የአፍሪቃ ዋንጫ ዝግጅት እና ኢትዮጵያ
ዓርብ፣ ጥር 10 2005የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገር ደቡብ አፍሪቃ!? ነገ ፣ ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2005 የሚጀመረው ውድድር ፣ የ 16 አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው።
ለነገሩ፤ ውድድሩ በተረኛዋ ሊቢያ ነበረ መስተናገድ የነበረበት። ይሁንና አምና በተፈጠረው የእርስ-በርስ ጦርነትና ከዚያም በቀጠለው አለመረጋጋት ሳቢያ በሌላ ቦታ ቢዘጋጅ ይሻላል ተብሎ፣ እ ጎ አ ከ 1996 ዓ ም ወዲህ ዕድሉ ዳግመኛ ለደቡብ አፍሪቃ ሊሰጥ ችሏል።
«ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ለተሰጣት ለደቡብ አፍሪቃ ይህ ክብር ነው። ከ 2010 የዓለም ዋንጫ ወዲህ፤ የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በዚያ እንዲስተናገድ ማድረጉ ብልህነት የተንጸባረቀበት ውሳኔ ነው። አገሪቱ፤ በመሠረተ ልማቱም ሆነ ፤ የተሳካ ውድድር ማዘጋጀት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ታሟላለችና!»
Max Grünewald በደቡብ አፍሪቃ አንደኛ ምድብ ከሚገኙት የአግር ኳስ ክለቦች፣ አያክስ ካፕሽታት ቡድን አሠልጣኝ ናቸው።
ጥር 11 የመክፈቻውና ፣ እሁድ የካቲት 3,2005 ዓ ም የፍጻሜው ግጥሚያ የሚካሄደው ጆሃንስበርግ ውስጥ በ «ሳከር ሲቲ ስቴዲዬም » ነው። የድርባኑ ሞሰስ -ማብሂዳ ስቴዲየማና ሌሎችም ለግጥሚያ ተመድበዋል። በ 2012 ጋቡን በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ፣ ሳይታሰብ፤ ዛምቢያ አይቮሪኮስትን አሸንፋ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆኗ አይዘነጋም። Max Grünewald አሁንም 2 ቱ ቡድኖች ጥሩ ዕድል እንዳላቸው ያምናሉ።
«አይቮሪኮስት በኮከብ የፊት አጥቂ ድሮግባ እርዳታ እንዳለፈው ጊዜ፤ ቡድኑ በ ፍጹም ቅጣት ምት ሳይሸነፍ ፣ አሁን ውጤት ለማስመዝገብ መሰለፉ አይቀርም። ናይጀሪያን የመሳሰሉትንም በቀላሉ መገመት የሚቻል አይደለም። »
ደቡብ አፍሪቃ በምድብ ሀ ከሞሮኮ አንጎላና አስገራሚ ከተባለችው ካፑቨርድ ጋር ትጋጠማለች። ደሴቲዩ ካፑቨርድ፤ በማጣሪያ ግጥሚያ ካሜሩንን አሸንፋ ያስቀረች መሆኗ የሚዘነጋ አይደለም። ጋና በምድብ ለ ከማሊ ፣ ኒዠርና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ጋር ይሆናል ውድድሯ! የዋንጫ ባለቤት ዛምቢያ፤ በ3ኛ ምድብ ከናይጀሪያ ቡርኪና ፋሶና ኢትዮጵያ ጋር ናት። በምድብ መ አልጀሪያ ቱኒሲያ፤ አይቮሪኮስትና ቶጎ ተጋጣሚዎች ናቸው።
አንዳንድ በከፍተኛ ደረጃ የታወቁ አፍሪቃውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አገሮቻቸውን ወክለው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከመገኘት ይልቅ፣ አውሮፓ ውስጥ ለክለቦቻቸው መሰለፉን ቢመርጡም፤ ግሩዑነቫልድ እንደሚሉት፣ በዛ ያሉ ሌሎች ተጫዋቾች ብቅ-ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው።ደቡብ አፍሪቃ፤ የዓለምን ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ ካስተናገደች ወዲህ፤ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኗ ተጫዋች ዴቪድ ኒያቲ እንደሚለው፣ አሁንም መሰናዶዋ እንደገና የሠመረ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
«ይህ ፣ ለኛ ፣ ለቱሪዝም ገበያና ለእግር ኳስ አፍቃሪው ህዝብም ትልቅ ዕድል ነው። ዓለም ፣ አንዲት አዳጊ ሀገር ምን ማከናወን እንደምትችል ዓለም አቀፉን የእስፖርት ማኅበረሰብም ማስተናገድ የምትችል መሆኗን ያይላታል፣ እኛም የኩራት ስሜት ያድርብናል። »
የ 43 ዓመቱ ኒያቲ ይህ ውድድር ፣ ለክፍለ-ዓለሙ በመላ ማለፊያ ሥም እንደሚያሰጥም ተስፋውን ገልጾአል።
«ውድድሩ፤ አፍሪቃ በአስፖርት ምን እንደሚመስል ያሳያል። የተነቃቃ ዐቢይ የእስፖርት ኃይል መሆኑንም ያሥመሰክርበታል። የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ፤ አንድ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ደረጃ ሊገኝ እንደሚችልም ያለንን ተስፋ ሊያለመልም ይችላል።»
የአፍሪቃ ዋንቻ ውድድር አሸናፊ ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው የ 2013 የዓለም ኮንፈዴሬሽን ዋንጫ ውድድር በቀጥታ ያልፋል። የአግር ኳስ አፍቃሪ ቤሪ ፣ በተለይ በዚያች ሀገር እግር ኳስ ካለው እጅግ ተወዳጅነት ጋር፣ ብዙ እንግዶች እንደሚገኙ ተስፋ ያደረጋል።
«ለማንም የምሰጠው ምክር፤ በደቡብ አፍሪቃ የሚካሄደውን የእግር ር ኳስ ጨዋታ እንዲመለከት ነው። አወንታዊ ኃይልና መንፈስ ነው የሚያጎናጽፈው። በደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ ህይወት አዳሽ መሆኑንም መገንዘብ ያስችላል።»
-------------------------------------------
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ነገ-በይፋ በሚጀመረዉ ሃያ-ዘጠነኛዉ የአፍሪቃ የእግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ ላይ ለመካፈል ዛሬ ጁሐንስበርግ ይገባል።ምናልባትም ስትዲዮ ከመጣሁ በሕዋላ ገብቶም ይሆናል።ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩና ደቡብ አፍሪቃ የገቡ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ቡድኑን ለመቀበል ከማለዳዉ ጀምረዉ የጁሐንስበርጉን አዉሮፕላን ማረፊያ አጨናንቀዉት ነዉ የዋሉት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታላቁ የአፍሪቃ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሲካፈል ከሰላሳ ዓመት ወዲሕ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ-የሚሆነዉ።ዉድድሩን ለመከታተል ከፓሪስ ወደ ጁሐንስበርግ የሔደችዉ ዘጋቢያችን ሐይማኖት ጥሩነት እንዳለችዉ ታላቁን ግጥሚያ የምታስናግደዉ ደቡብ አፍሪቃ በጣሙን ጀሐንስ በርግ ግን ገና የምታንቀላፈ ነዉ-የምትመስለዉ።ሐይማኖትን ስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት በሥልክ አነጋግሬያት ነበር።
ተክሌ የኋላ
ሐይማኖት ዓለሙ
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ