የአማራ ክልል አዲስ ርእሰ መስተዳድር ሹመት መጽደቅ
ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2011ከዚህም ሌላ በሕግ እየተመሩ ስርዓትን በማስፈን የተረጋጋ የፖለቲካ መስተጋብርን እውን በማድረግ ረገድም በክልሉ ቀላል የማይባል ውሱንነት እንደነበርም ተናግረዋል። የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችም በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት እንደሚገባቸው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ-አዴፓ የርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንን ህልፈት ተከትሎ በቅርቡ አቶ ተመስገን ጥሩነህን እጩ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መምረጡ የሚታወስ ነው። የእጩ ርዕሰ መስተዳድሩን ሹመት ዛሬ የተሰበሰበው የአማራ ክልል ምክር ቤት ሹመቱን በተባበረ ድምፅ አፅድቆታል። ርእሰ መስተዳድሩ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ ረዘም ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ዕጦትና ምክንቱን አንስተዋል። ከወሰንና ከማንነት ጋር በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ለሕዝቦች መራራቅ እና በጥርጣሬ መተያያ ምክንያቶች እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እና በጋራ ምክክር እንደሚፈቱ አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በንግግራቸው ጠቁመዋል።
ለሁሉም ችግሮች መነሻ የሰላም እጦት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን ይህን ችግር ለማስተካከል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለአመራራቸው ውጤታማነት የሴቶችን፣ የወጣቶችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እና የሌሎችም አካላት እገዛም ጠይቀዋል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዝቅተኛ አመራርነት እሰከ ከፍተኛ አመራርነት የሠሩ እና በቂ የአመራር ልምድ ያላቸው መሪ እንደሆኑ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተናግረዋል። ዝርዝሩን የባሕር ዳር ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን ልኮልናል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ተስፋለም ወልደየስ