1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአል ሲሲ ማንነት

ዓርብ፣ መጋቢት 21 2010

በግብፅ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደተጠበቀው የቀናቸው ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ፎቶግራፍ በአሁኑ ጊዜ በመዲናይቱ ካይሮ በምርጫ ዘመቻ ሰሌዳዎች በብዛት ተለጥፎ ይታያል፣ ይሁንና፣ ግብፃውያን ስለ አል ሲሲ የግል ኑሮም ሆነ ቤተሰባቸው ያን ያህል የሚያውቁት ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/2vDUp
Ägypten Präsidentenwahl Unterstützer von al-Sisi
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Nabil

አል ሲሲ

 አል ሲሲ አንድ ሴት እና ሶስት ወንድ ልጆች ያላቸው ፕሬዚደንት አል ሲሲ የግል ኑሯቸውን ሆን ብለው የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንዳያገኝ አድርገዋል። ይህ ጥረታቸው  ፕሬዚደንቱ የንግግር ሳይሆን የተግባር ሰው መሆናቸውን ለማሳየት ከፈጠሩት ገፅታ ጋር ይስማማል። ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ስለራሳቸው እንዲህ ብለው ነበር።
«  እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፣ እኔ ምንም ሳይሰራ የሚያወራ ብቻ ፖለቲከኛ አይደለሁም። ሀገሪቱን እየገነባን ነው ያለነው። ይህን የምናደርገው ግን በማውራት አይደለም።  ሀገሪቱ እንዴት እንደገና መቆም መቻሏን አምላክ ነው የሚያውቀው። »
የ63 ዓመቱ አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከድሀ ቤተሰብ ነው የመጡት ። በጦር መኮንን ሙያቸው የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ መሆን ችለዋል። የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚደንት  መሀመድ ሙርሲ በጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓም በጦር ኃይሉ ከስልጣን በተወገዱበት ጊዜ ዋና ሚና ተጫውተዋል። ይህም በብዙ ግብፃውያን ዘንድ ተወዳጅ አድርጓቸዋል፣ በ2014 ዓም ለፕሬዚደንትነት በተወዳደሩበት ጊዜ በ97% የመራጭ ድምፅ ማሸነፍ ችለዋል።  በተለይ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ለሴቶች ያሳዩት ክብር የሴቶችን ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።
«እኛ እያለን ግብፃውያንን ማንም አያሸብርም። ይህ ሲሆን ዝም ብለን ከማየት ብንሞት ይሻለናል።   ምክንያቱም ሰው አክባሪነትህ እና ጀግንነት የሚታወቀው ማንም ፣ በተለይም ፣ ሴቶች እንዳይፈሩ ስታደርግ ነው።»
ዛሬ በግብፅ መንግሥት ውስጥ ስልጣን ላይ ያሉት ሴቶች ቁጥር ስድስት ሲሆን፣ ሀገሪቱ ካሁን ቀደም ይህን ያህል ሴቶች ባለስልጣናት ኖረዋት አያውቁም።
አብደል ፋታህ አል ሲሲ እንደ ብዙዎቹ ግብፃውያን ሀይማኖተኛ ናቸው፣ ከቁርዓን መጥቀስ ይወዳሉ። ይሁን እንጂ፣ ከሀይማኖታዊ ተቋማት ጋር ግልጹን ክርክር በመፍጠር የእስልምና እምነት ዘመናይ የሚሆንበት ተሀድሶ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በ2015 ዓምም አል ሲሲ ወደ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በመሄድ በገና በዓል ስርዓተ ፀሎት ላይ ተሳትፈዋል፤ ይህን ከርሳቸው በፊት የነበረ አንድም የግብፅ ፕሬዚደንት አድርጎ አያውቅም።
ምዕራቡ ዓለም፣  ጀርመን ጭምር አል ሲሲን ለግብፅ መረጋጋት እንደ ዋስትና ይመለከቷቸዋል። ይህ የምዕራባዊው ዓለም አመለካከት ታድያ ፕሬዚደንቱ ግብፅን በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በጠንካራ እጅ እንዲመሩ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ለሚሰነዘርባቸው ትችት አል ሲሲ አልፍ አልፎ የሚሰጡት መልስ ምን ያህል ትችት መቀበል እንደሚከብዳቸው ያሳያል፣  አንድ የምክር ቤት እንደራሴ የነዳጅ ዋጋን ለመጨመር የተያዘውን እቅድ አል ሲሲ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲገፉት በጠየቁበት ጊዜ ቀጥሎ የሰጡት የቁጣ መልስ ይህን እንዳረጋገጠ ምሳሌ ሊታይ ይችላል።
«  ማን ነህ አንተ? ለመሆኑ ይህን ጉዳይ በሚገባ ተመልክተኸዋልን? ምን ማለትህ ነው? ስለዚህ እየተነጋገራችሁበት ያለውን ጉዳይ ተረድታችሁታልን?  እያሰብክ ነው ወደ ሌላ ጊዜ ግፋው የምትለኝ? ይህ መንግሥት እንደገና ጠንክሮ እንዲቆም ትፈልጋለህ? »  
በ2011 ዓም  የኤኮኖሚ ቀውስ በተከሰተበት ጊዜ አል ሲሲ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ አይ ኤም ኤፍ ቀደም ሲል እንዲወሰድ አቅርቦት የነበረውን ተሀድሶ በተግባር ተርጉመዋል፤ እርግጥ፣ ይህ የሸቀጦችን ዋጋ ቢያስወድድም፣ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ግን ተፎካካሪ ማድረጉ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም አል ሲሲ  የስዌዝ ቦይን የማስፋት እና አዲስ መዲና መቆርቆርን የመሳሰሉ ግዙፍ የግንባታ ፕሮዤዎችን አነቃቅተዋል። ይህ ሁሉ፣ በአል ሲሲ ደጋፊዎቻቸው አስተያየት፣  በተግባር በሚያምን ፕሬዚደንት የምትመራው ግብፅ ወደፊት በመገስገስ ላይ መሆኗን ያሳያል።
አርያም ተክሌ/ካርስተን ኪውንቶፕ

Ägypten Präsidentenwahl Unterstützer von al-Sisi
ምስል Getty Images/AFP/F. Belaid
Bildergalerie Ägypten Dritter Jahrestag des Aufstandes 25. Januar 2014
ምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሀመድ