1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍጋኒስታውያን ስደተኞች በዩጋንዳ ያጫረው ስጋት

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29 2013

ታሊባንን የሸሹ የመጀመሪያው ዙር የአፍጋኒስታውያን ስደተኞች ዩጋንዳ ደርሰዋል። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመወሰዳቸው በፊትም በጊዜያዊ ስደተንነት ዩጋንዳ ይቆያሉ። ኾኖም አንዳንድ ዩጋንዳውያን የሀገራቸው የደኅንነት ጉዳይ አስግቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/3ztde
Afrika Uganda Flüchtlinge aus Afghanistan
ምስል ABUBAKER LUBOWA/REUTERS

አንዳንድ የሀገሬው ነዋሪዎች የደኅንነት ስጋት ተሰምቷቸዋል

የተወሰኑ አፍጋኒስታውያን ስደተኞች ወንዶች፤ ሴቶች እና ሕፃናት በልዩ በረራ ዩጋንዳ መግባታቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ ዐስታውቀዋል። ከዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ግን ስለስደተኞቹ ማንነት በዝርዝር የተነገረ ነገር የለም። ዩጋንዳ ውስጥ በጊዜያዊነት ይቆያሉ ከተባሉት 2,000 አፍጋኒስታውያን ስደተኞች መካከል የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች መሆናቸው ግን ታውቋል።

«የዩጋንዳ ሪፐብሊክ መንግሥት ከአፍጋኒስታን የወጡ እና በግል ልዩ አውሮፕላን የተጫኑ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የደረሱ 51 ሰዎችን ዛሬ ጠዋት ተቀብሏል» ሲል ይነበባል የዩጋንዳ ውች ጉዳይ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት የሰሞኑ መግለጫ።

ሰዎቹ ኢንቴቤ አውሮፕላን ጣቢያ የደረሱት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት «ስጋት የተጋረጠባቸው» አፍጋኒስታውያንን እና ሌሎችን መዳረሺያ ወዳሏቸው ሃገራት እስኪወስድ ድረስ በጊዜያዊነት ዩጋንዳ ተቀብላ እንድታቆያቸው በጠየቀው መሰረት ነው። ዩጋንዳ ካምፓላ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፦ «ለእነዚህ ማኅበረሰብ ለተደረገው አቀባበል እና ደግነት» ላለው ምሥጋና አቅርቧል። «የዩጋንዳ መንግሥት እና ሕዝብ ስደተኞችን እና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ማየማኅበረሰብ አካላትን ተቀብሎ የማስተናገድ የረዥም ጊዜ ልማድ አለው» ሲልም ኤምባሲው በይፋዊ የትዊተር ማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፉ ጽፏል።

ከዩጋንዳ እጅግ የምትሰፋው እና 50 ግዛቶች ያሏት አሜሪካ 2,000 ስደተኞቹን ተቀብላ በየግዛቱ 40 ሰው ለምን አላከፋፈለችም ሲሉ የጠየቁ ዩጋንዳውያንም አሉ። ዩጋንዳ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር መተባበሯ ከአልሸባብ ጥቃት ሊደርስባት ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አክለዋል።

ዩጋንዳ በአፍሪቃ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልእኮ ሶማሊያ ውስጥ ካለፉት 7 ዓመታት አንስቶ ወታደሮች ስላላት ምናልባት ከሶማሊያው አሸባሪ ቡድን አል ሸባብ ዩጋንዳ ውስጥ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን የገለጡ ነዋሪዎች አሉ። ካምፓላ ከተማ ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምሕር የሆኑት ዩጋንዳዊው የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያ ምዋምቡትስያ ንዴብሳ ስጋት ከገባቸው አንዱ ናቸው።

«የአፍጋኒስታን ስደተኞች መምጣት እንደ አል ቃኢዳ፤ አል ሻባብ እና አይሲስ ያሉ ዓለም አቀፍ ሽብርተኞችን ትኩረት ወደ ዩጋንዳ ሊስቡና ሀገሪቱንም ሊያተራምሱ ይችላሉ።»

በእርግጥም ከዛሬ 11 ዓመት በፊት ካምፓላ ከተማ ውስጥ በደረሱ መንታ ግዙፍ ፍንዳታዎች ቢያንስ 74 ሰዎች ተገድለዋል። ለሽብር ጥቃቱ በወቅቱ የሶማሊያው አል ሸባብ ኃላፊነቱን ወስዷል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ተደጋጋሚ የሽብር ሴራዎችን አምክናለች። የዩጋንዳ የቤቶች ሚንስትር ክሪስ ባሪዮሙንሲ ግን ከምንም በላይ ዩጋንዳ ስደተኞቹን የተቀበለችው በሰብአዊነት መርኅ ነው ብለዋል።

Symbolbild Kongo Flüchtlinge
ምስል Reuters/J. Akena

«እዚህ ዩጋንዳ በአሁኑ ወቅት ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች አሉን። ጥያቄው ሲቀርብልን የሰው ልጅን መርዳት ስለሚገባን ከግብረገብ አኳያ እምቢ ልንል አንችልም። እዚህ በሚቆዩባቸው ጥቂት ጊዜያት ልንደግፋቸው ይገባል። ከዚያም ወደመጨረሻ ግባቸው ያቀናሉ።»

የዩጋንዳ መንግሥት አፍጋኒስታውያን ስደተኞች ወደፊት ወደ ካናዳ አለያም ዩናይትድ ስቴትስ ይዛወራሉ ብሏል።  ዩጋንዳ ውስጥ ይቆያሉ በተባሉባቸው ሦስት ወራት ውስጥም አሜሪካ የስደተኞቹን ወጪ እየሸፈነች እንክብካቤ እንደምታደርግም ዐስታውቀዋል።

እንደ ፖለቲካል ሳይንስ ባለሞያው የአፍጋኒስታውያን ስደተኞች ዩጋንዳ መምጣት የዩጋንዳ መንግሥትን እጅግ ይጠቅማል።

«አሁን ምዕራቡ ዓለም ዩጋንዳን እንደ ስልታዊ አጋር ይመለከታታል። ዩጋንዳ የምዕራቡ ዓለምን ወይንም የዩናይትድ ስቴትስን ስልታዊ ፍላጎት ወደፊት ታገለግላለች። በሌላ ጎኑ የዩጋንዳ ፕሬዚደንት በዓለም አቀፉ መድረክ ደግ ናቸው በሚል ጥሩ ስም ያገኛሉ፤ ስለ ሰብአዊ መብቶች ከሚቀርብባቸው ነቀፌታም እፎይ ይላሉ።»

አፍጋኒስታውያንን መቀበል አነጋጋሪ ሊሆን አይገባም የሚሉ ዩጋንዳውያን ተቺዎች የዩጋንዳ መንግሥት ሌላው ቢቀር አፍጋኒስታን ካንዳሃር ግዛት ውስጥ ቀልጠው ለቀሩ ዜጎቹ ጭንቀት የሌለው አስመሳይ ነው ሲሉ ይከሳሉ። የዩጋንዳ መንግሥት በበኩሉ ስደተኞችን እና ጭንቀት ውስጥ ያሉ ሰዎችን መቀበል ብሎም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስጨናቂ የኾኑ ጉዳዮች ላይም ሚናውን በመጫወት ኃላፊነቱን መወጣት ግዴታው መሆኑን ይገልጣል።

ይሳቅ ሙጋቢ/ዪጋ ፍራንክ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ