የኢራን የኒኩሊየር መርሃግብር ድርድር
ረቡዕ፣ መጋቢት 23 2007ማስታወቂያ
ላለፉት ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየዉ ድርድር ካለዉጤት እንዳይበተን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ እና ጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬም ከኢራኑ አቻቸዉ ሞሀመድ ጃቫ ዛሪፍ ጋ በስዊዘርላንዷ ሎዛን ከተማ ንግግር መቀጠላቸዉ ተዘግቧል። የሩሲያ፤ ቻይና እና ፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ግን ትናንት ማምሻዉን ወደየሀገራቸዉ መመለሳቸዉ ተሰምቷል። ትናንት ዉይይቱ ሲቋረጥም የኢራኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ መገኘቱን ተናግረዋል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በድርድሩ አግባቢ ነጥብ ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋቸዉን ገልጸዋል። የኢራንን የአቶም መርሃግብር በስጋት የምትከታተለዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸዉ ድርድሩ ትርጉም ያለዉ ስምምነት እንዲያስገኝ አጥብቀዉ እያሳሰቡ ነዉ። ስለቀጠለዉ የኢራን ድርድር ብራስልስ የሚገኘዉ ዘጋቢችን ገበያዉ ንጉሤን አንዳንድ ነጥቦች በማንሳት ቀደም ብዬ በስልክ አነጋግሬዋለሁ።
ገበያዉ ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ