1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 21 2010

በፖለቲካዊ ቀውስ የምትናጠውን አገር ለመምራት ወደ ብሔራዊው ቤተ-መንግስት መንገድ የጀመሩት ዶክተር አብይ አሕመድ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘንድ ዋንኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል። በዚሕ ሳምንት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዷዓለም አራጌን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና በባሕር ዳር ከተሞች የታሰሩ ዜጎችን #ፍቷቸው የሚል ዘመቻም ተካሒዷል

https://p.dw.com/p/2vGCP
Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

"ንጉሰ ነገሥቱ በ6 አመቱ የሞቱት ዘመዴ 'ስሚ አንቺ እኔ እኮ 3 መንግስት አይቻለሁ' እያለ ይጎርርብኝ ነበር" ትላለች የትዊተር ተጠቃሚዋ  ሐና ጫላ። "ኢህአዴግዬ ምን ይሳነዋል በዚች እድሜዬ 3 ጠቅላይ (ሚንስትር) አሳየኝ ለዛውም ታላቁ መሪ፣ የቀድሞው ጠ/ሚ እና ለዚሕኛው ደግሞ በቅርቡ ስም እናገኝላቸዋልን" ስትል ፅፋለች። የዶክተር አብይ አሕመድ ምርጫ በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ  ከተለያዩ አቅጣጫዎች የውይይት መነሾ ሆኗል። 

የአብይ ምርጫ እና የኢሕአዴግ መንደር

በእርግጥ ዶክተር አብይ ከሶስት አመታት በላይ ለዘለቀው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ያገኙለት ይሆን? ይኸ የበርካቶች ጥያቄ ነው። ሰኞ ከአራት ኪሎው ቤተ-መንግሥት የሚገቡት የአብይ ምርጫ ለገዢው ግንባር ቅርበት ባላቸው ወገኖች ዘንድ ተፃራሪ አቀባበል ገጥሞታል። ነቀፋም አላጣውም። ፍጹም ብርሐነ "ይቻላል!! ምንም የማይቻል ነገር የለም!! ድንጋይ ወርውረህ ጠቅላይ ሚኒስትር ማስቀየርም ትችላለህ፡፡" ይላል በግል የፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ፅሁፍ።  "እንጂ በምንም አይነት መስፈርት ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ብቃታቸው አልተፈተነም፡፡ ቢያንስ አንድ ሚኒስትር መስሪያቤት (እንደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አይነት የስልጣን ደረጃ) ተፈትነው ቢያልፉ እስማማባቸው ነበር፡፡ ለማንኛውም እንደ ሾላ ዛፍ ፍሬ በድንጋይ ለወረዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም እያመሰገንኩ ለአዲሱ ጠቅላያችን መልካም የስራ ዘመን እመኛለሁ፡፡" ይላል ፍጹም።

EPRDF Logo

ስለኢትዮጵያ መንግሥት እና አገሪቱን ስለሚመራው ገዢው ግንባር በግል የፌስቡክ ገፃቸው በመፃፍ የሚታወቁት አባቡ ረሺድ "ኢሕአዲግ የመጨረሻ እድሉን እና ጥይቱን የተከበሩ ዶክተር አቢይ አህመድን በመምረጥ ተኩሷል።" የሚል እምነት አላቸው። አቶ አባቡ ኢሕአዴግ "ሌላ ምንም የቀረው ጥይትም ሆነ እድል እንደሌለው አውቆ የሕዝብ ቅቡልነትና ተኣማኒነትን ለማግኘት ጠንክሮ መስራት ይገባዋል። እንደ ኢህአዲግ ሳይሆን እንደ ሀገር የቀረን እድል ወታደራዊ መንግስት ይሆናል።በብዙ ምክንያቶች አሁን ባለን ሁኔታ ይሄ ደግሞ እንዳለ እንደቀረ እድል የሚታይ አይመስለኝም።" ብለዋል። 

አደረች አራዳ "እኔም እላለሁ፤ ሁሉም ራሱን ለለውጥ ያዘጋጅ!" የሚል ፅሁፍ አጋርተዋል። አደረች አራዳ ከሚያንጸባርቁት ሐሳብ ለኢሕአዴግ ቅርበት ያላቸው "ከዶ/ሩ ጀርባ የሚሸረብ ሴራ"ም ያሰጋቸው ይመስላል። "ሁሉም አመራር እና መዋቅር ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎን መሰለፍ ፤የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የውዴታ ግዴታ ነው መሆን ያለበት! የዶ/ር አብይ ስኬት የኢህአዴግ ስኬት ነው፡፡ የዶ/ር አብይ ውድቀት የኢህአዴግ ውድቀት ነው፡፡ ከጎን ሆኖ መጠራጠርና ያለመተማመን ስሜት ማቀጣጠል ለየትኛውም ወገን የማይጠቅም የዜሮ ድምር ጨዋታና የጥፋት መንገድ ብቻ ነው፡፡"  ሲሉ አደረች አራዳ ለገዢው ግንባር ሰዎች ጥሪ አቅርበዋል።

"ከአሁን በኋላ ከዶ/ሩ ጀርባ የሚሸርብ ሰው ዞሮ ዞሮ ስርዓቱን ጠልፎ እየጣለ መሆኑን በሚገባ ሊያውቀው ይገባል! የግለሰብ ጠላት ብቻ ሳይሆን የድርጅቱም የሃገርም ጠላት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ማንም አያተርፍም! የሚቀለድበትና የሚባክን ጊዜ ሊኖር አይገባም! ያባከናቸውን ጊዜያት ዋጋ ጭምር የምንከፍልበት እንጂ!" ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። 

የዶክተር አብይ ምርጫ ፓርቲያቸው ኦሕዴድን አብዝተው ከሚተቹ ተቃዋሚዎች ጭምር ድጋፍ አግኝቷል። ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ሲሾሙ ሊሰሯቸው ይገባል ያሏቸውን የዘረዘሩ ተንታኞች እና ተቃዋሚዎች ፈተናዎቻቸውን ግን አልዘነጉም። ቱሉ ሊባን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ በገባችባቸው ዘመናት የኦሮሞ ፖለቲከኞችን በመሾም መፍትሔ ለመሻት መጣሯን አስታውሰዋል። ቱሉ እንደሚሉት አጼ ምኒሊክ ታመው አልጋ ሲይዙ አገሪቱን የመምራት ኃላፊነቱ በተዘዋዋሪም ቢሆን የወደቀው ከፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ትከሻ ላይ ነበር። ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ከተገደሉ በኋላ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ የደርግ ሊቀ-መንበር ሆነው መሾማቸውንም ጠቅሰዋል። ደርግ ሊወድቅ ሲንገዳገድ ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ብቅ ያሉት ደግሞ ተስፋዬ ዲንቃ ነበሩ የሚሉት ቱሉ ሊበን አብይ በተለየ መንገድ ሊጓዙ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

"ዶ/ር አብይ አሕመድ በቀውስ ወቅት የማስተዳደር ኃላፊነት ከተቀበሉ ቀደምቶቻቸው በተለየ መንገድ እንዲሰሩ እንጠብቃለን። አሁን ጠቅላይ ምኒስትር እንደሚሆኑ አውቀናል። ለሁሉም ወገኖች እኩልነት ለፍትኃዊነት፣ ተመጣጣኝ ውክልና ይሰራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አሁን ያለውን ሁኔታ ለማስቀጠል ከሞከሩ ግን ትርፉ የጊዜ ብክነት ይሆናል።  ኢትዮጵያ ኦሮሞን በመግፋት እና በማግለል ረጅም ታሪኳ ልትቀጥል አትችልም" ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል። 

ተስፋዬ አበበ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ኃይለኛ ማዕበል ተነስቶ በባህር ላይ የሚቀዝፈውን መርከብ እያናወጠው ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ ሊሰምጥ የሚንገዳገደውን መርክብ ለማዳን ካፕቴን ሁነው ተመርጠዋል። ካፕቴን ዶ/ር አብይ አህመድ መርከቡን ለማዳን እድል ያላቸው ይመስላል። እድላቸውም የባህሩን ሞገድ በትክክል አዳምጠው መልስ ሲሰጡ ብቻ ነው" ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል "በተከታታይ የህዝብ ትግል እየታየ ያለው ለውጥ ጠንካራ አቅም እና ሙሉ ስልጣን ያለው አመራር ይፈልጋል!" ያሉበትን ጽሁፍ አጋረዋል። ጽሑፋቸው "ለተተኪው ጠቅላይ ሚንስትር የመልካም ምኞት መግለጫ እና አገራዊ የለውጥ ጥሪ" አዝሏል። የሐይማኖት መምሕሩ በፌስቡክ ገፃቸው ካሰፈሩት ሽንጠ ረዥም ጽሁፍ መካከል የሚከተለው ሰፍሮ ይገኛል። 

"በቅርብ አመታት ለነበሩ በይፋ ለሚታወቁ ህዝባዊ ትግሎች መነሻ ከሆኑት ውስጥ አገርን ከስልጣን ያለማስቀደም፣ የፍትህ ስርአቱ በህግ የበላይነት መርህ ብቻ አለመስራት፣ ስልጣንን ተገን አድርጎ የህዝብ ሀብትን ለግል ጥቅም ማዋል እና በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የዜጎችን የእምነት ነፃነት መንፈግ ዋነኞቹ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ምላሽ ያጡ የዜጎችን የመብት ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል ጠንካራ ካቢኔ ማቋቋም እና ለህግ ተገዥ የሆነ መዋቅራዊ አሰራር መከተል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ እናምናለን፡፡ የተጀመረው የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን የመፍታት ጅምር በማስፋት ሀሳባቸውን በመግለፃቸውና የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው የተለያዩ የወንጀል ስያሜዎች ተከሰው በመላ አገሪቱ ታስረው የሚገኙትን መፍታት፤ ንፁሀንን ለእስር የሚዳርጉ ህጎችን ማንሳት አዲሱ አመራር አዲስ ሀሳብ ያነገበ መሆኑን የሚያሳይበት የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደ ሀገር የምንገኝበትን ስር የሰደደ ድህነት የሚቀርፉና የብዙሀኑን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሪፎርሞች ሳይዘገይ ካልተጀመሩ ሁሉንም የለውጥ ሂደቶች ጠልፎ ይጥላቸዋልና ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን"

በቀለ ቢቲ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጠጠር ያለ የቤት ሥራ ለመጪው ጠቅላይ ምኒስትር ሰጥተዋል።። "ዶክተር አብይ በአቶ መለስ እና በአቶ ሐይለማርያም ያልተቋጨው የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚፈቱት ተስፋችን ላቅ ያለ ነው። በጦርነት ፈተና ለ20 አመት መኖር ከባድ ፈተና ነው"

ፍቷቸው ዘመቻ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች

Äthiopien Eskindr Nega und Andualem Arage
ምስል Serkalem Fassil

ትናንት ምሽት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ፍቷቸው የተሰኘ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ አካሒደዋል። በዘመቻው የተሳተፉት ሲያነይ አንለይ በትዊተር "ወጣትነትዋን የምትገብረው አገሬን በማለት ነው፣ ሌላ የለውም።" ሲሉ ማህሌትን ማሰር ስህተት ነው ሲሉ ተችተዋል። 

ሲያነይ የጠቀሷት ማኅሌት ፋንታሁንን ነው። ጦማሪዋ ማኅሌት ከስድስት ቀናት በፊት የታሰረችው ከነ እስክንድ ነጋ፣ አንዷለም አራጌ ፣በፍቃዱ ኃይሉ እና ተመስገን ደሳለኝ ጋር ነበር። በዘመቻው የተሳተፉት ዮናስ፦ "ወንጀላቸው ምንድነው? የኅሊና እስረኞች በእስር ቤቶች የሚገጥማቸውን ተችተው መናገራቸው ይሆን?" ሲሉ ጠይቀዋል። 

"ዶ/ር ደሳለኝ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ማዕከል (Institute of Disaster Risk Management) ዳይሬክተር ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችና የጣና ሐይቅ የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ የሚደረጋው ዘመቻ ያደርጋሉ። በአሁኑ ወቅት በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ። በአስቸኳይ ፍቷቸው" ሲሉ የፃፉት ወንዶሰን ናቸው። ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ለእስር ከተዳረጉ 18 ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ጋዜጠኞች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጭምር ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ