1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳው ኅብረትና የማዕከላይ ባሕር አካባቢ

ሐሙስ፣ የካቲት 25 1996

በማዕከላይ ባሕር አካባቢ የሚገኙት አራቱ ዓረባውያት ሀገሮች ዮርዳኖስ፣ ግብጽ፣ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ባለፈው ሣምንት በአጋዲር/ሞሮኮ በተፈራረሙት “አጋዲር-ስምምነት” በተሰኘው ውል ሥር የንግዱን መሰናክል ለማቃለል ዝግጁ ሆነዋል። በዚህ አኳኋን፣ እነዚሁ ሀገሮች የዘመኑ ጥሪ የሆነውን አካባቢያዊውን ትብብር በማነቃቃት፣ የራሳቸውን ንግድ-ቀጣና ይፈጥራሉ ማለት ነው። የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን የአራቱን ሀገራት የንግድ ትብብር እንቅስቃሴ ገና ከውጥኑ ጀ

https://p.dw.com/p/E0fv

��ሮ ነው በአጽንኦት ሲደግፈው የቆየው። የንግድና የውዒሎተንዋይ መሰናክል ውገዳ ነው በአውሮጳው ኅብረትና በማዕከላይ ባሕር አካባቢ ባሉት ሀገራት መካከል ለሚኖረው ስልታዊ ጥምረት አንድ ዓቢይ ከፊል የሚሆነው። ይኸው አጋዲር-ስምምነት በአውሮጳው ኅብረትና በማዕከላይ ባሕር አካባቢ መካከል እጎአ እስከ ፪ሺ፲ ድረስ አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲፈጠር የወጣው ዕቅድ የሚተገበርበትን መንገድ የሚያቃርበው ይሆናል


አራቱ ሀገሮች ዮርዳኖስ፣ ግብጽ፣ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ አጋዲር ላይ የተፈራረሙት ስምምነት አንድ-መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሰፈረበት እና በጠቅላላው ፩፻፶ ሚሊያርድ ኦይሮ የሚደርስ ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት ያለበት ጥምምር የገበያ አካባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም በዚያው አካባቢ እጅግ ለሚፈለገው ደንዳና የኤኮኖሚ ዕድገት ዓይነተኛ ንቃት የሚሰጥ ይሆናል። እንዲያውም፣ ያው የአጋዲር ስምምነት በመላው የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር አንድ ትልቅ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲፈጠር የሚደረግበትን መንገድ ለሚከታተሉት ለሌሎቹ ሀገሮች አርአያ ሆኖም ነው የሚታየው። የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን ወኪሎች እንደሚሉት፣ የአራቱ ሀገሮች ስምምነት ለዚያው ለማዕከላይ ባሕር አካባቢ ዕድገት እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍም ነው የሚቆጠረው፤ እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፲ ድረስ በመላው የማዕከላይ ባሕር ደቡባዊ አካባቢ አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲፈጠር የዚያው አካባቢ ሀገሮች ያላቸውን የጋለ ፍላጎት የአውሮጳው ኅብረት በአጽንኦት ነው የሚደግፍላቸው። የአጋዲር ስምምነት ተፈራራሚዎቹ አራቱ ሀገሮች ይኸው ትልቅ የነፃ ንግድ ቀጣና ለሚፈጠርበት ግብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነው የሚያደርጉት።

በአውሮጳና በማዕከላይ ባሕር አካባቢ መካከል አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲፈጠር ሐሳቡ የተንቀሳቀሰው፣ እጎአ በ፲፱፻፺፭ ባርሴሎና/እስጳን ውስጥ በተካሄደው የአውሮጳና የማዕከላይ ባሕር ተካባቢ ሀገሮች ጉባኤ ላይ ነበር። ከአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮች መካከል ብዙዎቹ ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምረው ከማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገሮች ጋር ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ግንኙነቶችን አጠናክረው ነው የቆዩት። ግን ከሃያ ዓመታት የሚበልጥ ጊዜ ከፈጀው ከንግዱና ከልማት ትብብሩ ግንኙነት በኋላ እጎአ በ፲፱፻፺፭ ባርሴሎና ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ አማካይነት ነው በዚያው ግንኙነት ረገድ አዲስ እርከን የተፈጠረው። በዚያው ጊዜ ነበር የአውሮጳው ኅብረት ከ፲፪ ሀገሮች ጋር የትብብር ስምምነቶችን የደረሰው። እነዚሁም፥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአውሮጳው ኅብረት ሙሉ አባላት ከሚሆኑት ቆጵሮስና ማልታ ጎን ሞሮኮ፣ አልዠሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ እሥራኤል፣ የፍልሥጥኤም ራስገዝ አካባቢ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ሦርያ እና ቱርክ ሲሆኑ፣ ሌላይቱ የማዕከላይ ባሕር ተካባቢ ሀገር ሊቢያ በታዛቢነት ደረጃ ነው በትብብሩ ስምምነት የተጣመረችው።

በባርሴሎና የተደረሰው የትብብር ስምምነት ዋና ፍሬነገር፣ በማዕከላይ ባሕር አካባቢ እ.ጎ.አ. እስከ ፪ሺ፲ ድረስ አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና መፍጠር ነው። ከዚህም በላይ፣ ስምምነቱ የማዕከላይ ባሕር ተካባቢ ሀገሮች ከአውሮጳው ኅብረት ጋር ላላቸውና ለእርስበርሳቸውም ግንኙነት ጥልቀት የሚሰጥ ይሆናል። የባርሴሎናው ስምምነት ያንኑ የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ለማልማት አንድ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሆኖ ነው የሚታየው። ይኸው ግብ ይሳካ ዘንድ፣ የአውሮጳውም ኅብረት ትብብሩን በይበልጥ ለማጠናከር ይሻል። የትብብሩ ጥንካሬ የኤኮኖሚን እርጋታና እመርታ የሚያስከትልና ለራሳቸው ለአውሮጳውያኑም ጠቀሜታን የሚያመጣ እንደሚሆን ይታመንበታል።
አራቱ የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገሮች ዮርዳኖስ፣ ግብጽ፣ ቱኒዚያና ሞሮኮ ወደፊት መላውን የንግድ መሰናክሎች ለማስወገድ አሁን ያንቀሳቀሱት ሐሳብ፣ የአውሮጳው ኅብረት ወደተለመው የነፃ ንግድ ቀጣና ግብ የሚያቃርበው ይሆናል። ለውጭ ግንኙነቶች ተጠሪ የሆኑት የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሳር ክሪስ ፓተን ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ፣ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር በትብብር ስምምነት የተጣመሩት ሌሎቹም የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገሮች የአጋዲሩ ስምምነትም አባላት እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው። እርሳቸውና ሌሎቹም የአውሮጳው ኅብረት ወኪሎች እንደሚሉት የንግዱ ቀጣና ምሥረታ ለሁሉም ነው ጠቀሜታን የሚያመጣው።

የአውሮጳው ኅብረት ወኪሎች እንደሚሉት፣ አራቱ የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገሮች የተፈራረሙት አጋዲር-ስምምነት በመካከላቸው ላለው የንግድ ግንኙነት አዲስ ማነቃቂያ ዕድል ነው የሚሰጠው፤ ግን፣ ከሁሉ ይልቅ፣ አካባቢው አውሮጳውያን ባለሐብቶች ለሚያደርጉት የውዒሎተንዋይ ተሳትፎ መስሕብ የሚሆንበት ዝንባሌ ነው የበለጠ ትርጓሜ የሚያገኘው። ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የኤኮኖሚ ግንኙነቶች ጥንካሬ በመንግሥታት መካከል ያለውንም ጠቅላላ ትሥሥር የሚያሻሽለው ነው የሚሆነው።

ከማዕከላይ ባሕር አካባቢ ጋር የተቀራረበውን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትሥሥር ለማነቃቃት የሚሻው የአውሮጳው ሕብረት፣ ከአብዛኞቹ የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገሮች ጋር ስፋት ያላቸው የትብብር ጥምረት ስምምነቶችን ነው የደመደመው። በዚሁ ጥምረት ረገድ መጨረሻ ላይ የመጣችው የማዕከላይ ባሕር አካባቢ ሀገር ሦርያ ናት። ሦርያ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር ያላት የትብብር ጥምረት የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረው የሚደረግበት ድርድር አሁንም በመካሄድ ላይ ነው። እንግዲህ፣ አራቱ የማዕከላይ ባሕር ተካባቢ ሀገሮች ግብጽ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮና ዮርዳኖስ በመካከላቸው አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና ለመፍጠር አሁን በአጋዲር የደረሱት ስምምነት የሚያስከትለው አዎንታዊው ውጤት፣ መላው ያካባቢው ሀገሮች በጋራው ጥቅም የሚቀራረቡበትን ሂደት በይበልጥ የሚያፋጥነው፣ የአውሮጳውም ኅብረት በማዕከላይ ባሕር አካባቢ አንድ የነፃ ንግድ ቀጣና የሚፈጥርበትን ግብ የሚያቃርበው ይሆናል።