የአዉሮጳ ሕብረት፥ ብሪታንያና ጀርመን
ሰኞ፣ ኅዳር 3 2005ሐገር፥ ሜርክል እንደ መሪ አዉሮጶችን አግባቢነታቸዉን አስመሰከሩ ማለት ነዉ።
የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ትናንት ለንደን ዉስጥ ባደረጉት ዉይይት የአዉሮጳ ሕብረት ሕብረት በጀትን ለመወሰን «አግባቢ» ነጥብ ላይ ድረሰዋል።ሁለቱ መሪዎች ትናንት ማታ እራት ላይ ያደረጉት ዉይይት ካበቃ በሕዋላ ከብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ፅሕፈት ቤት የወጣዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ ሕብረቱ በጀቱን በተመለከተ የአበል ሐራት ሕዝብ የሚሰጠዉን አስተያየት መቀበል አለበት በሚለዉ ሐሳብ መሪዎቹ ተስማምተዋል።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን ብሪታንያ በአዉሮጳ ሕብረት በጀት ብቻ ሳይሆን ሥለ ሕብረቱ አጠቃላይ አሰራር ከሌሎቹ አባል ሐገራት ጋር ብዙም አትግባባም።ሜርክልን ለንደን ድረስ ያጓዘዉም ብሪታንያ አቋሟን እንድታለዘብ ለማግባባት ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች ከሁለት ሳምንት በሕዋላ በሚያደርጉት ጉባኤ ሕብረታቸዉ እ.ጎ.አ.ከ2014 እስከ 2020 ባለዉ ጊዜ የሚያስፈልገዉን በትሪሊዮን የሚቆጠር በጀት ይወስናሉ። የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ግን ሕብረቱ ወጪዉን መቀነስ አለበት ባይ ናቸዉ።
የጋራዉ ማሕበር በተለይ በዚሕ የምጣኔ ሐብት ድቀት ወቅት ወጪዉን ለመቀነስ ካልፈቀደ ካሜሩን እንደዛቱት የበጀት ረቂቁን ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣናቸዉ ዉድቅ ያደርጉታል።የካሜሩን ዛቻ ብሪታንያ ወትሮም የሕብረቱን ሥራ እና አሠራር ከመደገፍ ይልቅ ማንቀፉ ነዉ-የሚቀናት እያሉ ለሚተቿት ወገኖች የተጨማሪ ትችት ምክንያት፥ለሌሎቹ የሥጋት ምንጭ ነዉ የሆነዉ።
ብራስልስ የሚገኘዉ የአዉሮጳ መርሕ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ማርኮ ኢንሰርቴ እንደሚሉት ደግሞ የካሜሩን ዛቻ ብሪታንያን ላለማጣት ብዙ የሚታገሉትን ሐይላት ልፋት መና የሚያስቀር አይነት ነዉ።
«እስከ ቀርብ ጊዜ ድረስ አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሕብረት ወዳጆች ብሪታንያ በሕብረቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆን ለማድረግ አበክረዉ ሲጥሩ ነበር።አሁን ግን ይሕ እንዳልሰራ እያዩት ነዉ»
አንጌላ ሜርክልን ትናንት ማታ ከበርሊን ለንደን አድርሶ የመለሰዉም የካሜሩን ዛቻ ነዉ።ሜርክል በቢላ፥ ሹካ፥ ማንኪያዉ ቅጭልቅልታ፥ በብርጭቆ ጠርሙሱ ግጭ-ግጭታ መሐል የእራት ጋባዣቸዉን ሐሳብ ማስቀየር አለማስቀየራቸዉ በዉል አልታወቀም።
ሕብረቱ በተለይ የአዉሮጳ ምጣኔ ሐብት በኪሳራ ቁል ቁል በሚዘቅጥበት ባሁኑ ወቅት ተጨማሪ ወጩዎቹን መቀነስ፥ የሕዝብ አስተያየትንም መቀበል አለበት በሚለዉ ሐሳብ ሁለቱም መሪዎች መስማማታቸዉን ከካሜሩን ፅሕፈት ቤት የወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል።
የካሜሩን ሐሳብ ግን የቀድሞዉ የቤልጂግ ጠቅላይ ሚንስትር ጉይ ፈርሆፍሽታት እንደሚሉት የሕብረቱ ወጪ ወይም በጀት ብቻ አይደለም።ብሪታንያ ሥለ ሕብረቱ ያላት የቆየ፥ መንታ አቋም ነፀብራቅ ነዉ።
«እንደሚመስለኝ ከብሪታንያ ጋር መሠረታዊ ችግር አለ፥ ምክንያቱም የሕብረቱ አካል መሆን ይፈልጋሉ ግን ደግሞ በየትኛዉም የሕብረቱ መርሕ አይሳተፉም።የቡድኑ አባል ሆኖ፥ የቡድኑን ግጥሚያ አለመጫወት አዳጋች ነዉ»
የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሲበዛ፥ብሪታንያ ከሕብረቱ አባልነት መዉጣት አለበት በሚሉ፥ ሲያንስ ብሪታንያ ለሕብረቱ የምትከፍለዉን መዋጮ መቀነስ አለባት የሚሉ የፓርቲያቸዉን አባላት በግባባቱና የሕብረቱን ደንቦች በማክበሩ መሐል ተቃርጠዋል።ሕብረቱ ዉጪዉን ይቀነስ የማለታቸዉ ምክንም አጣብቂኝ በመግባታቸዉ ነዉ ባዮች ብዙ ናቸዉ።
የሕብረቱ የበጀት ጉዳይ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ፋብሪሶ ፍዮሪሊ እንደሚሉት ግን ካሜሩን ያሉትን ማለታቸዉ የዲሞክራሲያዊዉ አሠራር ገፅታ በመሆኑ ሊያስወቅሳቸዉ አይገባም።
«ብሪታንያን በየትኛዉም መንገድ ቢሆን መነጠል የለብንም።በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሑሉም ሐሳቡን መግለፅ አለበት።ጉዳዩ ጥሩ አይደለም ብለዉ ካሰቡ ሃያ ሰባቱ አባል መንግሥታት ድምፅን በድምፅ መሻር ይችላሉ።ይሕ የተለመደ ነዉ።»
ከሁለት ሳምንት በሕዋላ በሚደረገዉ ጉባኤ ካሜሩን ሌሎቹን መሪዎች ከመሰሉ፥ የአዉሮጳን ምጣኔ ሐብት የምትማራዉ፥ለከሰሩት ሐገራት ከፍተኛዉን ብድርና ድጎማ የምትሰጠዉ ጀርመን እንደ ሐገር፥ ሜርክል እንደ መሪ አዉሮጶችን አግባቢነታቸዉን አስመሰከሩ ማለት ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ