የአየር ንብረት ትንበያ ሂደት እና ጥቅሙ
ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2006ለሰብል ምርት የዝናብ ወቅትን እና ብዛትን አስቀድሞ ማወቁ በበቂ ጥንቃቄ እና ለአመርቂ የሰብል ምርት አስፈላጊነቱን ባለሞያዎች ይናገራሉ። በዓለማችን ላይ የሚከሰተዉ ከፍተኛ የአዉሎ ንፋስ እና የባህር ላይ ማዕበል እንዲሁም ሃይለኛ ዝናብ እና የከባቢ ሙቀት መጠን በቅድምያ እንዴት ነዉ የሚታወቀዉ? ቀስተ ደመናስ ምንድነዉ?
ከሳምንታት በፊት በፊሊፒንስ በሽዎች የሚቆጠር ህዝብን በአንድ ግዜ የጨረሰዉ ሃያን የተሰኘዉ አዉሎ ንፋስ፤ ፊሊፒንስ ከመድረሱ ከቀናቶች በፊት አደገኛ አዉሎንፋስ ወደ ፊሊፒንስ እየገሰገሰ መሆኑን የአየር ትንበያ ባለሞያዎች አስቀድመዉ ተናግረዋል፤ በዚህም ምክንያት ጥንቃቄ በመወሰዱ የዛኑ ያህል የበርካቶች ህይወት ተርፎአል። ግን የዚህ አይነቱ አዉሎንፋስ አደጋ፤ ከባድ ዝናብ መጣሉ፤ አልያም ፀሃያማ፤ ቀን መዋሉ በቅድምያ እንዴት ይታወቃል? በምስራቅ ጎጃም መቸከል ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አድማጫችን አቶ አማኑኤል ከተማ እባካችሁ መልሱን ጠይቁልን ባሉን መሰረት፤ በአዲስ አበባ በብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፤ በከባቢ አየር ሁኔታ ትንበያ እና ቅድምያ ማስጠንቀቅያ፤ ዳይሬክቶሪት ዳይሪክተር አቶ ደሪባ ቆርቻ እንደሚሉት፤ ዋናዉ ነገር የባህር ላይ ማዕበልም ሆነ አዉሎንፋስ የሚከሰተዉ፤ በባህር ላይ ባለዉ የአየር ግፊት እና የሙቀት ልዩነት ነዉ፤
በቅርቡ ፊሊፒንስን የመታዉ የባህር ላይ ማዕበል እና አዉሎንፋስ በሰዓት እስከ 300 ኪሎ ሜትር እየተምዘገዘገ ወደ ፊሊፒንስ እያመራ መሆኑ ነበር ቀደም ብሎ የተገለጸዉ። እንደ አየር ትንበያ ባለሞያዉ እንደ አቶ ድሪባ ቆርቻ፤ የአየር ጠባይ ቅድመ መረጃ የሰዓታት የቀናት የሳምንታት እና የወራት ሊሆን ይችላል፤
በቅርቡ በሶማሊያ ገሚስ ራስ-ገዝ መስተዳድር ፑንትላንድን በተከሰተ ኃይለኛ አዉሎ ነፋስ ወደ 300 የሚገመት ሰው መሞቱ ተገልጾአል።
አዉሎ ንፋሱና ነፋሱ ያስነሳዉ የባሕር ነዉጥ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ከብቶች መግደሉን፥ በርካታ የአሳ ማጥመጃ ጀልባዎችን ጠራርጎ መዉሰዱም ይታወቃል። በተመድ ስር የተዋቀረ በዓለማች ላይ የሚታየዉን የአየር ንብረት የሚከታተል ማዕከላዊ የመረጃ ቢሮ አለም ተብሎአል።
ይህንኑ የአየር ንብረት ተከትሎ የዘወትር አድማጫችን ቀስተ ደመና ምንድነዉ እንዴትስ ይከሰታል ሲሉ ጠይቀዉን ነበር? ቀስተ ደመና የሚፈጠረዉ ፀሐይ ጨረር እና ርጥባማ የአየር ሁኔታ ባለበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ የሚሉት አቶ ደሪባ አብራርተዉልናል። አቶ ድሪባ በከባቢ አየር መለዋወጥ ሰበብ፤በዓለም ላይ የሚታየዉን እንደ ጎርፍ አዉሎንፋስ እና የባህር ማዕበል አደጋን ለመከላከል የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርን መከላከል ይኖርብናል
ይላሉ ። አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ