1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞዉ ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም

ሰኞ፣ መጋቢት 24 2010

ገዢዉ ግንባር የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ መቶ በመቶ የምክር ቤቱን መቀመጫዎች በያዘ ማግስት ድንገት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመቻቸ ነገር እንዳልጠበቃቸው ብዙዎች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/2vN9W
Äthiopien PK Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል EBC

የቀድሞዉ ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

የደህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ምንም እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትር ስም በኃላፊነት ከፊት ቢጋፈጡም ሥልጣናቸዉ በሚፈቅድላቸዉ መጠን መሥራት አልቻሉም የሚሏቸውም ይበረክታሉ። ቀደም ሲል በምክር ቤቱ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ለነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ኃይለ ማርያም ዕድል አጋጥሞት መጠቀም ያልቻለ ዜጋ ናቸዉ።

«በኢትዮጵያ ዉስጥ የራሳቸውን አንድ አሻራ ለማስቀመጥ ጥሩ የሆነ ቦታ እና ዕድል አግኝተው የነበሩ ግን በአግባቡ ያልተጠቀሙበት «መሪ» ናቸው ብዬ ነው የማስበው። ያን ዕድል አልተጠቀሙበትም ብዬ ነው የማስበው።»

ቀድሞ በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች በሚኒስትር ደኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሠ፤ አቶ ኃይለ ማርያም በዘመናቸዉ በስልጣናቸዉ ልክ መሥራት አላስቻሏቸዉም ያሏቸዉን ምክንያቶች ይዘረዝራሉ።

«ስልጣን የሚባለው ነገር የስልጣን ምንጮቹን ማየት ነው፤ ያንቺ ግርማ ሞገስሽ የሚባለው፤ አንዱ እሱ ነው። ከግርማ ሞገስ አንፃር ኃይለ ማርያም ግርማ ሞገሥ አለው ብዬ ማለት ይከብደኛል። ሁለተኛው ይሄ በሕግ በመመሪያ የምታገኚው ነው። መንግሥታዊ ስልጣንን በመያዝ ያ ሚኒስቴር ቢሮ የተሰጠውን ነገር በመተግበር ነው። አቶ ኃይለ ማርያም ሕጋዊ ስልጣንም አለው ማለት አይቻልም። በወረቀት ተጻፈለት እንጂ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚባል ድርጅታዊ መመሪያ የሚወስናቸው ውሳኔዎች የግዴታ በቡድን ነው የሚወሰኑት።»

አቶ ኃይለ ማርያምም በአንድ ወቅት ይህንን የሚያመላክት መግለጫ ሰጥተዉ ነበር።

Äthiopien Premier Hailemariam Desalegns Rede in Parlament
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

«ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ እኔ መረጃ አለኝ ብዬ ለመናገር የሚያስችል አፍ የለኝም። ሰዎች በተናገሩት ላይ ተመስርቼ ነው እየወሰንኩ ያለሁት እንጂ።»

አቶ ኃይለ ማርያም በዘመነ ስልጣናቸዉ መንበራቸዉ የሚፈቅድላቸዉን ኃይል መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ጥላ ከሆኑባቸዉ የቀድሞ ታጋዮች ይልቅ አዲሱን ኃይል ቢያስጠጉ ይበጃቸዉ እንደነበርም አቶ ኤርሚያስ ያስረዳሉ። ይህ ሆኖ ቢሆን ቢያስን በስልጣናቸዉ ደረጃ እንደ ፀረ ሽብር ሕጉ፣ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመለከተዉን ሕግ ማስቀረት ይችሉ እንደነበርም ይከራከራሉ። የገዢዉ ግንባር መመሪያ የሆነዉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚከተለዉ ጠላት እና ወዳጅ ብሎ የመፈረጅ አካሄድም እሳቸዉ ቢፈልጉም ባይፈልጉም ሁሉንም ወገን አቅርቦ ለመንቀሳቀስ ሙሉ ለሙሉ ስልጣን እንዳልሰጣቸዉም ሳይገልፁ አላለፉም።

«እነዚህን ነገሮች ማድረግ በእርሱ ስልጣን እርከን ውስጥ ስለሆነ ቀላል ነው የሚመስለኝ። ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ጋር በተያያዘ የግሉን ኢኒሼቲቭ ወስዶ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ግልፅ ውይይት የሚያደርግበት፤ አቶ መለስ እኮ ከፊት ለፊት ይናገራል እንጂ ከጀርባ ሄዶ እኮ ከኦነግ ጋር ሲደራደር ነበር፤ ከሶማሌ ነፃ አውጪ ጋር እኮ ሲደራደር ነበር የነበረው።»

እሳቸዉ እንደተመኙት አሁን የቀድሞዉ ጠ/ሚኒስትር ለመባል የበቁት አቶ ኃይለ ማርያምን በካድሬ ስልጠናዎች ጨምሮ ከ18 ዓመታት በላይ እንደሚያዉቋቸው የሚናገሩት አቶ ኤርሚያስ አዎንታዊ ያሉትን ጎናቸዉን ሲያነሱ አንባቢነታቸዉን ያስቀድማሉ።

«አቶ ኃይለ ማርያም በጣም አንባቢ ነው እዉነቱን ለመናገር፤ በአካዳሚክ በያዘው ነገር ላይ ጥያቄ የሚነሳበት ሰው አይደለም። በተለይ በሊደር ሺፕ ትምህርት ውስጥ አብረን ተምረን ነበር በሳምንት ውስጥ ሁለት ሦስት መጽሐፍ የማንበብ እንደው ይሄ ቡኪሽ የሚባል ሰው አይነት እንደሆነ አውቃለሁ። አይቻለሁም። »

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል Getty Images/AFP/K. Desouki

ወደ ፖለቲከኛዉ ኃይለ ማርያም ሲመለከቱ ደግሞ ሁለት ሰብዕና ያላብሷቸዋል።

«ኃይለ ማርያም ሁለት ሰብዕና ነው ያለው። በአንድ በኩል በተለይ ድርጅቱ የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያመነበት ወይም ያወቀበት ሰብዕና የለውም። የሃይማኖት ገፁም ስላለ መጋጨት የፈጠረበት ነገር አንዱ ነጥብ ይመስለኛል። ሁለተኛ የሥርዓቱ ባለቤት አድርጎ ራሱን አለማየቱ ምክንያቱም አብዛኞቹ አጠገቡ ያሉት ሰዎች ከበረሃ የመጡ፣ ፓርቲዉን እንደንብረት የሚቆጥሩ ሰዎች ናቸው። የኃይለ ማርያም የሕይወት ልምድ ከአካዳሚክ ጋር የተያያዘ እንደማንኛዉም መደበኛ ኑሮ እንደኖረ ሰው ስለሆነ ወደፓርቲዉ ሊደርሺፕ ሲመጣ የበታችነት ስሜትን ነው ተሸክሞ የመጣው።»

በአቶ ኃይለማርያም ዘመነ ስልጣን ከተከሰቱት ጎላ ጎላ ያሉትን ለመጥቀስ፤ ከ20 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለርሃብ ተጋልጧል፤ በአፍሪቃ መዲናዋ አዲስ አበባም የቆሻሻ ክምር ተንዶ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል። በሁለት ክልሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በመቶ ሺህዎች የሚገመት ወገን ተፈናቅሏል። በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች የተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ አመፅ ያስከተለዉ ስጋትም ሀገሪቱን ከ10 ወራት በላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር አሰንብቷል። አቶ ኃይለ ማርያም ከስልጣን እለቃለሁ ባሉበት ንግግራቸዉ ሀገሪቱ ከባድ ችግር ዉስጥ እንዳለች እና እሳቸዉ የመፍትሄው አካል ለመሆን እንደሚሹ ተናግረዋል። አቶ ኤርሚያስ ግን መንስኤ ላልሆኑበት ችግር የመፍትሄ አካል ሊሆኑ አይችሉም ይሏቸዋል።

«በፈቃደኝነት፣ ሌጋሲዬን እንትን ለማለት፣ የችግሩ መፍትሄ ለመሆን ….. ሲጀምር አቶ ኃይለ ማርያም የችግሩ ባለቤትም አይደለም፤ የችግሩም ምንጭ አይደለም። ስለዚህ የመፍትሄዉም አካል የሚሆንበት ዕድል አይኖርም፤ አሁንም አልሆነም።»

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቆይተዋል። ስልጣን የለቀቁት ጫና ተደርጎባቸዉ ነዉ ከሚለዉ አንስቶ ከመንበራቸው ለመነሳታቸዉ የተለያዩ ግምቶች ይሰነዘራሉ። ተቺዎቻቸዉ ወትሮዉንም ስልጣን አልነበራቸዉም ባዮች ናቸዉ። አቶ ግርማ ሰይፉ በጫና ከሆነ በዘመነ ስልጣናቸዉ ያመለጣቸዉን ታሪክ የሚሰሩበት አጋጣሚ ነበር ነዉ የሚሉት።

«ጫና ተደርጎባቸው ልቀቁ ሲባሉ በቃ ጫና ተደርጎብኝ እንድለቅቅ ተደርጌያለሁ ከዚህ በፊትም እንድሰራ ያልተደረኩት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ብለው ይፋ አድርገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ሊሰሩ ይችሉ ነበር። ጫና ተደርጎባቸው ለቀቁ ፤ በፈቃዳቸው ለቀቁ በነበረባቸው አምስት ዓመት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የእሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ የሚያስችል ምንም ነገር አላደረጉም የሚለው ነው የበለጠ የሚታየው።»

Windenergie Projekt Ashegoda Mekelle
ምስል DW/Y.G. Egziabher

ከቅርብ ቤተሰቦቻቸዉ ሳይቀር መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ የሚሉት አቶ ኤርሚያስ ገዢዉን ፓርቲ እንደግል ንብረታቸዉ የሚመለከቱ አንጋፋ ፖለቲከኞች ጫና አድርገዉባቸዋል የሚለዉን ግምት ነዉ የሚያጠናክሩት። እንደእሳቸዉ ከሆነም ግፊቱ ከዓመት በላይ ዘልቋል።

«ይሄ ነገር ሲሯሯጥ የነበረው በአንድ ዓመት ውስጥ ነው። በፈቃደኝነት የለቀቀው ነገር አይደለም። እነዚህ ቅድም ያልኩሽ ነባር የኢህአዴግ ባለቤቶች ነን፤ የህወሀት ባለቤቶች ነን፤ የኦህዴድ ባለቤቶች ነን የሚሉ ሰዎች ያሳደሩበት ተፅዕኖ ከቁጥጥሩ ዉጭ ስለወጣበት የተፈጠረ አድርጌ ነው የማስበው።»

የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታይ እንዲሁም ባለትዳር እና የልጆች አባት የሆኑት በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ዉስጥ መወለዳቸዉ የሚነገረዉ አቶ ኃይለ ማርያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን በሲቪል ኢንጅነሪንግ፤ ሁለተኛዉን ደግሞ ከፊንላድ በሳኒቴሽን ኢንጂነግሪን አግኘተዋል። በዩኒቨርሲቲም በሙያቸዉ በማስተማርም ሆነ በአስተዳደር ከ10 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። በድርጅት አስተዳደርም ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ ይዘዋል። በአካዳሚክ ይዞታቸዉ ጥያቄ እንደማይነሳ የሚናገሩት አቶ ኤርሚያስ ፤ አቶ ኃይለ ማርያም ፖለቲካ ዉስጥ ባይገቡ ኖሮ ግሩም መምህር ይወጣቸዉ ነበር ብለዋቸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ