1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረት ትንሣዔ 50ኛ ዓመት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2000

ለዛሬው የአውሮፓ ሕብረት ጽንስ የሆነው የሮማ ውል ከጸና ትናንት 50 ዓመት አለፈው። ጥር 1 ቀን. 1958 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ ዕለት ለአውሮፓ አንድነትም የአዲስ ዘመን ምዕራፍ የከፈተ ነበር።

https://p.dw.com/p/E0cV
ምስል AP

ቀደም ሲል በ 1951 በተፈረመው ውል መጽናት የአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብና የአውሮፓ የጋራ የአቶም ሕብረት ሕያው ይሆናሉ። ዛሬ ዓቢይ ዕርምጃ እያደረገ የመጣው የአውሮፓ ማሕበረሰብ ሰፊ ለሆነ ሕብረት በቅቶ የጋራ ሰንደቅ ዓላማ፣ የጋራ ምንዛሪ አለው። የሚጎል ነገር ካለ የጋራ ምንዛሪው ኤውሮ ገና ሁሉንም አለማዳረሱ፣ የጋራ ቋንቋ ባለመኖሩ የሕዝብ መዝሙር አለመጻፉ ብቻ ነው።

አውሮፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያስተሳሰረው የሮማው ታሪካዊ ውል የኤኮኖሚ አንድነት ጥርጊያ ከፋች ብቻ አልነበረም። ለሰላምና ለዕርጋታ ዘመን በር ከፋች፤ ታሪካዊ ክብደትም ያለው ነው። ጠበብት መላውን አውሮፓውያን የሚያስተሳስር ምን ነገር አለ ተብለው ሲጠየቁ በአብዛኛው እንደ መረጃ ሶሥት ታሪካዊ ነጥቦችን ያነሣሉ። እነዚሁም የግሪክና የሮማውያኑ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች፣ ሊቃውንት፣ ጠበብትና ፈላስፎቻቸው ናችው።

ወደ ሮማው ውል እንመለስና ራዕይ-ግቦቹ ዛሬም ጽናት አላቸው። የአውሮፓ ሕዝቦች የቀረበ ትስስር፣ የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ዕርምጃ፤ እንዲያም ሲል የኑሮና የሥራ ሁኔታቸው መሻሻል፣ እንዲሁም የሰላምና የነጻነት ከበሬታ ናችው። የአውሮፓው ማሕበረሰብ እንደ ድርጅት በመጀመሪያ ደረጃው የቆመው በሁለት ምሶሶዎች ላይ ነበር። በአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ምሥረታና የአቶም ሃይልን በሰላም በመጠቀሙ የኤውራቶም ውል ላይ ነበር የተመሠረተው። እርግጥ አውሮፓን የማስተሳሰሩና የማዋሃዱ ጽንሰ-ሃሣብ ረጅም ዕድሜ ያለው ጉዳይ ነው።

ገና ከ 500 ዓመታት በፊት ነበር ለምሳሌ የኔዘርላንዱ ፈላስፋ ኤራስሙስ ለአውሮፓ ሕዝብ አንድነት ጥሪ የሰነዘረው። ከዚያ በኋላም መሰሎቹ ሞንቴስክ፣ ላይብኒትስና ቪክቶር ኡጎም ለተዋሃደች አውሮፓ ቀስቅሰዋል። “እናንት ፈረንሣውያን፣ ሩሢያ፣ ኢጣሊያ፣ እንግሊዝና ጀርመን፤ በምድር ላይ ያሉት ሕዝቦቻችሁ በሙሉ መለያ ባሕርያታችውን ሳያጡ የሚዋሃዱባት ቀን ትመጣለች። እንደ ኖርማንዲይ፣ ብሬታኝ፣ ቡርጉንድ፣ ሎትሪንገንና ኤልዛስ በአጠቃላይ ሁሉም የፈረንሣይ ክፍለ-ሃገራት እንደተነሱት ሁሉ እናንተም አውሮፓዊ ወንድማማችነትን ትመሠርታላችሁ” ቪክቶር ኡጎ!

እርግጥ ኡጎ በ 1851፤ ከ 156 ዓመታት በፊት የተባበረች አውሮፓን ጥሪ ሲያደርግ በጊዜው መሳቂያና መሳለቂያ ነበር የሆነው። አውሮፓ በተለያዩት ሃገራት ብሄራዊ ስሜት የጠነከረባት ነበረች። ይህ በተለይም በጀርመንና በፈረንሣይ ጦርነት ሲከሰት የኋላ ኋላም ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች ማስከተሉ ይታወቃል። እንግዲህ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር ሰላም የሰፈነባትና የተዋሃደች አውሮፓ ራዕይ መልሶ ጭብጥ ነገር የሆነው። ብዙ ሳይቆይ የአውሮፓን ሸንጎ ምሥረታና የሞንታን ሕብረትን ተከትሎ የሮማው ውል ይፈረማል። የመጀመሪያው የፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን

ቻንስለር ኮንራድ አደንአወር በ 1951 በአገሪቱ ምክር ቤት ቡንደስታግ ውስጥ የአውሮፓን የአንድነት ራዕይ አንስተው ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት። “በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ ባለፉት ምዕተ-ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገራት ያላንዳች ግዴታ በውዴታ የሉዓላዊነታቸውን አንድ ክፍል አሳልፎ ለመስጠት፤ ይህን ሉዓላዊነት ከብሄራዊ ክልል ባሻገር ለሚፈጠር ስብስብ ለማስረከብ ዝግጁ እንደሆኑ አምናለሁ። ይህ ክቡራትና ክቡራን! በጥብቅ ለማስረገጥ እወዳለሁ፤ ለኔ እንደሚታየኝ ለብሄረተኛነት ማክተም ምክንያት የሚሆን ዓለምአቀፍ ታሪካዊ ትርጉም ያለው ሂደት ነው”

ዕርምጃው፤ አዝጋሚ ሂደቱም ቀላል አይሁን እንጂ የጥንቱ ፈላስፎችና ፖለቲከኞች ራዕይ መንፈሱን አልሳተም። የሮማው ውል በተፈረመ በ 46 ዓመቱ የአውሮፓው የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ መንግሥታት መሪዎች ኔዘርላንድ-ማስትሪሽት ላይ በመሰብሰብ በከተማይቱ ሥም የሚታወቀውን የአውሮፓን ሕብረት ምሥረታ ውል ይፈራረማሉ። ይህ ዓባል መንግሥታቱን ከነጻ ንግድና ቀረጥ ስምምነቶች ባሻገር ለፖለቲካ አንድነትም ያበቃው ውል በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው። የሕብረቱ ምሥረታ 120 ሺህ ገደማ የሚጠጉ ነዋሪዎች ያላትን ትንሽ የኔዘርላንድ ከተማም ለታሪክ አብቅቷል። እርግጥ የማስትሪሽት መመረጥ የአጋጣሚ ነበር። ውሉ በማስትሪሽት መፈረሙ ኔዘርላንድ በጊዜው የማሕበረሰቡን ርዕስነት በመያዟ ነበር።

ከማስትሪሽቱ ውል በፊት የአውሮፓ የአንድነት ጥረት አዝጋሚ ነበር። ቀስ በቀስ ተጨማሪ ሃገራት የኤኮኖሚ ማሕበረሰቡን ሲቀላቀሉ የጋራ ገበያው ራዕይም ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እየሆነ ይሄዳል። በ 1968 ዓ.ም. ውስጣዊው ቀረጥ ይወገዳል፤ በ 1979 ደግሞ የአውሮፓ የምንዛሪ ደምብ ገቢር መሆን ይጀምራል። ተከታዮቹ 80ኛዎቹ ዓመታት በዓባል መንግሥታቱ ዘንድ የኤኮኖሚ ቀውስ የተከሰተባቸው ነበሩ። የማሕበረሰቡ ዓባል መንግሥታት ከብዙ የመስፋፋት ዙሮች በኋላ ብቃት ማጣታችው አልቀረም። ሆኖም እንዲያ ሲል እያዘገመ ወደ 12 ዓባል ሃገራት የተስፋፋው ማሕበረሰብ በ 1992 በማስትሪሽት ውሎች አማካይነት ታላቅ ዕርምጃ ማድረጉ ይሳካለታል። የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ መምሕር የነበሩት ሩሜኒያዊት ማዳሊና ኢቫኒትሣ እንደሚሉት ከ 15 ዓመታት በፊት የሰፈነው የማስትሪሽት ውል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

“መንግሥታቱ በሶሥት ምሶሶዎች ላይ የቆመ ስርዓት ያሰፍናሉ። ይህም የጋራ የጸጥታና የውስጥ ፖሊሲን ይጠቀልላል። እንግዲህ የዓባል ሃገራቱ የውስጥ ፖሊሲ ጉዳዮች ወደ አውሮፓ ፖሊሲነት የተሻገሩት እንዲህ ነበር። ውሉ ሌሎች ዘርፎችም ወደ አውሮፓ ሕብረት ደረጃ ከፍ እንዲሉ አድርጓል። ለምሳሌ የተፈጥሮ ጥበቃና ማሕበራዊ ፖሊሲን የመሳሰሉትን ነገሮች። የአውሮፓውን ሕብረት ሥልጣን ከኤኮኖሚ ባሻገር ወደ ሌሎች ዘርፎች አስፋፍቷል ማለት ነው። ስለዚህም ማስትሪሽት በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ምዕራፍ ከፋች ናት ብዬ አስባለሁ”

የአውሮፓ ሕብረት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዚያው ከማስትሪሽቱ ውል በመነሣት የጋራ ምንዛሪውን ኤውሮን ሲያሰፍን የመስፋፋት ፖሊሲውንም ወደፊት በማራመድ የዓባላቱን ቁጥር ወደ 25 ከፍ ለማድረግ በቅቷል። በጋራ ምንዛሪው የሚገለገሉት ዓባል ሃገራት ቁጥር ትናንት በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ማልታንና ቆጵሮስን በመጠቅለል ወደ 15 ማደጉም ሌላው የስኬት ታሪኩ ነው። የኤውሮው ዞን ዛሬ በዓለም ላይ ታላቁ የንግድ አካባቢ ነው። በአውሮፓ ሰላምና እርጋታን አስተማማኝ በማድረጉ ዓላማ ላይ ያለመው የሕብረቱ የመስፋፋት ተግባር ወደፊትም ቀጣይነት አለው።

በሶቪየቱ ስርዓት መውደቅ ሳቢያ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ማክተም ብዙዎች የቀድሞ ሶሻሊስት አገሮች ለሕብረቱ ዓባልነት በር እንዲያንኳኩ ነበር ያደረገው። ይህ ደግሞ ታሪካዊ ግምት የሚሰጠው አስደሳች ነገር ቢሆንም በሌላ በኩል ነባሮቹን አገሮች ማሳሰቡና የሕብረቱ አቅም እስከምን? የሚል ክርክርን ማስነሣቱ አልቀረም። ይህ ዛሬም ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ይሁንና አውሮፓን በሰፊው የማስተሳሰሩ ራዕይ ጥያቄው በምን ፍጥነት እንጂ ጽናት ኖሮት ይቀጥላል። የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ኮል በ 1991 መንግሥታዊ መግለጫችው እንዲህ ነበር ያሉት።

“ክቡራትና ክቡራን፤ የአውሮፓው ማሕበረሰብ መላው አውሮፓ እንዳልሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። ስለዚህም ማሕበረሰቡ በመሠረቱ ለሌሎች አውሮፓውያን አገሮች ክፍት መሆኑ ግድ ነው። ግን ይህ ከዛሬ ወደነገ ሁሉንም መቀበል ይቻላል ማለት አይደለም። የዚያኑ ያህልም አውሮፓውያን ጎረቤቶቻችንን የማግለል ፍላጎት የለንም”

በዕውነትም የአውሮፓ ሕብረት የተገኘውን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም ፋንታ በሩን ግጥም አድርጎ አልዘጋም። በ 2004 ዓ.ም. አሥር የምሥራቅና ደቡብ አውሮፓ አገሮች ሕብረቱን ሲቀላቀሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሩሜኒያና ቡልጋሪያ ታክለው የሕብረቱን ዓባል መንግሥታት ቁጥር ከፍ አድርገውታል። የሕብረቱ የምሥራቅ ክልል ዛሬ ከጀርመን 800 ኪሎሜትር አልፎ እስከ ፖላንድ የዘለቀ ነው።

በአጠቃላይ አውሮፓ ባለፉት አምሥት አሠርተ-ዓመታት ብዙ ተራምዳለች። የጋራ ገበያ ተፈጥሯል፤ የሕብረቱ ነዋሪዎች ነጻ እንቅስቃሴና ማሕበራዊ ይዞታ ተጠናክሯል፤ በመስፋፋቱ ሂደት የሰላምና የመረጋጋቱ ዋስትናም እጅግ ነው የዳበረው። ይሁንና የዓባል ሃገራቱ ነዋሪዎች በሕብረቱ ጠቀሜታ ላይ ያላቸው ንቃተ-ህሊና ዕርምጃውን ተከትሎ አድጓል ለማለት አይቻልም። የመንግሥታቱ በተናጠል ብሄራዊ ጥቅምና ፍላጎትን የማስቀደም አስተሳሰብ ገና ጨርሶ አልተወገደም። ይህም አዘውትሮ በዓባል ሃገራቱና በብራስልስ መካከል የውዝግቦች መንስዔ ሲሆን የሚታይ ነው። ለሕዝቡ ንቃተ-ህሊና አለመዳበር የሕብረቱ ቢሮክራሲያዊና ግልጽ ያልሆነ ውስብስብ የአሠራር ዘይቤም እርግጥ የራሱ ድርሻ አለው። የሕብረቱን የፖለቲካ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር የተወጠነው የጋራ ሕገ-መንግሥት ፈረንሣይና ኔዘርላንድ ውስጥ በተካሄዱ ሕዝበ-ውሣኔዎች የከሸፉበት ዋናው ምክንያትም ይህ እንጂ ሌላ አልነበረም።
የሆነው ሆኖ ግን ይህ የእውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ዕውን የሆነበትን ከሃምሣ ዓመታት በፊት ጽናት ያገኘውን የሮማን ውል ታሪካዊነት አጠያያቂ አያደርገውም። የአውሮፓ ሕብረት ዛሬ በዓለም ላይ ታላቁ ዴሞክራሲያዊ ስብስብ ነው። ምናልባትም በሚቀጥሉት አሥርና አሥራ አምሥት ዓመታት በስተምሥራቅ እስከ ኡክራኒያ፤ በስተደቡብም እስከ ባልካን ጫፍ በመስፋፋት የሰላምና የእርጋታ ዋስትናነት አድማሱን ይበልጥ ያሰፋ ይሆናል። በነገራችን ላይ ሕብረቱ ለአሴያን አገሮች፤ ለአፍሪቃ ሕብረትም እንዲሁ አርአያ መሆኑ አልቀረም። ችግሩ አፍሪቃን በተለይ ከተመለክትን ለአውሮፓው ሕብረት ምሶሶ የሆኑት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እሴቶች ፍንጫቸው እንኳ አለመታየቱ እንጂ!