1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን የስለላ ቅሌት በጀርመን

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1 2006

አንድ የጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት ባልደረባ ለአሜሪካጠቃሚ መረጃ በመስጠት ንም በመሰለል መጠርጠሩ የጀርመንን መንግሥትና ህዝብ አስቆጥቷል ። የጀርመን መንግሥት የስለላው እውነትነት ከተረጋገጠ ሃገሪቱ በአሜሪካን ላይ ያላትን እምነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አስጠንቅቋል ።

https://p.dw.com/p/1CYM8
Symbolbild BND und NSA Spionageaffäre
ምስል imago

የ 31 ዓመት ወጣት ነው ። ማንነቱ ያልተገለፀው ይህ የጀርመን ፌደራል መንግሥት የስለላ መሥሪያ ቤት በምህፃሩ BND ባልደረባ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለአሜሪካን መንግሥትም በመሰለል ተጠርጥሮ ባለፈው ሳምንት ተይዟል ። ተጠርጣሪው ማንነቱ ላልተገለፀ የአሜሪካን የስለላ ድርጅት 218 ሰነዶችን በ 25ሺህዩሮ ወይንም በ33 ሺህ ዶላር ሸጧል ተብሏል ። ዘገባዎች እንዳመለከቱት ከሆነ ትዕዛዝ ሲቀበል የቆየው በቀጥታ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ከሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ነበር ። ጀርመናዊው የስለላ ጉዳዮች አዋቂ ኤሪሽ ሽሚት ኤንቡም አሜሪካን ይህን መሰሉን ድርጊት ቀደም ባሉት ዓመታትም ስትፈፅም ቆይታለች ይላሉ ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት የአሁኑን የስለላ ቅሌት ግን የሚስተካከል የለም ።

«አሜሪካውያን የጀርመንን ፖለቲካ የጦር ኃይል እና ህብረተሰብ ሁሌም ይሰልላሉ ። ሆኖም አነዚህ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው አያውቁም እንዲሁ በቀላሉ ይታለፋሉ ። የጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለአሜሪካን የስለላ ድርጅትመረጃ አሳልፈው የሰጡባቸው ጊዜያትም ነበሩ ። ሆኖም እንዲህ ያለ የጀርመን የስለላ ድርጅት ሠራተኛ በህገ መንግሥታዊ አካል ላይ ለአሜሪካውያን የሰለለበት ከባድ ጉዳይ ደርሶ አያውቅም ። »

ጀርመን ውስጥ በጀርመን የስለላ ድርጅት ባልደረባ በአሜሪካን ባለሥልጣናት ትዕዛዝ በጀርመን ህገ መንግስታዊ ተቋም ላይ ተፈፀመ የተባለው ይህ ከባድ ስለላ (ወንጀል) በጀርመን መንግሥትም በተቃዋሚዎችም ተወግዟል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናንት ቻይና ውስጥ በሰጡት መግለጫ ድርጊቱ ተፈፅሞ ከሆነ ሁለቱ ሃገሮች በመተማመን ከሚካሂዱት ተግባር ጋር የሚጋጭ ነው ብለዋል ።

Symbolbild Angela Merkel Barack Obama NSA Affäre
ምስል picture-alliance/dpa

«የተሰነዘሩት ወቀሳ እውነት ከሆኑ እንደኔ ግንዛቤ በአገልግሎት ና በአጋርነት በሙሉ መተማመን የሚደረግን ትብብርን የሚቃረን ሥራ ነው »

ወሬው እንደተሰማ ከጀርመኑ የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ CDU ጋር ተጣምሮ ሥልጣን የያዘው የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ቶማስ ኦፐርማን ድርጊቱ ምንም ዓይነት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ሲሉ ነበር ቁጣቸውን የገለፁት ።

« ስለላዎቹ እውነት መሆናቸው ከተረጋገጠ በምክር ቤታችን እና በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ ተቋሞቻችን ላይ የተፈፀመ ከባድ ጉዳት ነው ። ለዚህ ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት አይኖርም ። የጀርመን ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአስቿኳይ ጉዳዩን ያጣራል ፣አሰፈላጊውን እርምጃም ይወስዳል ብዬ እጠብቃለሁ ።በኔ አመለካከት ስለ ጉዳዩ የማሳወቅ ሃላፊነት የዩናይትድ ስቴትስ ነው ።

በጀርመን ምክር ቤት የተቃዋሚው የግራዎቹ ፓርቲ ምክትል ተጠሪ ኮንስታንቲን ቮን ኖትስም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት

«እነዚህ ክሶች እውነት ከሆኑ ትልቅ ቅሌት ነው ። በህገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ምክር ቤቱ ነው የስለላ መስሪያ ቤቶችን የሚቆጣጠረው ፤ የስለላ ድርጅቶች ፓርላማዎችን አይቆጣጠሩም ። ስለዚህ አስቸኳይ ገለፃ እንጠብቃለን ። አስፈላጊ ከሆነም ህጋዊ መዘዞችንም ሊያስከትል ይችላል ።»

Symbolbild NSA Spionageaffäre
ምስል imago

ሌላው ተቃዋሚየአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደግሞ ሃላፊነቱ በመራሂ ተመንግሥት አንጌላ ሜርክል ፅህፈት ቤት ላይ እንደሚወድቅ አስታውቆ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ባለስልጣናት ያለ አንዳች ገደብ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ሜርክል ያዛሉ ብዬ እጠብቃለሁ ብሏል ። ተጠርጣሪው ፣የአሜሪካን ብሔራዊ የስለላ ድርጅት በምህፃሩ NSA በጀርመን ባለሥልጣናትና በጀርመን ህዝብ ላይ አካሄደ የተባለውን ስለላ ለማጣራት ከጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመውን ኮሚቴ ሰነዶች ለአሜሪካን የስለላ ድርጅቶች አሳልፎ ሰጥቷል ሲሉ በመጀመሪያ የዘገቡት ጉዳዩን በጋራ ሲከታተሉ የቆዩት 3 የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ናቸው ። NDR ና WDR የተባሉት የጀርመን የራድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ዙድ ዶይቸ ትሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ በዘገቡት

መሠረት ተጠርጣሪው የNSAን ጉዳይ የሚያጣራውን ኮሚቴ መረጃዎችን መሰብሰቡን ቃሉን ሲሠጥ አምኗል በዘገባው መሠረት ። ይሁንና የአጣሪው ኮሚቴ የበላይና የወግ አጥባቂው የጀርመን ክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ በምህፃሩ የCDU አባል ፓትሪክ ዜንስቡርግ መረጃ ወጥቷል መባሉን አስተባብለዋል ።

«ዝም ብዬ በመላ ምት መናገር አልሻም ። ባለኝ መረጃ የመርማሪው ኮሚቴ ሰነዶች በስለላ መጠለፋቸውን ሳይሆን ሰነዶቹ ለመርማሪው ኮሚቴ መተላለፋቸውን ነው የማውቀው ።ማለትም ከመንግሥት ተቋማት ወይም ባለሥልጣናት የተላለፈውን ማለት ነው ። የውስጥ ጉዳይ ሰነዶች በጥብቅ የተያዙና ወደ ውጭ ሾልከው የማይወጡ ናቸው ። እንደሚመስለኝ አነዚህ መረጃዎች ሌሎች ባለሥልጣናት በአሁኑ ጊዜ ካሏቸው ሰነዶች ይልቅ ይበልጥ የሚያጓጉ ናቸው ።»

ሃላፊው ቢያስተባብሉም ይኽው አጓጊነታቸው የአሜሪካን ሰላዮችን ትኩረት እንደሳበ ይገመታል ። ጀርመናዊው የስለላ ጉዳዮች አዋቂ ኤሪሽ ሽሚት ኤንቡም አሜሪካን ከዚህ ኮሚቴ ማግኘት የምትፈልጋቸው ሚስጥራዊ መረጃዎች አሉ ይላሉ ። ከመካከላቸውም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው ።

Erich Schmidt-Eenboom
ኤሪሽ ሽሚት ኤንቡምምስል imago stock&people

« አንዱ በድብቅ ስብሰባዎችም ቢሆን ኤድዋርድ ስኖውደን ለኮሚቴው የሚነግረውን በሙሉ ማወቃቸውን እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ ። ከዚህ ሌላ ሚስጥራዊ ተብለው በሚያዙት ጉዳዮች ላይ በጀርመን የስለላ ድርጅት እና በNSA መካከል ስላለው ትብብር የጀርመን የስለላ ድርጅት ለጀርመን ምክር ቤት አባላት እስከምን ድረስ መረጃ እንደሰጠ ማወቅ ይፈልጋሉ ። በአጠቃላይ ሲታይ ለመገናኛ ብዙሃን የመጨረሻ መልስ ለመስጠት ዝግጅት ለማድረግ ከሚቴው ስለ ጉዳዩ ያለውን እውቀት ለመፈተሽ ታስቦ የሚደረግ ነው ።»

ከዚህ ቀደም NSA የጀርመን መራሂተ መንግስትን ስልክ ጨምሮ በጀርመን ዜጎች ላይ አካሂዷል የተባለው ስለላ ያስከተለው ንዴት ሳይበርድ ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የዚህ ስለላ ቅሌት መፈፀም ፖለቲከኞችን ና በአጠቃላይ ዜጎችን በእጅጉ አስቆጥቷል ። አሜሪካን እስካሁን አልሰልልም የሚል ውል አልፈርምም ማለቷንም ይቃወማሉ ። ብዙዎችም ጀርመን በተደጋጋሚ ለአሜሪካን የሥስለላ ዒላማ ለምን ሆነች የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው ።ሽሚት ኤንቡም እንደሚሉት የዚህ አንዱ ምክንያት ሃገሪቱ የአሜሪካን ሰላዮች የያዘችበት መንገድ ነው ።

« ትልቅ ቅሌት ነው ። የምንገኝበት ሁኔታ የጀርመን የስለላ ድርጅት BND ጀርመን የሚገኙ የአሜሪካን ሰላዮችን እንደ ጠላት ኃይሎች የማይቆጥርበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ። ጀርመን ውስጥ በሰፊው የስለላ ሥራ እንዲያካሂዱ ተፈቅዶላቸዋል ። ይሁንና አንድ የጀርመን የስለላ ድርጅት ሠራተኛ አንድ የጀርመንን የህግ ተቋም እንዲሰልል ሲሰማራ በስለላ አገልግሎት ትብብር ረገድ ተሰምቶ የማይታወቅና ገደቡን ያለፈ ድርጊት ነው ።»

Symbolbild NSA Überwachung
ምስል imago/Roland Mühlanger

አንዳንድ ጀርመናውያን አሜሪካን በጀርመን ላይ ከወዳጅ ሃገር የማይጠበቅ ስለላ ማካሄዷ በቀላሉ መታለፍ አይገባውም ይላሉ ። የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቃል አቀባይ ከባድ ባሉት በዚህ ጉዳይ ላይ ፖሊስ ምርመራውን እስኪጨርስ ድረስ ጽህፈት ቤታቸው ምንም ዓይነት እርምጃ አይወስድም ብለዋል ። የስለላው ቅሌት ሽሚት ኤንቡም እንዳሉት ለጊዜውም ቢሆን በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል አይሆንም ።

« ይህ በርግጠኝነት የፖለቲካውን መድረክ ያበላሸዋል ። ይሁንና የስለላ ስራዎችን በተመለከተ ላቅ ያለ ሙያዊ አስተሳሰብ ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ ። ይህም ማለት የስለላ ሠራተኞች ለየት ያለ ባህርይ ያሳያሉ ። ከተወሰነ ንትርክ በኋላ ወዲያው ግንኙነቱና ሥራው ሁሉ እንደነበረው ይቀጥላል ።»

ጉዳዩን ተከታትለው ያጋለጡትሶስቱ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ተጠርጣሪው ሰላይ ለሩስያዎች መረጃ ለመሸጥ ሲሞክር ነው የተያዘው ።በመጀመሪያ ላይ እንዲያውም ለሩስያ ይሰልላል የሚል ጥርጣሬ ነው የነበረው ። አሁንም ቢሆን ይህ ከነ አካቴው የተተወ ጉዳይ አይደለም ። በሽሚት ኤንቡም አባባል በውጭ ስለላ ሥራ ውስጥ ሰላዩ ለማን እንደሚሰራም በትክክል ላያውቅ ይችላል ።

« በስለላ ሥራ በሃሰት በማስመሰል መመልመልም ሊኖር ይችላል ።ምናልባት ለሩስያ የሚሰሩ ሰዎች ለአሜሪካን ድርጅት ነው የምትሰራው ብለው ነግረውት ይሆናል ። በዚህ ሥራ ውስጥ ይህም ሊሆን ይችላል ።»

ተጠርጣሪው ለማንም ይስራ ለማን ጥፋተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ ወንጀሉ ህገ መንግሥታዊ አካልን መሰለል ነውና በሽሚት ኤንቡም ኣስተያየት የብዙ ዓመታት እሥራት ሊበየንበት ይችላል ።

አድማጮች ለአውሮፓና ጀርመን ዝግጅት ጥቆማ ጥያቄ እንዲሁም አስተያየት ካላችሁ በኢሜል በSMS ወይም በፌስቡክ ፃፉልን እናስተናግዳለን ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ