1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ስደተኛና ተፈናቃዮች

ዓርብ፣ የካቲት 1 2011

ዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ለሚሰደዱ ሰዎች መሬት እየሰጠች ሰርተዉ እንዲኖሩ በማድረግ እንደ ጥሩ አብነት እየተጠቀሰች ነዉ።ይሕ ስልት ግን ዘላቂ አይደለም ባዮች ብዙ ናቸዉ።ኢትዮጵያና የኤርትራ በቅርቡ ያደረጉት የሰላም ስምምነት ግን መጨረሻዉ ካማረ የስደት-መፈናቀልን ምክንያትን ለመቀነስ  ከሁሉም እንደተሻለ አማራጭ እየተወደሰ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3D22k
Südsudan Binnenflüchtlinge in Wau
ምስል Getty Images/AFP/A. Gonzalez Farran

Kein Weg zurück für Binnenflüchtlinge - MP3-Stereo

የአፍሪቃ ሕብረት ከዚሕ ቀደም ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የጎርጎሪያኑን 2019 ለሐጉሪቱ ስደተኛ፣ተፈናቃይና ተመላሾች ችግር ትኩረት የሚሰጥበት፣ መፍትሔ የሚፈለግበትና ችግሩ የሚታሰብበት ዓመት ነዉ።የፊታችን ዕሁድ የሚሰየመዉ የሕብረቱ ጉባኤ ከሚነጋገርባቸዉ ርዕሶች አንዱ የስደተኛ፣ ተፈናቃዮችና ተመላሾች ጉዳይ ነዉ ተብሏል።የአፍሪቃ መሪዎች ብዙዎችን ሐገራት የሚነካዉን  ችግር ለማቃለል ትኩረት መስጠታቸዉ አስደሳች ቢሆንም ችግሩን ማቃለል መቻላቸዉ ግን፣ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ አጠራጣሪ ነዉ።ዚሊያ ካተሪና ፍረሕሊሽ ያጠናቀረችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ስደትና መፈናቀል  ብዙ የአፍሪቃ ሐገራትን የሚነካ፣ብዙ ሚሊዮን አፍሪቃዉያንን የሚያሰቃይ፣ ብዙ ተቋምና ድርጅቶችን የሚያሳስብ ጉዳይ ነዉ።የአፍሪቃ መሪዎች በአብዛኛዉ ራሳቸዉ ለፈጠሩትና ለሚፈጥሩት ችግር መፍትሔ ለመፈለግ መነሳታቸዉ ለችግረኞቹና ችግሩ ለሚነካ-ለሚያሳስባቸዉ ሁሉ ተስፋ ነዉ።
«አበረታች» ይላሉ ኤሮል ያይቦኬ፣የአሜሪካዉ ዓለም አቀፍ የስልታዊ ጥናት ተቋም ምክትል ኃላፊ ናቸዉ።«እኛ አሜሪካና አዉሮጳዉያን ሥለ አፍሪቃ ስደተኞች የምናዉቅና የምናሰብዉ» ቀጠሉ አጥኚዉ «በአነስተኛ ጀልቦች እየተጠለጠሉ ሐገራችን ገቡብን እያልን ነዉ።» ችግሩ ግን ዛይቦኬ እንደሚሉት ከዚሕ የከፋ ነዉ።መፍትሔዉም  በአፍሪቃዉያን እጅ-እንደ አጥኚዉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) እንደሚለዉ ባለፈዉ የጎርጎሪያኑ ዓመት 2018 ብቻ፣ 30 ሚሊዮን አፍሪቃዊ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።ከነዚሕ ዉስጥ 7,5 ሚሊዮን ስደተኛ፣ 630 ጥገኝነት ጠያቂ፣ አንድ ሚሊዮን ሐገር የለሽ፣ ግማሽ ሚሊዮን  ከስደት ተመላሽ ነዉ።የተቀረዉ ግን በየራሱ ሐገር ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ ነዉ።18 ሚሊዮን።
ከ18 ሚሊዮኑ ትልቁን ቁጥር የያዙት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዜጎች ናቸዉ።4.4 ሚሊዮን።ኮንጎዎች ስደተኛቸዉም ብዙ ነዉ።ኮንጎ ወደ ዩጋንዳ፣ሩዋንዳና ታንዛኒያ የተሰደዱ 815 ሺሕ ሕዝብ አላት።ደቡብ ሱዳን ወደ 3 ሚሊዮን፣ ሶማሊያ 2.7 ሚሊዮን፣  ናጄሪያ 2 ሚሊዮን  ተፈናቃዮች አሏቸዉ።ኤሮል ያይቦኬ የተፋናቃዮች መከራ ከስደተኞች የከፋ ነዉ ይላሉ።
                                   
«በየሐገራቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች አንድ ቀን ወደየቀያችን እንመለሳለን የሚሉት ብቻ አይደሉም።ሌላ ስፍራ ለመሔድ አቅሙም አጋጣሚዉም የሌላቸዉ ጭምር እንጂ።ብዙ ጊዜ ስደተኞች ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል ብለን እናስባለን።እንደዉነቱ ከሆነ ለብዙ ችግር የሚጋለጡት ተፈናቃዮች ናቸዉ።»
አጥኒዎቹ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች አጣዳፊ መፍትሔ መፈለግ የሚገባቸዉም ለተፈናቃዮች ነዉ።ይሁንና የስደተኞች መርሕ የተሰኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ ተቋም መስራች ወይዘሮ ካተሊን ኒዉላንድ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች ለተፈናቃዮችም ሆነ-ለስደተኞች መፍትሔ ለመስጠት ይፈልጉ ይሆናል። አቅመ ቢስ መሆናቸዉ ነዉ-እንጂ ክፋቱ።
                              
«አቅማቸዉ ዉስን ነዉ።ስለዚሕ እኔ አይሳካም የሚለዉን ሐሳብ እጋራለሁ።አባል ሐገራት ማድረግ የሚገባቸዉን እንዲያደርጉ ለማስገደድ (ሕብረቱ) መሳሪያዉ፣ሐብቱ፣አቅሙ፣ ሥልጣኑም የለዉም።»
ችግሩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ነዉ።እስከ ቅርብ አመታት ድረስ መፈናቀል በአብዛኛዉ የምስራቅና የደቡባዊ ምሥራቅ የአፍሪቃ ሐገራት ችግር ነበር።እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2007 ወዲሕ ምዕራብ አፍሪቃም ማሊ፣ናጄሪያ፣ቡርኩናፋሶ ላይ ተፈናቃዮችን በሚሊዮን መቁጠር ጀምሯል።
ዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ለሚሰደዱ ሰዎች መሬት እየሰጠች ሰርተዉ እንዲኖሩ በማድረግ እንደ ጥሩ አብነት እየተጠቀሰች ነዉ።ይሕ ስልት ግን ዘላቂ አይደለም ባዮች ብዙ ናቸዉ።ኢትዮጵያና የኤርትራ በቅርቡ ያደረጉት የሰላም ስምምነት ግን መጨረሻዉ ካማረ የስደት-መፈናቀልን ምክንያትን ለመቀነስ  ከሁሉም እንደተሻለ አማራጭ እየተወደሰ ነዉ።

Äthiopien Gedeb Binnenflüchtlinge aus West-Guji
ምስል picture-alliance/dpa/World Vision/Fitalew Bahiru
Äthiopien Gedeb Binnenflüchtlinge aus West-Guji
ምስል picture-alliance/dpa/World Vision/Fitalew Bahiru

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ