የኢትዮጵያ የድርቅ ቀዉስ የገጠሩን ሕዝብ ከአፋፍ ላይ ጥሏል
ኢትዮጵያ ዉስጥ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ለዓለም አቀፍ ስደተኞች ቅድሚያ በሚሰጠዉ የሰብዓዊ ርዳታ ሥርዓት ምክንያት ሕይወታቸዉን ለማቆየት እየታገሉ ነዉ።
የሞት ድባብ በጫንቃቸዉ ላይ
በኢትዮጵያ ከጎዴ 15 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ከሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አቅራቢያ ከቆመችዉ ሴት በስተጀርባ የሞቱ ፍየሎች ወዳድቀዋል። መንግሥት እንደሚለዉ 58 የሚሆኑ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖች በስፍራዉ ርዳታ እያገኙ ነዉ። ሆኖም ግን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2016ዓ.ም ማለቂያ ላይ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት «IOM» ባካሄደዉ ቅኝት በ 222 መጠለያ ጣቢያዎች 400,000 ተፈናቃይ ወገኖች እንደሚኖሩ ታዉቋል።
የደረቀ መሬት
በታሪክ እጅግ ከከፉ ድርቆች አንዱ በአፍሪቃዉ ቀንድ አካባቢ ተከስቷል። ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ሞት የሚያስከትል የርሃብ አደጋ እንዳለ ተገልጿል፤ ይኸዉ እዉነታም ሶማሊያ እና የመን ላይም እዉነት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ምንም እንኳን ጎረቤት ሶማሊያን ያጋጠማት ተመሳሳይ የአየር ጠባይ እና የዝናብ እጥረት በኢትዮጵያዉ ሶማሌ ክልል ዉስጥ ቢታይም በአንፃራዊነት የተረጋጋ እና ግጭት የሌለበት አካባቢ በመሆኑ የከፋ አይደለም። ሆኖም ግን ቀዉስ ሊያጋጥም ይችላል።
መሄጃ የለም
«አብዛኞቹን ከብቶቻቸዉን አጥተዋል፤ በዚያም ላይ የቀሪዎቹ እንስሶቻቸዉን ሕይወት ለማቆየት ሲሉ ያጠራቀሟትን ገንዘብም ለማዉጣት ተገደዋል።» ይላሉ በኢትዮጵያ የሕፃናት አድን ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ቻርሊ ማሶን። «ሁሉንም ያጡት ደግሞ ማድረግ የሚችሉት ምግብ እና ዉኃ ለማግኘት ወደ መንግሥት የርዳታ ጣቢያዎች መሄድ ነዉ።»
ባለአራት እግሩ የኑሮ ዋልታ
ከብቶች የክልሉ ኤኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸዉ። የደቡብ ኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች 182 ሚሊየን ዮሮ በላይ የሚገመቱ ከብቶች፣ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎችን አጥተዋል። ሥጋ እና ወተት የአርብቶ አደሮችን የኑሮ መደጎሚያ ሥርዓትን ይወክላሉ። «እንዲህ ያለ ድርቅ በዕድሜዬ አይቼ አላዉቅም።» ይላሉ የ80 ዓመቱ አዛዉንት አቢካር መሐመድ። «ቀደም ባለዉ ጊዜ ሁሉም ሳይሆኑ ጥቂት እንስሳት ይሞቱ ነበር።»
የእንስሳት ክስረት
«የበፊቱ ዕቅዴ ዝናቡ ከመጣ ከብቶቹን በሙሉ ሸጬ ገንዘቡን ቤተሰቤን በሙሉ ወደ ከተማ ለማዛወር አዉለዋለሁ የሚል ነበር፤ ግን አሁን ዕቅዴ ሁሉ ተበላሸ።» ይላሉ የ40 ዓመቱ ሙክታ መሐመድ። ከብቶችና እንስሳቶቻቸዉን ለመግዛት ለስድስት ዓመታት ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ትንሽ ሱቅ ከፍተዉ በመነገር ገንዘብ አጠራቅመዉ ነበር። በድርቁ ምክንያት ግማሾቹ ሞቱባቸዉ፤ የተረፉትም በተዳከመ ሁኔታቸዉ ምክንያት ዋጋ የሚያወጡላቸዉ አይመስሉም።
ስሜት የሚነካ ጉዳይ
«ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ብቻ ነዉ ሀገር ዉስጥ ስለተፈናቀሉ ሰዎች መነጋገር መጀመር የቻልነዉ።» ይላሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚሠራ የሰብዓዊ ጉዳዮች ተቋም ዳይሬክተር። «ሆኖም መንግሥት ጉዳዩን ወደጎን ማለት እንደማይችል በማወቁ ስለእዉነታዉ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ ነዉ።» «IOM» እንደሚለዉ በመላዉ ኢትዮጵያ በሚገኙ 456 መጠለያ ጣቢያዎች 696,000 ተፈናቃዮች ይገኛሉ።
የሰብዓዊነት ነፀብራቅ
የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች ድርቁ ባደረሰበት ጉዳት ምክንያት በራሱ አቅም መነሳት ያልቻለዉን ግመል መቆም እንዲችል ይረዱታል። «ሰዎች ድንበር ሲሻገሩ ዓለም ይበልጥ ለጉዳዩ ፍላጎት ያሳያል።» ይላሉ ጎዴ የሚገኘዉ የተመድ ቡድን ባልደረባ ሃሚዱ ጃሌህ። «በተለይ ደግሞ የግጭት የሚሸሹ ከሆነ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ይሆናል። በሀገር ዉስጥ የሚፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ ያን ያህል ቀልብ የመግዛት አቅም አይኖረዉም።»
ስደተኞች እና የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች
40,000 ሶማሌያዉያን የሚኖሩበት ይህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይዞታ በአንጻራዊነት ሲታይ ጥሩ ነዉ። ስደተኞቹ አብዛኞቹ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ማግኘት የማይችሉትን ሀገር፣ ዉኃ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት በነፃ ያገኛሉ። «ስደተኞችን መርዳትን አንቃወምም፣ ለትልቅ ችግር የተጋለጡ እንደመሆናቸዉ ሊረዱ ይገባል።» የሚሉት በአቅራቢያዉ ባለዉ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች መኖሪያ ጣቢያ የሚገኙት የ70 ዓመቱ አቢዩ አልሶዉ። «ሆኖም ግን ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ምንም ስለማናገኝ ይረብሸናል።»
ያለዉ አቅም ተሟጧል
በኤልኒኞ ሰበብ በመጣዉ ድርቅ ምክንያት የተጎዱትን 10 ሚሊየን ሰዎች ለመርዳት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተጓዳኞች ያደረጉትን ጥረትና ያወጡትን 1,64 ቢሊየን ዶላር በማስታወስ፤ «ባለፈዉ ዓመት የነበረዉ የመንግሥት ምላሽ የሚደነቅ ነበር።» ይላሉ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራዉን። «የያኔዉን አስጊ ሁኔታ አልፈናል። አሁን ግን የገንዘብ ድጋፉ ጉዳይ በሁለቱም ወገን ሰፊ ክፍተት አለበት።»
አሁን ላይ መጣበቅ
«ሰዎች በሚመገቡትም ሆነ በሚሸጡት ተጠቅመዉ ሕይወታቸዉን ለማቆየት ይችሉ ነበር፤ አሁን ግን ምን የቀረ ነገር የለም።» 650 የተፈናቀሉ የአርብቶ አደር ቤተሰቦች የሚገኙበት መጠለያ ቦታ የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ተፈናቃያዮች ምንም ዓይነት እርዳታ እንደማያገኙ ነዉ የሚናገሩት። እንደተገመተዉ በቂ የመፀዉ ዝናብ የማይኖር ከሆነ የከብቶቹ እልቂት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል። ምክንያቱም አርብቶ አደሮቹ የቀሯቸዉን ከብቶቻቸዉን የሚያቆዩበት አቅም በበልጉ የዝናብ ወቅት ማግኘት አይችሉም። SL/AT