1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መግለጫ በጸጥታ ኃይሎች ተከለከለ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21 2011

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) በራስ ሆቴል ያቀዱት ጋዜጣዊ መግለጫ በጸጥታ ኃይሎች ተከለከለ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት "ከበላይ አካል በመጣ" ትዕዛዝ ጋዜጣዊ መግለጫውን ከመስጠት መከልከሉን አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/3Fvyg
Eskinder Nega - Äthiopien Journalist & Menschenrechtsaktivist
ምስል B. Manaye

በቦታው የነበረ የDW ዘጋቢ ከረፋድ 3፡30 ሰዓት ጀምሮ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች መግለጫውን ለመከታተል በቦታው መገኘታቸውን ተመልክቷል። ጋዜጠኞቹ በአካባቢው በነበሩ ፖሊሶች ጋዜጣዊ መግለጫው "ተከልክሏል" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። 
የጋዜጣዊ መግለጫው አስተባባሪዎች ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ሲነጋገሩ አልፎ አልፎም ሲጨቃጨቁ የDW ዘጋቢ ታዝቧል። ፖሊሶች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ምስል ለማንሳት የሞከሩትን መከልከላቸውን የአንዳንዶቹንም መቀማታቸውን ሰለሞን ሙጬ ከቦታው ዘግቧል። 
ከአስተባባሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ስንታየሁ ቸኮል "ይህንን መሰሉን ነገር ለ 20 አመታት አልፈነዋል" በማለት ሲናገር ተደምጧል። 
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) በአካባቢው ከነበረ የፖሊስ አዛዥ "ክልከላው ከበላይ አካል የተሰጠ ትዕዛዝ ነው" የሚል ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ክልከላ ላይ በሆቴሉ ደጃፍ ማብራሪያ ለመስጠት ቢሞከርም ክልከላ እንደገጠመው ያስታወቀው ባልደራስ በቦታው የነበሩ ጋዜጠኞች እና ጉዳዩን ለመከታተል የተገኙ ግለሰቦች በፖሊስ ኃይል አካባቢውን እንዲለቁ መደረጉን በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ ገልጿል። 

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለDW "አሁን የተረጋጋ ስሜት ላይ ባለመሆናችን ቢቀርብን ይሻላል። ነገሩ ግን የላይ ትእዛዝ ነው በሚል መግለጫው እንዳይሰጥ በፖሊሶች የተከለከልንበት ነው፡፡ ይህን ካልኩ ይበቃል።" ብሏል። በዛሬው ዕለት የተከለከለውን ጋዜጣዊ መግለጫ በሚቀጥለው ሳምንት እንሰጣልን የሚል ምላሽ መሰጠቱንም ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል። 

ሰለሞን ሙጬ

ልደት አበበ