1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ጦርነት፣ አትራፊና ከሳሪዉ

ሰኞ፣ ነሐሴ 17 2013

ብራስልስ-ዋሽተኖች ሲወቃቀሱ፣ የአፍቃኒስታን የወደፊት ጉዞ፣ የሕንዶች ክስረት፣የሩሲያዎች መሐል ሠፋሪነት፣ የቻይኖች ደስታ፣ የፓኪስታን-ኢራኖች አትራፊነት ሲተነተን የኤርዶኻንዋ ቱርክ እንደ ማዕድ ጨዉ በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆናለች።

https://p.dw.com/p/3zOQl
Afghanistan Kabul Flughafen Airbus A400M Bundeswehr
ምስል Marc Tessensohn/Bundeswehr/dpa/picture alliance

የምዕራቦች ስሕተት፣የታሊባን ድልና የአትራፊ ከሳሪዎቹ ማንነት

230821
በፅሁፍ የተሰነደ ታሪኳ እንደሚያመመለክተዉ ከክርስቶስ ልደት አምስት መቶ ዓመት በፊት ጀምሮ እንደ ግዛት ትታወቃለች።የአቼሜኒድን፣የፋርስን፣የመንጎልን ስርወመንግስታት ጠንካራ ጉልበት ስትፈታተን፣እንዳዴም ስታፈራርስ፣ ኃያል ወድቆባት፤ ለአዲስ ኃያል እንደሰገደች፣ ዘመን ሽኝታ፣ ዘመን ተቀብላለች።አፍቃኒስታን።የዓረብ-ሙስሊሞችን ክርን፣የዖስማን ቱርኮችን ጡንቻ፣የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎን ቡጢ እያነጠረች-አርግባለች።የሶቭየት ሕብረት ኮሚንስቶችን የመስፋፋት ዕቅድ አክሽፋለች።አፍቃኒስታን።በዚሕ ሁሉ ዘመን የሐገርነቷ ልዕልና፣ የዉስጥ ፖለቲካዋ እንዴትነት በዉስጧ ወይም በራስዋ ብቻ የተወሰነበት ጊዜ ጥቂት፣በጣም ትንሽ  ነዉ።ዘንድሮስ? የምዕራባዉያን የጆኦ-ስትራቴጂ ክሽፈት አብነት መሆኗ ይሆን? አብረን እንጠይቅ።
                                       
የቶራ ቦራ ገመገምን፣የናንጋርሐር ተራራን፣የኩናር ሸለቆ፣የሎጋር፣የኩንዱዝ፣የሒራት ሰርጥ፤ ጉጥ ስርጓጉጥን የሚጋየዉ የአየር-የምድር ቦምብ፣ሚሳዬል፣ መድፍ-አዳፍኔ፣ ታንክ-መትረየስ ዝም ብለዋል።ጭጭ፣ፀጥ-ረጭ።ሰላም ነዉ።
ላለፉት ሃያ ዓመታት የዚያችን ሐገር ተራራ-ሜዳ፣ ሸጥ-ሸለቆ፣ ዱር-ከተማ የሚያጋዩ፣የሚስገመግሙ፣ የሚያናፍሩበት ጄት-ሔሊኮብተር-ድሮኖች የሚነሱ-የሚያርፉበት፣ የአሜሪካ፣የብሪታንያ፣ የድፍን ምዕራብ ሐገራት ጄኔራሎች የጦር ስልት-ዕቅዳቸዉን የሚቀምሩበት የባግራም አዉሮፕላን ማረፊያ ግን ዛሬም ሠላም የለዉም።
የአሜሪካ-አዉሮጳ መግቢያ  ፍቃድ (ቪዛ) ያለዉ፣ፍቃድ የሚጠይቀዉ፣ ፍቃድ ኖረዉም-አልኖረዉ ያቺን መከረኛ ሐገር ጥሎ መሔድ የሚሻዉ፣ አዉሮፕላን ላይ መንጠላጠል የሚቃጣዉ።ሌባዉ፣ደላላዉ፣ የአየር ማረፊያ ሠራተኛዉ፣ ካገር የሚ,ጡትን የሚረዳዉ የአሜሪካና የተባባሪዎቿ ሐገራት ወታደር፣ የታሊባን ታጣቂዎች --ብዙ ነዉ ይተራመስባታል።
ሕፃናት፣ ልጆች፣እመጫቶች፣እርጉዞች፣አዛዉንቶች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ለመቅደም ይወራጡ፤ይገፉ-ይተፋፈጋሉ።ኢዛቱላሕ አንዱ ነዉ።አባቱ የአሜሪካ ኩባንዮች ዘበኛ ነበሩ።በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኘዉ ወጣት ባለፈዉ ቅዳሜ ባስተርጓሚ ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን እንደነገረዉ አዉሮፕላን ማረፊ የሔደዉ ለአባቱና ለቤተሰባቸዉ የአሜሪካ መግቢያ ፍቃድ ለመጠየቅ ነዉ።ግን አልሆነለትም።
«የተረጋገጡ ሴቶችና ሌሎች ሰዎች አይቻለሁ።እስከሬን መኪና ላይ ሲጫን አይቻለሁ።ሌላ ምርጫ የለንም።»
ከሰማይ በታች አቻ የማይገኝለትን ጦር የሚያዘዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የወትሮ ምግባሩ ከዚያ አዉሮፕላን ማረፊያ አጠገብ  የሚበሩ-የሚያርፉ ተዋጊ ጄቶች፣ ስንቅ-ትጥቅ ወታደር የጫኑ  አዉሮፕላን-ሔሊኮተሮችን ማዘዝ-ማዝመት፣ መቁጠር ነበር።አሁን ተረጋግጠዉ የሞቱ ሰዎችን ይቆጥራል።ከ20 በለጡ።
አዉሮፕላን ማረፊያዉ የሰፈሩ የኔቶ በተለይም የአሜሪካን ወታደሮች ደሕንነት የሚጠብቁት ድፍን ሃያ ዓመት ደም የተቃቧቸዉ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ናቸዉ።አጃኢብ-ይል ይሆናል አፍቃን-በፓሽቱንኛ።የኔቶ መስራችና ዋና አዛዥ የዩናይትድ ስቴትስ እርስ-በርስ እየተወዛገበች ነዉ።የአሜሪካ ጦር ከአፍቃኒስታን እንዲወጣ ያዘዙት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሚሰነዘርባቸዉን ትችት፣ወቀሳ፣ዉግዘት ለማስተባበል ይባትላሉ።
                                          
«በዚሕ ጦርነት ወቅት፣ በዉጊያዉ መሐል ከካቡል እስከ ካንዳሐር እስከ ኩናር ሸለቆ ተጉዢያለሁ።አራቴ ሔጃለሁ።ከሕዝቡ ጋር ተገናኝቻለሁ፤ከመሪዎቹ ጋር ተወያይቻለሁ።ከወታደሮቻችን ጋር ብዙ ጊዜ ተነጋግሪያለሁ።እራሴ ካየሁና ከሰማሁት አፍቃኒስታን ዉስጥ የነበረዉንና የማይቻለዉን ተረድቻለሁ።አሁን ትኩረታችን መሆን ያለበት፣ በሚቻለዉ ላይ ነዉ።»

Indien | Evakuierte Afghanen aus Kabul
ምስል IANS
Afghanistan | Flughafen Kabul | Italienischer Evakuierungsflug
ምስል Ministero Della Difesa/AFP

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የተቃዋሚዎቻቸዉ ትችት ወቀሳ ሲያይል-ባይደንን በቃላት ሸንቆጥ፣ወቀሳዉ ረገብ ሲል ደግሞ አፍቃኒስታን ዉስጥ ተገኘ የሚሉትን ድል ደመቅ፣ የብሪታያ ዜጎችን ለማስወጣት የሚደረገዉን ጥረት ገዘፍ አድርገዉ በማዉራት ይቺን መጥፎ-የወከባ ጊዜ ለማምለጥ ያዉ እንደሁሌዉ እየተዋከቡ ነዉ። 
መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ልባቸዉ እሰወስት የተከፈለ መስሏል።ባንድ በኩል 16 ዓመት የኖሩበትን የትልቅ ስልጣን ትላልቅ ሰነዶችን መሸከፉ፣ ተተኪን መደገፍ፣ማበረታታቱ ፋታ የሚሰጥ አይደለም።በሌላ በኩል ጀርመንም፣ አዉሮጳ-ዓለምም የገነቡት ክብር፣ስም ዝናን የሚያረክስ የ2015ቱን (ዘመኑ በመሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) ዓይነት  የስደተኞች ቀዉስ እንዳይገጥማቸዉ መጠንቀቅ አለባቸዉ።-ሁለት።
ሶስት አፍቃኒስታን የሆነና የሚሆነዉን መከታተል ሌሎች የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ስለአፍቃኒስታን የሚሉና የሚደረጉትን  ማጤን ግድ አለባቸዉ።
ፕሬዝደንት ማክሮን ባለፈዉ ሳምንት አዉሮጳ ከእንግዲሕ የራስዋን የፀጥታ ኃይል ማደራጀት አለበት ብለዋል።ፈረንሳይኛዉ በየትኛዉም የዲፕሎማሲ ቋንቋ ሲተረጎም በአሜሪካ መመራት-አሜሪካን መከተሉ በቃን ነዉ።
አነጋገር፣ አሠራራቸዉ አስተኳሽ እንደሌለዉ ሚሳዬል ካገኘዉ ጋር የሚላተምባቸዉ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ፖሊስ ጆሴፍ ቦሪል አሜሪካኖችን በተለይ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን በግልፅ ይወቅሳሉ።ጦሩ እንዲወጣ ለምን ወሰኑ እያሉ።ሐሙስም ደገሙት።
                                 
«ካለፈዉ ዕሁድ ጀምሮ አፍቃኒስታን ዉስጥ አዲስና አሳማሚ እዉነት እያየን ነዉ።በግልፅና በድፍረት ልናገር።ይሕ ታላቅ ድቀት ነዉ።ይሕ ለአፍቃኒስታን ሕዝብ፣ለምዕራቡ እሴትና ተዓማኒነት፣ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ለማዳባርም ትልቅ ጥፋት ነዉ።»
ባይደን ከሳቸዉ በፊት የነበሩት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የወሰኑትን ያፀደቁት ሚያዚያ ላይ ነዉ።ከሚያዚያ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ዉሳኔዉን ደግፈዉ ጦራቸዉን ያስወጡት የምዕራብ አዉሮጳ ፖለቲከኞች ችግሩ ሲፈጠር አሁን ጣታቸዉን ዋሽግተኖች ላይ መቀሰራቸዉ በርግጥ ግራ አጋቢ አጋቢ ነዉ።
በ1980ዎቹ የአፍቃኒስታን ኮሚንስቶችን ለመርዳት የዘመተዉ የሶቭየት ሕብረት ጦር በአፍቃኒስታን ሙጃሒዲያን ተሸንፎ በ1989ኝ ካቡልን ሲለቅ ያሁኑ የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ድሬዝደን-ምስራቅ ጀርመን ነበሩ።
የግዙፉ የሶቭየት ሕብረት የስለላ ድርጅት (KGB) ወጣት፣ ሁለገብ፣ ጥንቁቅ፣ ቀልጠፋ ሰላይ የነበሩት ፑቲን የሐገራቸዉ ጦር የተሸነፈዉ አሜሪካኖች፣ ከለንደን እስከ ኢስላማባድ፣ከሪያድ እስከ ቴል አቪቭ የሚገኙ ተከታዮቻቸዉን አስተባብረዉ ባሠለጠኑ፣ ባስታጠቁና ባዘመቷቸዉ ሙጃሒዲያን ድጋፍ እንደሆነ ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።
እርግጥ ነው ፑቲን አሁን በታሊባኖች ድል ባደባባይ ሊደሰቱ-ሊቦርቁ-ሊፈግጉም አይችሉም።የፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ወግም አይፈቅድም።ድሉና የምዕራቦች ዉዝግብ ግን አማርኛ ቢችሉ ኖሮ «አንጄቴ ራሰ» ማለታቸዉ አይቀርም ነበር።ካቡል የሚገኝ ኤምባሲያቸዉን አልዘጉምም።
የዚያኑ ያክል ሞስኮዎች ባንድ ወቅት ታሊባንን በ«አሸባሪነት» በመፈረጃቸዉ ምክንያት፣ፑቲን ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት፣ ከድል አድራጊዉ ቡድን ጋር የሚኖራቸዉን ግንኙነት ለመወሰን «የቀድሞ የሶቬት ሕብረት ሳተላይት የሚባሉትን ሐገራት በማስተባበሩ ጠመዝማዛ  ግን አስተማማኝ መንገድ ለመጓዝ ሳይመርጡ አልቀረም።
                                     
«በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ርዕሶች አንዱ የፀጥታ ጉዳይ ነዉ።በተለይ አፍቃኒስታን ዉስጥ ካለሁኔታ ጋር በተያያዘ ፀጥታ በጣም ትኩረት የሚሻዉ ነዉ።በመጪዉ ሰኞ በሚደረገዉ የጋራ የፀጥታ ስምምነት ድርጅት (CSTO) የቪዲዮ ጉባኤ በጋራ መቆማችንን ለማረጋገጥ እንነጋገራለን።» 
ቤጂንጎች የታሊባኖችን ድል ባይፈቅዱትም፣ የምዕራቦቹን ዉደቅት አጥብቀዉ ስለሚሹት «የአፍቃኒስታን ሕዝብ የፈቀደዉ» በሚል ቻይኒኛ በሸፋፈኑት አገላለፅ ከታሊባኖች ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።
ከቻይናም፣ከፓኪስታንም፣ ከታሊባንም ጋር ዐይንና ናጫ የሆኑት የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዶ-የታሊባኖችን ድል የኢስላማባዶች ድል አድርገዉ ስለሚቆጥሩት አኩርፈዋል-ቢያንስ ዝምታን ነዉ የመረጡት።
ፓኪስታን ራስዋ ለታሊባኖች ትሰጣለች በሚባለዉ ድጋፍ ሰበብ ያለፈዉን 20 ዓመት ያሳለፈችዉ አሜሪካኖች ሲጎሹሙ፣ ሲያስፈራሩ፣ ሲቀጡ-ሲቆጧት ነዉ።የወደፊቱን የካቡል-ኢስላማባድ-ምዕራቦችን ወዳጅነት በስልት ለመያዝ ይመስላል ታሊባን ካቡልን በተቆጣጠረበት ዕለት የፓኪስታኑ ፕሬዝደንት አሪፍ አልቪ የኔቶ አባል ከሆነችዉ ከቱርክ አቻቸዉ ከሬስፕ ጠይብ ኤርዶኻን ጋር ለመነጋገር አንካራ ነበሩ።
ቴሕራኖች ከምዕራባዉያን በተለይም ከአሜሪካኖች ጋር በገጠሙት ተዘዋዋሪ ግጭት ምክንያት የጎረቤታቸዉን የታሊባኖችን ድል ቢደሰቱበት አይደንቅም።ይሁንና አዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ደስታቸዉ በይፋ መግለጡ የሚያመጣዉን መዘዝ ለመገመት አዲስ እነታቸዉ አላሰነፋቸዉም።ራይሲ ሐገራቸዉን ከምስራቅ ስለምታዋስነዉ አፍቃኒስታን ሁኔታ-ለማማከር የመረጡት የሐገራቸዉን ሰሜን ምዕራብ ጎረቤት መሪን ነዉ።ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንን።
የጀርመንዋ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ስልጣን ከማስረከብ፣ ከምርጫ ዝግጅት ዉጣዉረዱ፣ ከጆኦ-ፖለቲካዉ ጥልፍልፍ ጋር፣ ግራ አጋቢዉን የአዉሮጳ-አሜሪካኖች ወዳጅነት ለማረቅ ከመሞከር ይልቅ ወደ ሞስኮ በረሩ አርብ።ሜርክልና ፑቲን ከአፍቃኒስታን ቀዉስና ከዩክሬን የቀደመ ትልቅ ርዕስ አልነበራቸዉም። 
ሁለቱ መሪዎች አንዳቸዉ የሌላቸዉን ቋንቋ ጠንቅቀዉ ቢያዉቁም የሚነጋገሩት ባስተርጓሚ ነበር።አስተርጓሚዉ የፑቲኒን ሩሲያኛ ለሜርክል በጀርመንኛ ሲተርጎም ግን አንድ ትንሽ ፈገግ-የሚያሰኝ አናጣቢ ጉዳይ ገባ።ስልክ።የሜርክል ተንቀሳቃሽ ስልክ ጮኸ።
                                     
«ስልክ ይጮኻል-----በተደጋጋሚ በስልክ እንገናኛለን»
ፑቲን ናቸዉ።ሜርክል የክሬምሊን ጉብኝታቸዉን እንዳጠናቀቁ ስልክ ደወሉ።ወደ አንካራ።ከፕሬዝደንት ኤርዶኻን ጋር ባደረጉት ዉይይት ከአፍቃኒስታን በኢራን፣በአዛርበጃን ምናልባትም በሌላ በኩል አድርገዉ ቱርክ የሚገቡ የአፍቃኒስታን ስደተኞችን ቱርክ ወደ አዉሮጳ እንዳትለቃቸዉ ለማግባባት ነበር።
ምዕራባዉያን መንግስታት 20 ዓመት በተዋጉት ጦርነት የጆኦ-ስትራቴጂ ስሕተት መፈፀማቸዉ ሲነገር፣ብራስልስ-ዋሽተኖች ሲወቃቀሱ፣ የአፍቃኒስታን የወደፊት ጉዞ፣ የሕንዶች ክስረት፣የሩሲያዎች መሐል ሠፋሪነት፣ የቻይኖች ደስታ፣ የፓኪስታን-ኢራኖች አትራፊነት ሲተነተን የኤርዶኻንዋ ቱርክ እንደ ማዕድ ጨዉ በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆናለች።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም አስተዳደራቸዉ ከእንግዲሕ ስለ አፍቃኒስታን ከሚከተለዉ መርሕ አብዛኛዉ በአፍቃኒስታን ጎረቤቶች በኩል ገቢር እንደሚሆን ተናግረዋል።
                                       
«የአፍቃኒስታን ሕዝብን መደገፋችንን እንቀጥላለን።ዲፕሎማሲያችንን፣ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖና ሰብአዊ ርዳታችንን እንቀጥላለን።ሁከትና አለመረጋጋትን ለመከላከል አካባቢያዊ ዲፕሎማሲና ግንኙነት ላይ ግፊት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።የአፍቃኒስታን ሕዝብ፣ሴቶችና ልጃገረዶች መሰረታዊ መብት እንዲከበር መሟገታችንን እንቀጥላለን።»
የአፍቃኒስታን አካባቢ  ግን የአሜሪካ ተባባሪዎች ኢራን፣ሩሲያ ቻይናም ሊሆኑ አይችሉም።ምናልባት ፓኪስታን፣ ሕንድ አለያም ቱርክ እንጂ።
በተፈላጊነት ሽሚያዉ፣ በከሳሪ አትራፊዉ ትንታኔዉ መሐል የዋና አትራፊዉ የታሊባን ተባባሪ መስራች ሙላሕ አብዱል ጋኒ ባራዳር ስለመንግስት ምሥረታ ለመነጋገር ካቡል ገቡ።የ53 ዓመቱ ጎልማሳ ታሪክ-የ2500 ዓመቱ የአፍቃኒስታን ታሪክ ምሕፃር ነዉ ይላሉ።«አጤሬራ» በሉት የምታዉቁ።

Afghanistan | Mullah Baradar Akhund
ምስል Social Media/REUTERS
Russland Moskau | Angela Merkel und Vladimir Putin
ምስል Sputnik/REUTERS
USA ,Präsident, Joe Biden
ምስል ZUMA Wire/imago images

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ