮም ከጁማ ስግደት በኋላ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰልፈኞች« እስራኤል ትውደም» «ለፍልስጤማውያን ደማችንን እናፈሳለን ነፍሳችንን እንሰጣለን» ብለዋል። ህንድ በምትቆጣጠረው ካሽሚር ለተቃውሞ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች «አሜሪካ ትውደም» «እሥራኤል ትውደም» የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር። የካሽሚር መሪዎች የትራምፕን እርምጃ ፀረ ሙስሊሞች ሲሉ ኮንነዋል። ዮርዳኖስ ውስጥ የተሰለፉት ደግሞ «እየሩሳሌም አረብ ናት» «አሜሪካን የእባብ ጭንቅላት ናት» የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብተዋል። ኢራናውያንም ቴህራን ውስጥ «ሞት ለአሜሪካ» «ሞት ለእስራኤል» እያሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል። ሶማሊያ መዲና መቅዲሾም ለፍልስጤማውያን አጋርነትን ለመግለፅ በተካሄደ ሰልፍ ላይ «ትራምፕ ይውደም» የሚሉ ፀረ እሥራኤል እና ፀረ አሜሪካ መፈክሮች ተሰምተዋል። በሊባኖስ ከ5 ሺህ በላይ ፣ኢስታንቡል ቱርክ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች የተካፈሉበት ሰልፍ ተካሂዷል። በማሌዥያ ደግሞ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ርዕሰ ከተማ ክዋላላምፑር የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲሲ ፊት ለፊት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸዉ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ለመሆኗ እዉቅና ሰጥታለች ካሉ ወዲህ በመካከለኛዉ ምስራቅ ዉጥረት ነግሷል። የዉሳኔያቸዉ መዘዝ በዛሬዉ ዕለት ፍልስጤማዉያን የቁጣ ቀን አዉጀዉ ከእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲያጋጫቸዉ ዉሏል።
የሰዉ ሕይወት መጥፋቱንም ዘገባዎች ያሳያሉ። እስራኤል እና ፍልስጤም ከሚወዛገቡባቸዉ ጉዳዮች መካከል ሰፊ ድርሻ የያዘችዉ የኢየሩሳሌም ጉዳይ በዉስጧ የሚኖሩትን ፍልስጤሞች ብቻ ሳይሆን በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚገኙ የአረብ እና ሙስሊም ሃገራትንም ቁጣ ቀስቅሷል። በሙስሊሞች ዘንድ የጸሎት ዕለት በሆነዉ ዓርብ በአካባቢዉ ስለነበረዉ ሁኔታ ጄዳ የሚገኘዉን ተባባሪ ዘጋቢያችንን ነቢዩ ሲራክን ስቱዲዮ ከመግባቴ አስቀድሜ በስልክ አነጋግሬዋለሁ።
ነቢዩ ሲራክ/ ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ