የአሸባብ ጥቃትና የኬንያ የአፀፋ እርምጃ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1 2007የኬንያ አየር ኃይል ባለፈው ሰኞ በሶማሊያ የአየር ድብደባ ያካሄደ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የኬንያ መንግሥት ለሶማሊያ ጠቃሚ የሆኑ የገንዘብ ማስተላለፊያ ድርጅቶችን አግዷል ።ስለ ሰኞው የአየር ድብደባ ና የገንዘብ አአስተላላፊ ድርጅቶች መታገዳቸው በሶማሊያውያን ላይ ስለ ሚያሳድረው ተፅእኖ በመቅዲሾ የዶቼቬለ ተባባሪ ዘጋቢን አነጋግራ ኂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች ።
ካለፈው ሐሙሱ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ በጥቃት አድራሹ በአሸባብ ላይ መንግሥታቸው ከባድ የአፀፋ ጥቃት እንደሚፈፅም ካሳወቁ ወዲህ የኬንያ መንግሥት የተለያዩ የአፀፋ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው ። የኬንያ የአየር ኃይል ባለፈው ሰኞ በሶማሊያ የአየር ድብደባ አካሂዷል ። በማግስቱ ማክሰኞ በኬንያው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቋል ። ዛሬ ደግሞ የሶማሊያ የሃዋላ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን አግዷል ። ከዚህ ሌላ ኬንያ በሶማሊያ ተጨማሪ የአየር ጥቃቶች አካሂዳለች ሲሉ አንዳንድ የዜና ምንጮች ቢናገሩም በሶማሊያ የዶቼቬለ ዘጋቢ መሀመድ ዑመር ሁሴን ግን ከሰኞ ወዲህ የተካሄደ የአየር ድብደባ የለም ይላል ።
« የአየር ጥቃቱ የተካሄደው ለአንድ ቀን ብቻ ነው። ይኽውም ከ3 ቀናት በፊት ነበር ይህም በኬንያ መንግሥት የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው ። ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ባለፈው ሐሙስ ኬንያ ውስጥ ለደረሰው የሽብር ጥቃት ከባድ አፀፋ ጥቃት እንደሚፈፀም አስታውቀው ነበር ። ፕሬዝዳንቱ ያሉት በተግባር ተፈፅሟል ። »
በሰኞ የአየር ጥቃት የኬንያ መንግሥት የደፈጣ ተዋጊውን የአሸባብን ጠንካራ ይዞታ ማጥቃቱን ነው የገለፀው ።ሆኖም መሀመድ እንደተናገረው በጥቃቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎችም መገደላቸውን ከአካባቢው ምንጮች ሰምቷል ።
«የአየር ድብደባው የተካሄደው በሶማሊያና በኬንያ ድንበር ላይ ጌዶ በሚባል አካባቢ ነው ። የኬንያ መንግሥት በዚሁ ስፍራ የአሸባብን ተዋጊዎች ጠንካራ ይዞታ መደብደቡን አሰታውቋል ። ሆኖም ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ግን ሰላማዊ ሰዎችም ላይ ጉዳት መድረሱን ያሳያሉ ። በርግጥ በጥቃቱ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ግን ማወቅ አልቻልንም ።»
148 ተማሪዎች በተገደሉበት የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ፣ ጥቃቱ በተፈፀመበት እለት የኬንያ መንግሥት ልዩ ኃይል ፈጥኖ መድረስ አለመቻሉ መንግሥትን ክፉኛ እያስተቸው ነው ። ባለፈው ማክሰኞ ናይሮቢ ውስጭ ሟቾቹን ለማሰብ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች የመንግሥት ወታደሮችን ያኔ የት ነበራችሁ ሲሉ ጠይቀው ነበር ። ያለፈው ሳምንቱ የኬንያው የአሸባብ ጥቃት ከዚህ ቀደም ስለ ቡድኑ መዳከም ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶችን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ። ተባባሪ ዘጋቢ መሀመድ በበኩሉ የቡድኑን መዳከም የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳሉ ሁሉ ያለ መዳከሙም መገለጫዎች አሉ ይላል ።
«አዎ አሸባብ ተዳክሟል ። በሌላ በኩል ደግሞ አልተዳከመም ። ይህን የምልበት ምክንያት አሸባብ ከዋና ዋናዎቹ የሶማሊያ ከተሞች እንዲወጣ ተደርጓል ። ያም ሆኖ አሁንም ራቅ ብለው በሚገኙት የሶማሊያ አካባቢዎች ግን ግን በትጋት ይንቀሳቀሳል ። አሁንም ቢሆን በሶማሊያም ሆነ በጎረቤት አገሮች ከባድ ጉዳቶች ማድረስ ይችላል ። »
የሐሙስ ጥቃት ካስከተለው መዘዝ አንዱ ኬንያ የሚገኙ የሐዋላ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች መታገድ ነው ። የኬንያ መንግሥት ዛሬ እንዳስታወቀው ለሶማሊያ ጠቃሚ የሚባሉ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን አግዷል ። ይህም ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ ህይወታቸው ለተመሰረተው በርካታ ሶማሊያውያን ከባድ ጉዳት መሆኑ ግልጽ ነው ።መሀመድ እንደሚለው ግን እርምጃው የሚጎዳው ሶማሊያውያንን ብቻ አይደለም ።
«የነዚህ የሐዋላ ድርጅቶች ተገልጋዮች ሶማሌዎች ብቻ አይደሉም ። ኢትዮጵያውያንና ሱዳኖችና የረብ ሃገራት ዜጎችም ናቸው ። ሃዋላው ለበርካታ አፍሪቃውያን በጣም ጠቃሚ ነው ። በነርሱም ላይ ተፅእኖ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ በፍጥነትና በቀላሉ ገንዘብ የሚልኩበትና የሚቀበሉበት መንገድ ነበር ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሃዋላ አገልግሎት ከሚሰጡ ሌሎች ተቋማት ገንዘብ ማግኘቱ ውስብስብ ነው የሚሆነው እናም ያለ አንዳች መጠራጠር ይጎዳቸዋል ።»
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ