የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እና የአምነስቲ ግምገማ
ሐሙስ፣ የካቲት 15 2010ባለፈዉ ዓመት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ በመንግሥት መረጃ መሠረት 26 ሺህ ገደማ ዜጎች ታሥረው እንደነበር ያመለከቱት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ አቶ ፍሰሀ ተክሌ፤ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2017 ዓ.ም. የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ብዙም አጥጋቢ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በወቅቱ ከታሠሩት 20ሺህ ያህሉ በዚያዉ ዓመት ቢለቀቁም ቀሪዎቹ ሲንገላቱ እንደነበር ዘርዝረዋል። በመቶሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችም በዚሁ ዓመት መፈናቀላቸዉንም አብራርተዋል።
ከዚህም ሌላ አቶ ፍሰሀ በተጠቀሰዉ ዓመት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያትም ሆነ በፀረ ሽብር አዋጁ የተከሰሱ ሰዎች ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸዉም አምነስቲ በዘገባዉ በዝርዝር ማዉጣቱንም አመልክተዋል።
ምንም እንኳን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተለያየ መልኩ መፈጸማቸዉን ተጎጂዎች አቤት ቢሉም ተገቢ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተጠያቂነት ወደ ሕግ እንዳልቀረቡ ነዉ የአምነስቲ ዘገባ የሚያመለክተዉ። አቶ ፍሰሃም ይህንኑ ያጠናክራሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረዉን ጨምሮ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንደሚከታተል ያመለከቱት የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ፤ አሁን በቅርቡ የሚታዩት የመብት ይዞታዎች በፊት ከነበረዉ ብዙም እንደማይለዩ ሳይገልፁ አላለፉም። እጅግ አሳሳቢ የሆነ ነው ያሉትንም እንዲህ ጠቅሰዋል።
አቶ ፍሰሀ አክለውም መንግሥት የተወሰኑ የሕሊና እስረኞችን ፈትቶ እና የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አደርጋለሁ ባለበት ጊዜ፤ የሰብዓዊ መብትን በተለያየ መልኩ የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ በሀገሪቱ ዳግም መታወጁ አምነስቲን እንደሚያሳስበው አመልክተዋል።
የአምነስቲን ዘገባ አስመልክቶ በዋትስ አፕ ከደረሰን አስተያየት መካከል፤ «የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ብሎም እየባሰበት ሔደ እንጅ ምንም መሻሻል አልተስተዋለም እንደ ቆሎ እየቆነጠሩ ሀያ እና ሰላሳ የህሊና እና የፓለቲካ እስረኞችን ከዕስር እየለቀቁ በሺ የሚቆጠሩ ንፁሀን ኢትዮጵያዉያን ቀን ከሌት ያግዛሉ» የሚለው አንዱ ነው። በፌስ ቡክ ገጻችን ላይ ደግሞ ፒተር በሚል ስም፤ «ይህ መንግሥት የሚፈጽመውን ዘርዝረን አንዘልቀውም የተደበቁ ብዙ ነገሮች አሉ» ሲሉ፤ ታየ ምሳሌ የተባሉ ደግሞ «አንድ ቀን መጠየቃቸዉ አይቀርም» የሚል አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። ሙሉቀን ደግሞ «ዝምታ ነው መልሴ ምን ይባላል ሆድ ይፍጀው» ብለዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ