1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአብሮነት እሴቶቻችን እና አሳሳቢዉ የጥላቻ ንግግር

ሐሙስ፣ ኅዳር 24 2013

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚታየዉ የጥላቻ ንግግር፤ ብሎም የሃሰት መረጃ የአብሮነት እሴቶቻችንን ይበልጥ ጎድቶታል ይላሉ አብዛኞች ተጠቃሚዎች።  በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የሚታየዉ የማኅበረሰብ እሴት መሸርሸር ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ስለዚህም የሲቪክ ማኅበራት ፊታቸውን ወደ እሴት ግንባታ ሊያዞሩ ይገባል ሲሉ ዜጎች እየወተወቱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3mCFw
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

በዓለም የሚታየዉ የዘመናዊነት መጎልበትን ተከትሎ የመጣ ችግር ይሆን?

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚታየዉ የጥላቻ ንግግር፤ ብሎም የሃሰት መረጃ የአብሮነት እሴቶቻችንን ይበልጥ ጎድቶታል ይላሉ አብዛኞች ተጠቃሚዎች።  በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የሚታየዉ የማኅበረሰብ እሴት መሸርሸር ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ስለዚህም የሲቪክ ማኅበራት ፊታቸውን ወደ እሴት ግንባታ ሊያዞሩ ይገባል ሲሉ ዜጎች እየወተወቱ ነዉ። ሽማግሌዎችን፤ የሃይማኖት አባቶችን፣ ወንድም ወንድሙን፣ ታናሽ ታላቁን፣ ወገን ወገኑን ማክበር፣ መተሳሰብ፣ ሰብዓዊነት እና እርስ በርስ መደጋገፍ የመሳሰሉት ኢትዮጵያውያን የሚታወቁባቸው ወርቃማ እሴቶቻችንን እየተሸረሸረ በመሆኑ ልናስብበት ይገባል ሲሉም ያማርራሉ። የመንግሥትም ይሁን  የተለያዩ ተቋማት ሕጎች ሲወጡ በማኅበረሰባዊ እሴቶች፣ ባህሎች እና ወጎች ላይ በመመርኮዝ ቢሰሩ ይመረጣል ሲሉም ይወተዉታሉ። 

አሁን አሁን በኢትዮጵያዉያን ዘንድ እየሰፋ የመጣዉን የጥላቻ ንግግር በተመለከተ ከዓመታት በፊት ከባልደረቦቼ ጋር ስንወያይበት ስንጽፍና ስናሳስበዉ የነበረ ጉዳይ ነዉ ያለን አንጋፋዉ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ የጥላቻ ንግግሩ ከየትም የመጣ ሳይሆን ይዘነዉ ያደግነዉ በመሆናችን ነዉ ይላል። 

በሃገራችን የሚታየዉ የጥላቻ ንግግር መልክ ያጣ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶአል ያሉን በጅማ ዩንቨርስቲ በሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ሊቀመንበር እና መምህር ዶ/ር ጌታቸዉ ጥላሁን በበኩላቸዉ ነገሩን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ። ምናልባት የትምህርት ስርዓታችንን መቀየር ገብረገብን ማካተት እየሰፋ የመጣዉን የጥላቻ ዘመቻን መቅረፍ ይቻል ይሆን?

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተሳታፊ የሆኑት እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ጉዳዮችን የሚከታተሉት  የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ አቶ ነጋ ወዳጆ እንደሚሉት በዓለም ላይ የሚታየዉ ዘመናዊነትን መጎልበትን ተከትሎ የማኅበራዊ ተቋማት እሴቶቻችንን ማስጠብቀን ባለመቻላቸዉ ነዉ ።

የጥላቻ ንግግርን ለመቀረፍ መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር ሊሰራ የሚችለዉ ነገር ይኖር ይሆን ?  በኢትዮጵያዉያን ዘንድ እየሰፋ የመጣዉ ጥላቻ ንግግር የአብሮነት እሴቶቻችንን አይሸረሽርምን? መንስኤዉ ምን ይሆን ?

ወደ ጎሳ፣  እና በአፍቅሮተ ነዋይ የተለወጠዉን የመተሳሰብ፣ የሰብዓዊነት እና አንዱ ለአንዱ ደጀን የመሆን እሴቶቻችንን ዜጋዉ ሁሉ በየሞያዉ በየሚዉልበት ሁሉ ሊያስመልስ ይገባል ሲሉ የዛሬዉ ዝግጅት እንግዶች ገልፀዋል። የጥላቻ ስብዕናን የሚነካ ንግግር ሳይሆን ሃሳብን በሃሳብ መሞገት ፤ በሰላም እና በመተራረም ንግግር ቢተካ በቀላሉ የሰላሙ መንገድ ቅርብ ይሆን ነበር ብለዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ