1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ መንጋን የመከላከሉ እንቅስቃሴ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 2012

የዓለም የምግብ ድርጅት በእንግሊዝኛው ምሕፃር FAO በየጊዜው የአምበጣ መንጋ ከየት አካባቢ ተነስቶ ወደየት እያመራ እንደሆነ የሚያመላክት ትንበያውን በየጊዜው ይሰጣል። ዘንድሮም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ድርጅቱ ከየመን የተነሳ የአንበጣ መንጋ ወደ ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ግዛት መትመሙን አመልክቶ ነበር።

https://p.dw.com/p/3S9BV
Wüste Locust schwärmt in Nord- und Ost Äthiopien
ምስል Ethiopian Ministry of Agriculture

የአንበጣ መንጋን የመከላከሉ እንቅስቃሴ

ጥቂት ቆይቶ የአንበጣው መንጋ መከሰት ከአፋር እና ትግራይ አካባቢዎች ተሰማ። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ኅብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ ፀረ ሰብል የሆነውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ተደራጅቶ መውጣቱ ተሰምቷል። የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የመድኃኒት ርጭት እያካሄደ መሆኑን ተናግሯል።

የአንበጣን እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጠናቀረ የመረጃ መረብ አማካኝነት የመከታተል እና መረጃዎችንም የመዋወጥ ሂደት መኖሩን በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ ይናገራሉ። ኢትዮጵያም የዚህ መረብ አካል እንደመሆኗ በሀገሪቱም ሆነ በጎረቤት ሃገራት አካባቢ ስላለው የአንበጣ መንጋ እንቅስቃሴ መረጃዎች እንደምታሰባስብ እና እሷም እንደምታጋራም ያስረዳሉ። ከሰሞኑ በምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው ፀረ ሰብል እንቁላል ለመጣል በደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ከየመን እና ሶማሌ ላንድ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አመልክተዋል።

Wüste Locust schwärmt in Nord- und Ost Äthiopien
ምስል Ethiopian Ministry of Agriculture

እነዚህ ያደጉ እና እንቁላል ለመጣል የደረሱ አንበጣዎች በወቅቱ እንዳይራቡ የመድኃኒት ርጭት መካሄዱን የገለፁት አቶ ዘብዴዎስ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የተሰማራው የአንበጣ መንጋ ጉዳት ሳያደርስ ለማጥፋት በቅደም ተከተል ስልት ተቀምጧል ይላሉ።

በባህላዊ ስልት አንበጣውን ከየአካባቢያቸው እያባረሩ መሆናቸውን የሚገልፁት ወገኖች ከወደ አፋር አቅጣጫ የመጣውን የአንበጣ መንጋ የማኅበረሰቡ ጥረት በንፋስ ታግዞ ውኃ ወዳለቡት አቅጣጫ ገፍቶታል። ለአንበጣው መራቢያ ደግሞ እርጥብ አካባቢ ምቹ ነው። በባህላዊ ዘዴ አንበጣውን ለማባረርም ሆነ ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ላይ ባለሙያው በሰጡት ምክር፤  ደመቀዝቃዛ  ነው ያሉት አንበጣ ፀሐይ ወጥታ ካልሞቀው በቀር በገደላማ አካባቢ የመቆየት ልማድ እንዳለው ነው ያመለከቱት። ተሰብስቦ ካደረበት ሳይነሳ የማጥፋቱ ሙከራ ውጤታማ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ከአንድ አካባቢ ተባረረ ማለት ሌላ አካባቢ ጥፋት ማድረስ አይችልም ማለትም አይደለም እና በሰብል ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻል ይሆን? ሙሉውን ከድምፅ ቅንብሩ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ