1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ወዳጁ ታዋቂው ጀርመናዊ ደራሲና ጋዜጠኛ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 20 2012

ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የአፍሪቃ ሃገራት ኩራት፤ የአድዋ ድልም ኩራቴ፤ ራሳቸውንም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለዉ ሲናገሩ በኩራት ነዉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ አገዛዝ ዘመን በረሃብ ተሰቃይተው እንደነበር፤ ምግብን ጠግበዉ በልተዉ እንደማያውቁም ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/3SI9V
Theodor Wonja Michael
ምስል DW/Pareigis

ጀርመናዊዉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲሉ ነበር የሚናገሩት

ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የአፍሪቃ ሃገራት ኩራት፤ የአድዋ ድልም ኩራቴ፤ ራሳቸውንም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለዉ ሲናገሩ በኩራት ነዉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ አገዛዝ ዘመን በረሃብ ተሰቃይተው እንደነበር፤ ምግብን ጠግበዉ በልተዉ እንደማያውቁም ተናግረዋል።  በቆዳ ቀለማቸው በገጠማቸው መገለል ስቃይ ደርሶባቸውም አሳልፈዋል፤ ጥቁሩ ጀርመናዊ ሚሻኤል ዋንጃ ቴዮዶር። በ 94 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ውስጥ የወጣትነት ዕድሜያቸውን በስቃይ ያሳለፉት ሚሻኤል ቴዮዶር፤ ጦርነቱ አልፎ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው እዚሁ ጀርመን በተለያዩ ጋዜጦችና የመገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። ለጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፤ ብሎም  ደራሲም  ነበሩ። በተለይ በጎርጎረሳዊው 2013 ዓ.ም ለአንባብያን ይፋ የሆነዉ «ጀርመናዊ መሆን በዚያ ላይ ጥቁር» በሚል ርዕሥ የሕይወት ታሪካቸውን የሚያሳየዉ መጽሐፋቸው በጀርመን የመጽሐፍ ሽያጭ መዘርዝር የመጀመርያውን ስፍራ ይዞ ነበር። በእዚህ ዝግጅታችን በአባታቸው ካሜሩናዊ በእናታቸው ጀርመናዊ እሳቸዉ ራሳቸዉ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ይናገሩ ስለነበረው ስለ ጥቁሩ ጀርመናዊ ቴውዶር ሚሻኤል ሕይወት ታሪክ ቅንብር ይዘናል ።

DW Projekt Afro.Deutschland - Theodor Wonja Michael
ምስል DW/S. Jacob-Engelmann

የዛሬ ሁለት ሳምንት በ 94 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ደራሲ ሚሻኤል ቴዮዶር በጎርጎረሳዉያኑ 1925 ዓ,ም ከካሜሩናዊዉ አባታቸዉና ከጀርመናዊትዋ እናታቸዉ በርሊን ተወለዱ።  የፋሺስት ናዚን ዘረኛ አገዛዝ ሥርዓትን እና የሁለተኛዉን የዓለም ጦርነትን ከከባድ ችግር ጋር ያሳለፉት ቴዮዶር ሚሻኤል፤ በዘመኑ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንካ ፈቃድ አልነበራቸዉም። ቴዮዶር የኋላ ኋላ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አበቃና በበርሊን የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ፈቃድን አገኙ። ከስድስት ዓመት በፊት ቴዮዶር ለአንባብያን ያበቁት በጀርመንኛዉ «ዶች ዛይን ኡንድ ሽቫርዝ ዳዙ» ማለት «ጀርመናዊ መሆን በዝያ ላይ ጥቁር»  በተሰኘዉ የሕይወት ታሪካቸዉን በያዘዉ መጽሐፋቸዉ የጥቁር ሕዝብ ኩራት በሆነዉ በ«አድዋ ድል» እንደሚኮሩ፤ ኢትዮጵያዊ መባልም እንደሚያስደስታቸዉ በግልፅ አስቀምጠዋል። ሕጻን ሳሉ ወላጆቻቸዉን ሞት የነጠቃቸዉ ሚኃኤል ቲዮዶር፤ ጀርመናዊት እናታቸዉ ከካሜሩን የመጡትን አባታቸዉን በጎርጎረሳዉያኑ 1910 ዓም በርሊን ዉስጥ የተዋወቅዋቸዉ  መሆኑን በመጽሐፋቸዉ ተርከዋል። ቴዮዶር የዛሬ አምስት ዓመት ከዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ስርጭት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በዝያ ዘመን እናቴ አባቴን ተዋዉቃ በፍቅር ስትያዝ፤ አብዮትን ያህል ትልቅ ለዉጥ ሳታሳይ አልቀረችም ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና አባት እና እናታቸዉን ግንኙነት በጥልቅ ለመጠየቅ በጣም ሕጻን ስለነበርኩ ብሎም አስፈላጊም ስላልመሰለኝ ይሆናል ብዙ አላዉቅም ሲሁ በቁጭት ነግረዉን ነበር።

«አባቴ የካሜሩን ተወላጅ ነዉ። ካሜሩን በጎርጎረሳዎያኑ 1884 ዓ,ም የጀርመን ቅኝ ግዛት እንደሆነች ይታወቃል። አባቴ ፤ ካሜሩን ፤ በጀርመን የቅኝ ግዛት ስር ከመዉደቅዋ በፊት አልያም የቅኝ ግዛት ልትሆን ስትል ነዉ ወደ ጀርመን የመጣዉ። አባቴ ወደ ጀርመን ስለ ገባበት ግዜ፤ ቤተሰቦቼ የሚሉት የተለያየ አመለካከት ነዉ። ያም ሆነ ይህ በአባቴ ወገን ያለዉ አያቴ በዝያን ግዜ ካሜሩን በጀርመን የቅኝ ግዛት ስር አንድትሆን ስምምነትን ከፈረሙ ታላላቅ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ነበር»

በዝያን ግዜ አያቴ ከጀርመናዉያኑ ጋር የቅኝ ግዛት ዉሉን ሲፈራረሙ ካሜሩናዉያኑ የሚያዉቁት ነገር አልነበረም የሚሉት ቴዉዶር ሚሻኤል፤ ስለ ቅኝ ግዛቱ ዉል እንዲህ ነበር የነገሩትን፤ « ካሜሩናዉያኑ በቅኝ ግዛት ለመዉደቅ በዉል ሲፈራረሙ በርግጥ የሚያዉቁት አንዳችንም ነገር አልነበረም። ትምህርት ቤት እንኳ ምን እንደሆነ አያዉቁም፤ አይፅፉም፤ አያነቡም። ጀርመናዉያኑ ለመፈራረም ያቀረቡት የስምምነት ዉል በቋንቋ ምክንያት በተደጋጋሚ ተተርጉሞ እንዲረዱት በተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ እንደነበር ከታሪክ ተረድቻለሁ። እዚህ ላይ ለማለት የፈለኩት አባቴ ወደ ጀርመን የመጣዉ ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት ነዉ። ከዝያም እናቴን በርሊን ከተማ ላይ ተዋዉቆ በጎርጎረሳዊዉ 1915 ዓ,ም ትዳር መስርቶ አራት ልጆችን አፍርተዋል፤ እኔ ደግሞ የመጨረሻ ልጅ ነኝ»

ቴዮዶር ሚሻኤል ለቤተሰቦቻቸዉ የመጨረሻ ልጅ ነበሩ፤ ሌሎች ሦስት ወንድምና እህቶች ነበሯቸዉ። የመጨረሻ ልጅ ቴዮዶርን ከወለዱ በኋላ ሕመምተኛ የሆኑት የቴዶር ጀርመናዊትዋ እናቱ ቴዮዶር አንድ ዓመት እንደሞላቸዉ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። ካሜሩናዊ አባታቸዉም ቢሆኑ በናታቸዉ ሞት ሃዘንና ብቸኝነት ጠጭ ሆነዉ ቴዮዶር 9 ዓመት እንደሞላቸዉ እንደተለዩዋቸዉ አጫዉተዉን ነበር። ቴዮዶር 18 ዓመት እንደሞላቸዉ በዝያን ጊዜዉ የናዚ ስርዓት የስራ ዘመቻ ተልከዉ ነበር። እንዲህ ነበር ያስታወሱት፤

«የሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት አይቻለሁ። በወቅቱ ትምህርት ቤት መሄድ ተፈቅዶልኝ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህቴንም አጠናቅቄያለሁ ግን፤ በዝያንግ ግዜ የኑረንበርገር ህግ ተብሎ በሚጠራዉ የናዚ መንግስት ህግ መሰረት የከፍተና ደረጃ ትምህርቴን መከታተል አልተፈቀደልኝም። ምክንያቱም በህጉ መሰረት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን መከታተል የሚችሉት ነጭ የቆዳ ቀለም እንዲሁም ሰማያዊ የአይን ቀለም ያላቸዉ የሰሜን አዉሪጳ ተወላጆች ብቻ ነበሩ። እንዲህ አይነቱን ህግ እንደኔ ያለ ጥቁር አፍሪቃዊ ሰዉ ለመረዳት በጣም ይከብደዋል።»

በጥንት ዘመን አቢሲኒያ ትባል የነበረዉ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልወደቀች ብቸኛዋ አፍሪቃዊት ሃገር መሆንዋን ፤ 1896 ጣልያን ድል ከሆነበት ከአድዋ ድል በኋላ የአዉሮጳ ፖለቲካም መቀየሩን፤ 1935 ጣልያን ዳግም ኢትዮጵያን ለመዉረር መታተሩን ቴዮዶር ሚሻኤል በመጽሐፋቸዉ ከትበዋል። ቴዮዶር ኢትዮጵያን በታሪክዋ ተዋዉቀዉ ከዝያም 1937 ዓ.ም ፃድቅ ከተባለ ኢትዮጵያዊ ጋር ጀርመን ሃንቡርግ ላይ ተዋዉቀዉ በአንድ ሰርከስ ዉስጥ እንደ ብርቅዬ ጥቁር ሰዉ ለማገልገል በአንድ ሰርከስ ተቀጥረዉ ወደ ስዊድን መጓዛቸዉን ያስታዉሳሉ። ግን ግን ከሁሉ ከሁሉ በጣም ከማይረሳቸዉ ነገር በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊ መባል ክብር እንደነበር እንዲህ ብለዉ ነግረዉን ነበር።

DW Projekt Afro.Deutschland - Theodor Wonja Michael
ምስል DW/S. Jacob-Engelmann

« አዎ ስዊድን ነበርኩ። በዝያ ወቅት ስዊድን የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ ሃገር ነበረች። ባጠቃላይ የስካንዲኒቪያን ሃገራት በሙሉ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸዉ። በአንድ የጀርመን ሰርከስ ቡድን ዉስጥ እኔ እና አንድ ወልደፃድቅ የሚባል ኢትዮጵያዊ እንደ ብርቅዬ ጥቁር ህጻናት ለአንድ ዓመት ስዊድን ዉስጥ ቆይተን የተለያዩ ዝግጅቶችን አሳይተናል። ለነገሩ በዝያን ግዜ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መታየቱ እንደ ፖለቲካ ጨዋታ መሆኑ ነበር። እና እኔም ኢትዮጵያዊ ነህ ተብዬ ወደዝያ ስላክ፤ የ12 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከጀርመን አብሮኝ ወደ ስዊድን የተጓዘዉ ወልደ ጻድቅ የተባለዉ ባልደረባዩ ከዝያ ተመልሰን በርሊን ሽፓንዳዉ ይኖር ነበር ። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኃላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። »

በናዚ አስተዳደር ቴዉዶር ሚሻኤል ቀን ከለሊት በግዳጅ ግንባታ ስራ ላይ ተሰማርተዉ ይሰሩ አንደነበር፤ በ 24 ሰዓት ለአንድ ግዜ ብቻ እረፍት እንደነበራቸዉ፤ ረሃብ እና የእንቅልፍ እጥረት ይማቅቁ እንደነበር በመፃሃፋቸዉ አስቀምጠዉታል። ቴዉዶር ሚሻኤል የሁለተኛዉ ዓለም ከተጠናቀቀ በኃላ በጀርመንዋ የወደብ ከተማ ሃንቡርግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፖለቲካ ሳይንስና የኤኮኖሚ ትምህርታቸዉን ጀምረዉ ፓሪስ በሚገኘዉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀዋል። ለብዙ ዘመናት በጋዜጠኝነትና በአፍሪቃ ጉዳይ በአማካሪነትም ሰርተዋል፤ ከጀርመኑ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ ዶይቼ ቬለ ተባባሪ ሰራተኛም ነበሩ። አፍሪቃን ተጉዘዉ ያዉቋሉ? ኢትዮጵያንስ ጎብኝተዋት ይሆን? 

« ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከዓመታት በኃላ የኤኮኖሚ እና ፤ በማህበራዊ የከፍተኛ ትምህርቴን ተከታትዬ ፤ በጋዜጠኝነት እንዲሁም በጀርመን መንግስት አስተዳደር ዉስጥ በአማካሪነት አገልግያለሁ። በኮለኝ ከተማ ዉስጥ ለረጅም ዓመታት በአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ዘገባዎችን አቅርቤያለሁ። የዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ እንደተመሰረተ በተለይ በመጀመርያዎቹ ዓመታት፤ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ እና አስተያየቶችን በመስጠት በማማከር ከዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ ጋር ለዓመታት በቅርበት ሰርቻለሁ» ቴዉዶር ሚሻኤል ስለ አፍሪቃ ታሪክ በጥልቀት በማወቃቸዉ በጀርመን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች በአማካሪነት አገልግለዋል። ግን አፍሪቃንስ ጎብኝተዉ ይሆን? « የተለያዩ ሃገራትን ለተደጋጋሚ ግዝያት ጎብኝቻለሁ። እንዲሁ ካሜሩንን ተመላልሼ ጎብኝቻታለሁ። ያዉ እንደሚታወቀዉ ካሜሩን የአባቴ ሃገር ነዉ። አንድ የአፍሪቃዊ ክልስ ከአዉሮጳ ወደ አፍሪቃ ሲመጣ፤ ሃገሪነዉ በሚለዉ በዚያ የአፍሪቃ ሃገርም ቢሆን ባዳ መሆኑ የታወቀ ነዉ። እንዲህ ስል ካሜሩንን ስጎበኝ አቀባበል አልተደረገለኝም ማለቴ አይደለም። ሌላዉ የኢትዮጵያን ታሪክ በተለይ እጅግ የሚያረካኝ የአድዋ ታሪክ ጠንቅቄ ባዉቅም፤ ኢትዮጵያን አልጎበኘኋትም፤ ለምን እንደሆን ግን እኔም ራሴ መልስ ያላገኘሁለት እና የሚቆጨኝ ጉዳይ ነዉ።»

Die Eltern von Theodor Wonja Michael
ምስል Familie Michael

ኢትዮጵያዉያንን አፍቃሪዉ ጀርመናዊ በሕይወት ዘመናቸዉ የኢትዮጵያ አፈር ባይረግጡም ባለፉት 40 እና 50 አመታት ወደ ጀርመን የመጡ ኢትዮጵያዉያንን ሲያላምዱ፤ በእምነታቸዉ ወንጌላዊ ቢሆኑም በተለይ በኮለኝ ከተማ የሚገኘዉን የኢትዮጵያዉያኑን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን ክብር እንግዳ ሆነዉም ይገኙ ነበር። ቴዮዶር ሚሻኤል የኢትዮጵያዊዉን ንጉሠ ነገስት አፄ ኃይለሥላሴን አግኝተዋቸዉ ያዉቁ ነበር? እንደሚታወቀዉ ንጉሰነገስቱ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ ፌደራል ጀርመን መንግሥት እንደተመሰረተ በመራሔ መንግስት ኮነራድ አደናወር ይመራ የነበረዉን ምዕራብ ጀርመንን የጎበኙ የመጀመርያዉ የዓለም ሃገር መሪ ነበሩ። 

 «በ1960 ዎቹ መጨረሻ የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ አልጀርስ ላይ በተደረገ ግዜ ተገኝቼ ነበር። በዝያ ወቅት አፄ ሃይለ ስላሴን በአይኔ አይቻቸዋለሁ። ታድያ ሁል ግዜ የንጉሰ ነገስት ሃይለ ስላሴ መጨረሻዎቹ የስልጣን ቀናት በጣም ከሚሳዝኑኝ ክስተቶች አንዱ ነዉ» የደራሲ ቴዉዶር «ጀርመናዊ ዜጋ ሆኖ ጥቁር መሆን» በተሰኘዉ የህይወት ታሪካቸዉን ያስቀመጡበት መፀሃፍ በጀርመን የመፃህፍ ሽያጭ መድረክ ብዙ አንባብያን በመግዛታቸዉ ተወዳጅ መሆኑ ተነግሮለታል፤ ደራሲዉ መፃህፉን ካነበቡ ሰዎች ምን አይነት አስተያየት ደረሶአቸዉ ይሆን፤ « የሚገርመዉ እስካሁን የጀርመንን ታሪክ የሚያሳይ መፃህፍ ነዉ በማለት ሙገሳ እና ማበረታቻ አይነት አስተያየት ብቻ ነዉ የደረሰኝ ፤ ግን እኔ በተቃራኒዉ ማለትም ስለመፅሐፉ ትችት ቢደርሰኝም በጣም ደስ ባለኝ ነበር፤ ግን እስካሁን ገንቢ ሂስ ብቻ ነዉ ያገኘሁት»

DW Projekt Afro.Deutschland - Theodor Wonja Michael
ምስል DW/S. Jacob-Engelmann

ጀርመናዊ ቴዉዶር ሚሻኤል፤ በናዚ አገዛዝ ዘመን በዘረኝነት በረሃብ ቢሰቃዩም   ለዓላማቸዉ በፅኑ ታግለዋል፤ የናዚ ዘመን ተገርስሶ፤ በጀርመን የዲሞክራሲ ስርዓት ሰፍኖ፤ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ፤ እዉቅ ጋዜጠኛና፤ደራሲ እንዲሁም ለጀርመን መንግስት የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪና፤ የጀርመን አፍሪቃ አምባሳደር ሆነዉ አገልግለዉ ላይመለሱ ይችን ዓለም ተሰናብተዋል። 94 ዓመታቸዉ ነበር። በዚህ ሳምንት ሰኞ በኮለኝ ሎንግሪሽ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አማኑኤል ወንጌላዊት ቤተ ክርስትያን ፤ የሽኝት መረሃግብር ተካሂዶአል። በዚህ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አስተዳዳሪና የኮለኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ሊቀካህናት ዶ/ር መራዊ ተበጀ የቴዮዶር ሚሻኤል የቅርብ ወዳጅ ነበሩ። ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ