1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አድበስብሷል ተብሏል

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት ዘገባውን አቅርቧል፡፡ የቦርዱ ኃላፊዎች በጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ታይተው እንደነበር ቢያምኑም አጠቃላይ አያያዙን “ውጤታማ” ብለውታል፡፡ ታሳሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በቦርዱ ግምገማ ላይ የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2aGes
Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

Inquiry Board deliver its report to Parliament - MP3-Stereo

ሰባት አባላት ያሉበት የአስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በይፋ ሥራውን የጀመረው ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊ አለመሆናቸውን የመቆጣጠርና የመከታተል ስልጣን በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት የቦርዱ አባላት በሦስት ክልሎች እና በአዲስ አበባ በነበሩ ሕዝባዊ አመጾች ተሳትፈዋል የተባሉ 26ሺህ ገደማ ተጠርጣሪዎች የታሠሩባቸውን ማዕከላት ሲጎበኙ ቆይተዋል፡፡ 

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ ትላንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁን አፈጻጸም አስመልክቶ ባቀረቡት ዘገባ ላይም በማዕከሎቹ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጠቃቅሰዋል፡፡ በአዋሽ ሰባት፣ አላጌና ዲባ ባሉ ማቆያዎች “በምርመራ ወቅት የተወሰኑ ፖሊሶች በማስፈራራትና በማስገደድ የእምነት ቃል እንዲሰጥ ያደርጉ ነበር” ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በመጀመሪያዎቹ ወራት የታዩ እንደነበርና በስተኋላ ላይ መስተካከላቸውን ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

አቶ ታደሰ አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አያያዙን እንዲህ ገምግመውታል፡፡  

“በመንግስት በኩል በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዜጎች ሰብዓዊ መብትን ለመጠበቅ እና ሰላምን ለማረጋገጥ የተሠራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ቦርዱ ለመመልከት ችሏል፡፡”

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ አጥኚ አቶ ፍስሀ ተክሌ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በውሱን ቦታዎች ላይ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ የተከናወነ አይደለም ባይ ናቸው፡፡

“የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተለይ ይፈጸም የማሰቃይ ተግባር አልፎ አልፎ ብቻ የታየ ነገር አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ቦታዎች ላይ ታይቷል፡፡ ብዙም የተዘገበ ነገር ነው፡፡ አንድ ሁለት ብቻ የምንላቸው አይደሉም፡፡ አሁን በተለይ መረጃ ያለን የአዋሽ ሰባት፣ የብላቴ እና የብር ሸለቆን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እኛ ባለን መረጃ መሠረት በጣም በብዙ መልኩ ነበር የሚፈጸመው፡፡ የነበረው ማሰቃየት እና ከሰብዓዊ አያያዝ ውጭ የነበረው ነገር ብዙ ነበር፡፡ በተደራጀ ሁኔታ (ሲስተሚክ) ነበር፡፡ ስለዚህ እንደዚህ በቀላሉ ተደበስብሶ መታለፍ የነበረበት ሳይሆን እንደ ትልቅ ችግር መታየት የነበረበት ነው።”

የአቶ ፍስሀን አባባል በጦላይ ወታደራዊ ካምፕ በእስር የቆየው ስዩም ተሾመ ያጠናክራል፡፡ በአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነው ስዩም መንግሥትን የሚተቹ ጽሑፎችን በመጦመር ይታወቃል፡፡ ለ56 ቀናት በጦላይ በታሰረበት ወቅት የደረሰበትን እና በሌሎች እስረኞች ላይ ሲፈጸም የተመለከተውን ይዘረዝራል፡፡ 

“ጦላይ ውስጥ መጀመሪያ ዙር እኛ እንደገባን ወደ 5‚600 አካባቢ ሰው ነበር፡፡ የኮማንድ ፖስት መዋቅሩ እዚያ ምርመራ ሲያካሂድ የነበረው ምናልባት ያንን አምስት ሺህ ሰው ከ10 እስከ 15 ቀን ውስጥ ነው የጨረሱት፡፡ የምርመራ ሂደቱ በአጠቃላይ በስቃይ ነበር፡፡ በዱላ፣ በግርፍ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ ነበር ሲካሄድ የነበረው፡፡ እኔ ራሴ ለሁለት ሰዓት ያህል ነው የተገረፍኩት፡፡ ሶስት ጊዜ ነው ራሴን የሳትኩት፡፡ በጣም አሰቃቂ ነው፡፡ ሽጉጥ ተደቅኖብህ እስክትናገር እስከመገደድ የደረስኩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡”  

ከቦርዱ አባላት ውስጥ ጦላይን የጎበኙ እንዳሉ እና የተመረጡ 500 ገደማ ታሳሪዎች ያቀረቧቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማድመጣቸውን ስዩም ያስታውሳል፡፡ በእስረኞች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ከተባሉ ግለሰቦች ውስጥ ከፊሉ “ለህግ እንዲቀርቡ” መደረጋቸውን ሌሎቹ “አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶ ከደረጃቸው መውረዳቸውን” ቀሪዎቹ ደግሞ “ከስራ እንዲወጡ” እንደተደረገ አቶ ታደሰ ለምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡ ዝርዝሩን ከማቅረብ ግን ተቆጥበዋል፡፡ 

የአምነስቲው አቶ ፍስሀ በደፈናው ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብሎ ከመግለጽ በላይ መደረግ ነበረባቸው የሚሉትን እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

“አሁን እንግዲህ አነዚህ ሰዎች ማሰቃየት ድርጊት ፈጸሙ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ውጭ ሰዎችን መረመሩ የሚለው ነገር ካለ ይሄ መታየት ያለበት በምስጢር አይደለም፡፡ በይፋ ነው መታየት ያለበት፡፡ እርምጃ ተወስዷል የሚለው በቂ ምላሽ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የማሰቃየት እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ማካሄድ ራሱ ወንጀል ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ በማሰቃየት መረጃ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ወይም ደግሞ ሰዎች ላይ ማስረጃ እንዲሆኑ ማስገደድ የሚል አንቀጽ አለ፡፡ እነዚያ ሰዎች በዚህ መታየት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ስንል ሕግ የሚሰራው ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመንግሕት አካላትም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያላቸውን የመንግሥትን ኃላፊነት ተጠቅመው የሰዎችን መብት ከረገጡ የሕግ የበላይነት ባለበት ሀገር ላይ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡”  

የቦርዱን ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋን ለማነጋገር በቢሮ እና በእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ሊገኙልን አልቻሉም ። 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ