1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የኢትዮጵያ አናዳጅ ገፅታ» አምነስቲ

ሐሙስ፣ መጋቢት 20 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት፤  በመናገራቸዉ እና በመጻፋቸዉ ለዓመታት በእስር የማቀቁ ኢትዮጵያዉያንን በተለቀቁ ማግሥት ዳግም ማሰሩን የሚያሳዝን እና አናዳጅ ነዉ ሲል የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አወገዘ።

https://p.dw.com/p/2vDPe
Amnesty International Logo
ምስል picture-alliance/dpa

«እስረኞች ፍትህ ያግኙ» አምነስቲ

ድርጅቱ ባወጣዉ መግለጫ ታስረዉ የተፈቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ ጋዜጠኞች፤ ዓምደኞች እና ፖለቲከኞች ዳግም መታሰራቸዉ የመንግሥት ባለስልጣናት ስልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የመብት ጥሰት እያካሄዱ መሆናቸዉን በግልጽ የሚያሳይ ነዉ ሲል ገልፆአል።  አዜብ ታደሰ የድርጅቱን የምስራቅ አፍሪቃ ተመራማሪን አነጋግራ ዘገባ አጠናቅራለች።   

የኢትዮጵያ መንግሥት ያሠራቸዉን የፖለቲካ እስስረኞች እፈታለሁ ብሎ መግለፁ ለታሳሪ ቤተሰቦች ለታሳሪዎችና ብሎም ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሁሉ ሳይቀር ዜናዉ እንደ ሙዚቃ እፎይታን ፈጥሮ ሳለ መንግስት የፈታቸዉን ዳግም ሰብስቦ ማሰሩ የሚያበሳጭ ነዉ ፣ጉዳዩ አሳስቦናል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣዉ መግለጫ ገልፆአል።

መንግስት በርካታ እስረኞች ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል የተፈፀመበትን  «ማዕከላዊ» እስር ቤትን እዘጋለሁ ሲል መግለፁንም ድርጅቱ በመግለጫዉ አስታዉሶአል። ባለፈዉ እሁድ ዳግም ለእስር የተደራጉት ጋዜጠኞችና ዓምደኞች በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል ያሉት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪቃ ተጠሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ፤ መንግስት የገባዉንም ቃል ያክብር ሲሉ ተናግረዋል። መምህርና አምደኛ ስዩም ተሾመ እንዲሁም በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታየ ደንደአ፤ ያለምንም ፍርድ እስር ላይ እንደሚገኙ የገለፁት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ አቶ ፍስሃ፤ ታሳሪዎች ፍትህ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ወደፊት ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ዶክተር አብይ አሕመድ የእስረኞችን መፈታት እንዲሁም በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመቅረፍ ይጥራሉ የሚል ተስፋ አለን ያሉት የምስራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግሥትን የሚናገሩ ሰዎችን አፍ ለማስያዝ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም ሲሉ ተናግረዋል። ባለፈዉ ዓመት ለ 10 ወራት በዘለቀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይላት ከ 26 ሺህ በላይ ሰዎችን አስረዋል፤ ታሳሪዎቹም ግፍና በደል ተፈፅሞባቸዋል። ከዚያ በኋላ እስር ቤት የቆዩ ከሰባት ሺሕ በላይ እስረኞችን  መንግሥት በምሕረት መለቀቃቸዉን አምንስቲ ኢንተርናሽናል አስታዉሶ፤ ከእስር ከተፈቱት መካከል ታዋቂዉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካቶች ዳግም መታሰራቸዉን አስታዉቋል።

መጋቢት አንድ ቀን በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች በስህተት ፈፀሙት በተባለዉ ተኩስ በትንሽ ግምት 10 ሠዎች መገደላቸዉን፤15 መቁሰላቸዉ እና ቢያንስ ከ 8000 ሺህ በላይ ሰዎች ድንበር አቋርጠዉ ወደ ኬንያ መፍለሳቸዉ የአሚነስቲ ዘገባ ያሳያል። 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ