1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማህበሩ ጥያቄው ካልተመለሰ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ አስጠንቅቋል

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2011

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የሀኪሞችን የስራ ማቆም አድማ እንደማይደግፍ እና እንደማይተባበር ገልጿል። አሁንም ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም ያሉ የተወሰኑ የህክምና ባለሙያዎች በሃገሪቱ አንጋፋ በሆነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታ ትላንት የጀመሩትን የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/3Icbx
Äthiopien, Medizinische Vereinigung
ምስል DW/S. Muchie

ማህበሩ ጥያቄው ካልተመለሰ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ አስጠንቅቋል

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በጤና ባለሙያዎች ሲደረጉ የነበሩ ሰላማዊ የአደባባይ ጥያቄዎችን እንዳልመራ፣ በሂደትም የተከሰተውን የስራ ማቆም አድማ እንደማይደግፍ እና እንደማይተባበር አስታወቀ። ማህበሩ ይህንን እያደረገው ያለውን አካል በውል እንደማያውቅ እና ያንን ካደረጉት አካላት ጋርም በተቃርኖ እንደሚቆም ለጋዜጠኞች ተናግሯል። አካሄዱ ከሃኪሞች የማይጠበቅ እና ማህበሩ የማያምንበት እንደሆነም ተገልጻል።

በተለይ በወጣት የህክምና ባለሙያዎች ዘንድ "አይወክለንም" የሚል ተደጋጋሚ ትችት የሚሰነዘርበት ማህበሩ በሃኪሞች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው ብሏል። ለዚህ ማሳያውም "ሃኪሞች ልጅ ማስተማር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ በኑሮአቸውም የሞራል ድቀት እያስተናገዱ ያሉ ናቸው" በማለት አብራርቷል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ የተነሱትን ጥያቄዎች ይፈታል ተብሎ የተቋቋመው ኮሚቴ ባለቤቶቹን ያገለለ ነው። ኮሚቴው ችግሩን ከስሩ ይፈታል ተብሎ ዕምነት የሚጣልበት አለመሆኑንም ገልጸዋል።

"የጤናው ዘርፍ በውስብስብ ችግር የተተበተበ፣ ጠይቀንም ምላሽ ያጣንበት ነው" ብለዋል የማህበሩ ሃላፊዎች። ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጽ ስንሰራ ብንቆይም። ባለፉት 27 አመታት የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ በማስተላለፍ በታካሚና አካሚ መካከል እምነት እንዲሸረሸር ብሎም አጠቃላይ ዘርፉ እምነት የለሽ እንዲሆን ሰርተዋል በማለት ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡ማህበሩ ምላሽ ያግኙ ያላቸው ጥያቄዎች ካልተመለሱ ግን ሰላማዊ ሰልፍ እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡የህክምና ባለሙያዎች አሁንም ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም በማለት ትናንት በሃገሪቱ አንጋፋ ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ ውስጥ ሳይቀር የስራ ማቆም አድማው ቀጥሎ ጉዳዮ እየተባባሰ መሄዱን አመልክቷል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

ሰለሞን ሙጬ

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ