1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንድ ቀን ብሔራዊ ሐዘን ታወጀ

እሑድ፣ መጋቢት 1 2011

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ዛሬ ቢሾፍቱ አቅራቢያ ተከስክሶ 157 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ቀን የሚቆይ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ለነገ አውጇል።

https://p.dw.com/p/3Ejqf
Äthiopien Mehr als 150 Tote bei Flugzeugabsturz
ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302 ቦይንግ 737 የመንገደኞች አውሮፕላን ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ-ኬንያ ሲበር ወድቆ በመከስከሱ አሳፍሯቸዉ የነበሩ፣ 149 መንገደኞች እና 8 የበረራ ሠራተኞች በሙሉ ሞቱ። አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ዛሬ ጠዋት 2 ሰአት ከ44 ደቂቃ ላይ ነው። 

አደጋው የደረሰው ቢሾፍቱ ወይም ደብረ ዘይት አቅራቢያ ሲሆን የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን በግልፅ የተነገረ ነገር የለም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአደጋው የተረፈ ሰው አለመኖሩን አረጋግጧል። አይሮፕላኑ ከ30 ሀገራት በላይ ዜግነት ያላቸው ሰዎች አሳፍሮ የነበረ ሲሆን ከሟቾቹ ውስጥ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን፣ 32 ኬንያውያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 8 አሜሪካውያን እና አምስት ጀርመናውያን ይገኙበታል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ የሟቾቹን ማንነት ለመለየት እንዲቻል የፎረንሲክ ምርመራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚያካሄድ አስታውቋል። ምርመራውን ለማካሄድም ከአየር መንገዱ ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እንደዚሁም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የተውጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጿል።

የአደጋውን መንስኤ እስካሁን ምን እንደሆነ ያልገለፀው አየር መንገዱ ምክንያቱን ለማወቅ ምርመራ ይካሄዷል ብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ከአደጋው በሁዋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አውሮፕላኑ አዲስ እንደነበር እና ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ችግር እንዳልታየበት አስታዉቀዋል።

Äthiopien Mehr als 150 Tote bei Flugzeugabsturz
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

በዛሬው አደጋ የአውሮፕላኑን አብራሪ እና ረዳት አብራሪውን ጨምሮ ስምንት ኢትዮጵያውያን የበረራ ሰራተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል። አቶ ተወልደ ስለ አብራሪው እና ረዳት አብራሪው ተከታዮን ብለዋል። «ካፒቴን ያሬድ ሙሉጌታ ይባላል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና ኬንያዊ ነው። ልምድ ያለው አብራሪ ነው። እኢአ ከ ሀምሌ 2010 ጀምሮ በጥሩ ሪከርድ ሲያገለግል የቆየ ባልደረባችን ነው። ብዙ ሰዓታት በሯል።»

 DW አደጋውን አስመልክቶ ከቦይንግ ኩባንያ በድምፅ ማብራሪያ እንዲሰጠዉ ቢጠይቅም ቦይንግ በፁሁፍ ተከታዮን አጭር መግለጫ  ልኮልናል። “ቦይንግ (ኩባንያ) በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302፣ A 737 MAX 8 አዉሮፕላን ይጓዙ የነበሩ መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች መሞታቸዉን በመስማቱ የተሰማዉን ጥልቅ ሐዘን ይገልጣል።በአዉሮፕላኑ ይጓዙ ለነበሩ መንገደኞችና ለበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦችና ተወዳጆች ከልብ የመነጨ ሐዘናችንን እንገልጣለን።የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመርዳትም ዝግጁ ነን። የቦይንግ የቴክኒክ ቡድን፣በሚቀርብለት ጥያቄና በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጉዞ ደሕንነት መመሪያ መሠረት አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነዉ።”

Äthiopien Mehr als 150 Tote bei Flugzeugabsturz
ምስል Reuters/T. Negeri


የቦይንግ ኩባንያ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው ተጨማሪ መግለጫ የቦይንግ የቴክኒክ ቡድን አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ እንደሚጓዝ አስታውቋል።
አደጋው መከሰቱን በቅድሚያ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ሲሆን ጽህፈት ቤቱ ስለ አደጋው ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይጠቅስ አደጋ ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ኃዘኑን በፁሁፍ ገልጿል።


 «የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 በረራ ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ይበር በነበረው አውሮፕላን በደረሰው  የመከስከስ አደጋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ የጠ/ሚር ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ኀዘኑን ይገልጻል::» 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አደጋው የደረሰበትን ቦታ ተገኝተው መጎብኘታቸውን የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ጀርመንን ጨምሮ የበርካታ የሀገር ባለስልጣናት በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። 

 

የአይሮፕላኑ መከስከስን አስመልክቶ አየር መንገዱ የሰጠውን መግለጫ የሚመለከት ዘገባ በድምፅ ከዚህ በታች ያገኛሉ።


ልደት አበበ

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ