1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2013

የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው እየተባለ ባለበት በዚህ ጊዜም በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ጉዳት እያስከተለ ያለው የበረሀ አንበጣ መንጋ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ አካባቢዎች መታየት መቀጠሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

https://p.dw.com/p/3kEv7
Äthiopien | Heuschrecken in der Hareri Region
ምስል Mesay Tekelu/DW

«በምሥራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋው ተጠናክሯል»

በሀረሪ ክልላዊ መስተዳደር ስር በሚገኙ ገጠር ቀበሌዎች የተከሰተ የበረሀ አንበጣ በግምት አንድ ሺህ ሄክታር በሚሆን ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።  በሌላ በኩል በ26 የገጠር ቀበሌዎቹ በተከሰተው መንጋ ጉዳት ባጋጠመው የድሬደዋ አስተዳደር በሄሊኮፕተር የታገዘ የኬሚካል ርጭት መካሄዱ ተገልጿል።  የሀረሪ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሻሜ አብዲ ለዶቼ ቬለ DW በስልክ በሰጡት መረጃ የበረሀ አንበጣ በክልሉ ባሉ የገጠር አካባቢዎች መከሰቱንና በተለይ በአምስት ቀበሌዎች አንድ ሺህ ሄክታር ግምት ባለው ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ባለሞያዎች ጉዳቱን ለመከላከል የሚረዳ የኅብረተሰብ ንቅናቄ እንዲፈጥር እየሠሩ ነው ያሉት ኃላፊው በክልሉ እና ፌደራል መንግሥት የጋራ ጥረት የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። በሌላ በኩል የድሬደዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሀ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በመስተዳድሩ 26 ቀበሌዎች የተከሰተውን የበረሀ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት መካሄዱን እና ባለፉት ቀናት በተደረገ ቅኝት አንበጣ አለመታየቱን ጠቁመዋል። የበረሀ አንበጣው በመስተዳድሩ የገጠር ቀበሌዎች ያደረሰው ጉዳት ጥናት መጠቃለሉን የጠቀሱት አቶ ኢብራሂም በቀጣይ ለችግሩ በመፍትሄነት ይሠራሉ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው እየተባለ ባለበት በዚህ ጊዜም በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ጉዳት እያስከተለ ያለው የበረሀ አንበጣ መንጋ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ አካባቢዎች መታየት መቀጠሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከድሬደዋ መሳይ ተክሉ ተጨማሪ ዘገባ ልኮልናል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ