1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ የንግድ ፖሊሲና አፍሪቃ

ረቡዕ፣ ኅዳር 15 2003

የአውሮፓ ሕብረት በአሕጽሮት ኤ.ሢ.ፒ. በመባል ከሚታወቁት ከአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሢፊክ አካባቢ አገሮች ጋር የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን በሚያደርገው ግፊት ዕርምጃው ሚዛን የጠበቀ አይደለም ሲሉ የሚወቅሱት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው።

https://p.dw.com/p/QH10
ምስል AP

በዚህ በጀርመንም በርካታ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ የልማት ድርጅቶች ሕብረቱ በአፍሪቃ የንግድ ፖሊሲው ላይ ተሃድሶ እንዲያደርግ ሰሞኑን አሳስበዋል። ለድርጅቶቹ ጥሪ መንስዔ የሆነው በፊታችን ሣምንት መጀመሪያ ሊቢያ-ትሪፖሊ ላይ የሚካሄደው የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ ነው። የኦክስፋም የጀርመን ቅርንጫፍና የአገሪቱ ዓብያተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅቶች ሕብረቱ የነጻ ንግድ ውል ለማስፈን ከ ኤ.ሢ.ፒ. ሃገራት ጋር የሚያካሂደው ድርድር እንደሚከሽፍ አስጠንቅቀዋል። እስካሁን የኤኮኖሚ ሽርክና ውሉን የፈረሙትም ለነገሩ ጥቂቶች ናቸው።

የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ ካራይብ ፓሢፊክ አካባቢ ሃገራት ለጋራ የነጻ ንግድ ውል መደራደር ከጀመሩ ስምንት ዓመታት ያህል ,አልፈዋል። ይሁንና በጅምሩ የታሰበው ወይም የተጠበቀው ዕርምጃ እስከዛሬ አልታየም። ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ነጻ የሆኑት የጀርመን የልማት ድርጅቶች እንደሚሉት ጥፋተኛው የአውሮፓ ሕብረት ነው። ለምን ቢባል አውሮፓውያኑ የአፍሪቃ መንግሥታት ከነርሱ ወደ አገር በሚያስገቡት ቢያንስ 80 በመቶ ዕቃ ላይ የሚጥሉትን ታክስ እንዲሰርዙና ወደ ውጭ ለሚወጣው የአፍሪቃ ጥሬ ሃብት ደግሞ ታክስ እንዲቀንሱ የሚጠይቁ መሆናቸው ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ከዚሁ በተጨማሪ በአገልግሎቱ ዘርፍም በሩ ነጻ ሆኖ እንዲከፈትለት መጋፋቱ አልቀረም። የአፍሪቃ አገሮች ድን ይህ በክፍለ-ዓለሚቱ ያልተሳፋፋ ነገር በመሆኑ በውጭ ሊጠቀሙ የሚችሉበት አይደለም። በዚህ መልክ የሚኖረው እንግዲህ የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ብቻ ነው። የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም የጀርመን ገጽ የንግድ ፖሊሲ ባለሙያ ዳቪድ ሃህፌልድ ከዚህ የተነሣና እስካሁን ከሚታየው የድርድር ስኬት-አልባነት አንጻር ፍሬ በመገኘቱ ተጠራጣሪ ናቸው። ሃህፌልድ መጪውን የትሪፖሊ ጉባዔ ሲያስቡ የሚሰጉት የአንዳንድ አገሮች የተናጠል ጉዞ እንዳይኖር ነው።

“በአንድ አካባቢ አብዛኞቹ አገሮች የአገልግሎት ዘርፉን ለውጭ መክፈት በሚቃወሙበት ጊዜ አንዳንድ የሚሹት ደግሞ መኖራቸው አይቀርም። እናም የአውሮፓ ሕብረት ከነዚሁ ከኋለኞቹ ጋር ለመቀጠል ይዘጋጃል። በኔ አመለካከት ይህ ጎጂ ነገር ነው። ስለዚህም አፍሪቃውያኑ መንግሥታት እንደማይከፋፈሉ ተሥፋ አደርጋለሁ”

በሌላ በኩል እንደ ካሜሩናዊው የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ እንደ ኦፋህ ኦባሌ ያሉ በመጪው የትሪፖሊ ጉባዔ ላይ ተሥፋ የሚጥሉ ወገኖችም አልታጡም። ካሜሩናዊው ባለሙያ የዓለም ንግድ ድርጅት በሚገኝበት በጀኔቫ ተቀማጭ ሲሆኑ ሲሆን የአፍሪቃ ሕብረት አማካሪም ሆነው ይሰራሉ። ኦባሌ በአውሮፓ ሕብረትና በአፍሪቃ መካከል ያለው የንግድ ችግር በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ ሊፈታ እንደሚገባው የሚያምኑ ሲሆን በርካታ መሪዎች የሚሳተፉበት የመጪው ሣምንት ጉባዔ ደግሞ ለዚሁ ጥሩ አጋጣሚ ነው ባይ ናቸው።

“የአፍሪቃና የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ 2015 ዓ.ም. ላስቀመጣው የሚሌኒየም ግብ በሚያበቁት ዘዴዎች ሳይነጋገሩ ድህነትንና የሕጻናት ሞትን መጠን ስለመቀነስ ወይም ይበልጥ ሕጻናት ትምሕርት ቤት ስለመሄዳቸው ማውራት መቻላቸው አዳጋች ነው። ስለዚህም በወሩ መጨረሻ ትሪፖሊ ላይ የሚካሄደው የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ ዓላማ በነጻው ንግድ ላይ በጥሞና መነጋገርና በኤኮኖሚ ሽርክና ውል ላይ የተመሰረተ ውጤት ማግኘት ይሆናል”

ኦፋህ ኦባሌ የመሪዎቹ ጉባዔ መፍትሄ ያመጣል የሚል ዕምነት ሲኖራቸው በአንጻሩ በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በጀኔቫ አገራቸውን የሚያማክሩት የሤኔጋል የንግድ ባለሙያ እንዲያጋ እምቡብ ደግሞ የሚያወሩት ስለ አዲስ የቅኝ አገዛዝ ዘይቤ ነው። አፍሪቃዊው ባለሙያ የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ላይ የሚከተለው የንግድ ፖሊሲ የክፍለ-ዓለሚቱን ድህነት ይብስ ሊያጠናክር ይችላል እስከማለትም ደርሰዋል።

“ችግሩ አፍሪቃ ጥሬ ዕቃዎችንና የዕርሻ ምርቶችን ወደ አውሮፓ በመሸጥ ብቻ ልታድግ አለመቻሏ ነው። አንድም አገር የራሱን ኢንዱስትሪ ሳይገነባ ዕርምጃ ለማድረግ አይችልም። እናም ሁሉም ነገር ባለበት ይቀጥላል። አፍሪቃ ለአውሮፓ ፋብሪካዎች ለምሳሌ ለነዳጅ ኢንዱስትሪ ምርቶች መስሪያ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ታቀርባለች ማለት ነው’”

የኦክስፋሙ የንግድ ባለሙያ ዳቪድ ሃህፌልድም የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ላይ በያዘው ስልታዊ ፖሊሲ በመጽናቱ ይበልጥ እየተገረሙ መሄዳቸው አልቀረም። ሌሎች ጥለውት እያለፉ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት።

“የአፍሪቃ አገሮች ከሕንድ፣ ከቻይና፣ ከብራዚል በሚያደርጉት ንግድ ሶሥት እጥፍ ዕድገት እያዩ ለምን ብለው ነው የአውሮፓን ሕብረት የሙጥኝ እንዳሉ የሚቀጥሉት?”

ይህ ሌ በመሠረቱ ሌሎች ብዙዎችም የሚያነሱት ጥያቄ ነው። ከዚህ አንጻር ጠንከር ባለ አነጋገር አፍሪቃ በረጅም ጊዜ ከአውሮፓ ጋር መነገዱን ልትተወው ትችላለች እስከማለት የሚድሱም አይታጡም። ይሁንና አፍሪቃውያኑ በወቅቱ ከሕብረቱ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት በተመለከተ ሌላ ስጋት ነው ያላቸው። የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ሰፊ የእርሻ ድጎማ በማድረግ የአፍሪቃን ገበሬዎች ፈተና ላይ እንደጣሉ ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል ጋና ውስጥ የዶሮ እርባታና ለገበያ የተዘጋጀ የዶሮ ምርት የማቅረቡ ተግባር በዚሁ ሚዛን ያልጠበቀ ፉክክር የተነሣ መቆሙ ግድ ነው የሆነበት።
ምክንያቱም በተጨባጭ የአውሮፓ ሕብረት ወደ ጋና የሚያስገባው ተመሳሳይ ምርት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከ 5 ሺህ ወደ 90 ሺህ ከፍ ማለቱ ነው። አፍሪቃውያኑ አምራቾች በመንግሥት ድጎማ የሚቀርበውን ምርት ርካሽነት ሊቋቋሙት አልቻሉም ማለት ነው። ወደ አፍሪቃ የሚላከው ወተትም እንዲሁ እንደ ተጨማሪ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። ይሄው እ.ጎ.አ. ከ 2005 እስከ 2008 በሶሥት ዓመታት ውስጥ ከአርባ በመቶ በላይ ነበር የጨመረው።

ሁኔታው በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘውን የድሃ-ድሃ የሆነ ሰፊ ሕዝብ ችግሩ ቀላል አያደርገውም። ድሀነትን እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በግማሽ ለመቀነስ የታለመለት የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግብም የሩቅ ሕልም እንደሆነ የሚቀጥል ነው የሚመስለው። በዓለም ገበያ ላይ የጥሬ ሃብት ዋጋ መውደቅ፣ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ቁጥብነትና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚላከው ገንዘብ በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ የማቆልቆሉ ተጽዕኖ ተደማምሮ ዛሬ የአፍሪቃን ሕዝብ እየፈተነ ነው። የቀውሱ ችግር በጅምሩ እንደታሰበው በበለጸገው ዓለም ብቻ ተወስኖ አልቀረም።
እርግጥ ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ የተፈጥሮ ጸጋ ያላቸው የአፍሪቃ ሃገራት ባለፉት ዓመታት በምርት ዋጋ ማደግ ሳቢያ ተጠቃሚዎች ሆነው ነበር። አሁን ግን በምርቱ ዋጋ መልሶ ማቆልቆልና የፊናንሱ ቀውስ በተዘዋዋሪ መልክ ባስከተለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሣ የኤኮኖሚ ዕድገታቸው እየተሰናከለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ጥር ወር አውጥቶት በነበረው የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት ሂደት ዘገባው በአፍሪቃ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት ያን ያህል የረባ ዕድገት ጨርሶ አንደማይጠበቅም መተንበዩ ይታወሣል።

አሃዙ ከ 2007 ዓ.ም. 6 ከመቶ አማካይ የዕድገት መጠን እንጻር እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን በብዙ የአፍሪቃ አገሮች በጀት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ለማሳደሩ አንድና ሁለት የለውም። የኤኮኖሚ ጠበብት በሚያስቀምጡት መስፈርት መሠረት በአፍሪቃ ዕርምጃ ታይቷል ለማለት ቢያንስ 5 ከመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያስፈልጋል። ከዚህ በታች ያለው ከሆነ ግን ድህነትን በመታገሉ ረገድ የረባ ለውጥ አይኖረውም።

ወደተነሳንበት ነጥብ እንመለስና የአውሮፓ ሕብረት ከአፍሪቃ አገሮች ጋር የነጻ ንግድ ውል ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት በአንድ ወገን ሳያጋድል ለሁለቱም ወገን እንዲጠቅም ፍትሃዊ ዘዴ መገኘቱ ግድ ነው። የአፍሪቃን ድሃ ገበሬ የፉክክር አቅም የሚያሳጣው የሕብረቱ የእርሻ ምርት የውጭ ንግድ ድጎማ ለምሳሌ መወገድ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ቀላል ነገር የሚሆን አይመስልም። የዓለምን ንግድ ፍትሃዊ ለማድረግ በሚል ለዓመታት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ከግቡ ሳይደርስ የቀረው የዶሃ ድርድር ዙር የከሽፈው በተለይም በዚሁ በድጎማ ፖሊሲ የተነሣ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ