1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና የአውሮፓ ሕብረት የኤኮኖሚ ግንኙነት

ሐሙስ፣ መስከረም 19 1998

በቻይናና በአውሮፓ ሕብረት የኤኮኖሚ ግንኙነት የወደፊት ዕርምጃው ላይ መፍትሄን የሚጠይቁ የተለያዩ ችግሮች ተደቅነው ነው የሚገኙት። የአውሮፓ ኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ቤይጂንግን ጎብኝተዋል።

https://p.dw.com/p/E0eJ

በዓለም ላይ በሕዝብ ቁጥሯ ቀደምት የሆነችው ሕዝባዊት ቻይና በተጠቃሚው ብዛትና በወደፊት ሰፊ ገበያነቷ ብቻ አይደለም ክብደት የሚሰጣት። በተፋጠነ ሁኔታ የሚያድገው ኤኮኖሚዋም አውሮፓውያኑ ችላ የሚሉት ነገር ሆኖ አልተገኘም።

የአውሮፓው ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት የመጀመሪያ ይፋ ጉብኝት ሰፊ የግንኙነት ዘርፎችን ይጠቅልል እንጂ በተለይ የፖለቲካ ጥያቄዎች ጎልተው የታዩበት ነበር። ሆሴ-ማኑዌል ባሮሶ በጉብኝታቸው ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎና ከኮሙኒስቱ ፓርቲ መሪ ከሁ ጂንታዎ ተገናኝተው የሁለቱ ወገን የኤኮኖሚ ግንኙነት ወደፊት ሊራመድ በሚችልበት ሁኔታ፣ እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳይና የአውሮፓ ሕብረት በቻይና ላይ ጭኖ ባቆየው የጦር መሣሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ላይ ተነጋግረዋል።

የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ባሮሶ ወደ ቻይና የተጓዙበት ዋና ዓላማ የአውሮፓ ሕብረት ጥም በተሻለ መልክ እንዲጠበቅ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ እንዲሁም የሁለቱን ወገን ስልታዊ ትብብር ለማጠናከር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፍቱን ሆኖ የሚራመድበትን ዘዴ ማፈላለግ ነበር።

“ቻይና ሊታሰብ በማይችል ፍጥነት እያደገች ነው። ይህን ደግሞ አውቀን መቀበል ይኖርብናል። አገሪቱ በዓለም ላይ ከቀደምቱ መንግሥታት አንዷ ለመሆን በመቃረብ ላይ ስትሆን ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር የምነጋገረውም በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ነው።” ባሮሶ ከቻይና መሪዎች ተገናኝተው ከመነጋገራቸው በፊት ነበር ይህን ያመለከቱት። የአውሮፓው ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ከዚሁ በማያያዝም ቻይና የነጻ ገበያ ኤኮኖሚውን ሥርዓት መሠረተ-ዓላማዎች ገቢር በማድረግ ለአውሮፓ ተገቢውን የፉክክር ዕድል ለመስጠት ዝግጁ በመሆኗ ጭብጥ መልስ እንደሚሹም ለጋዜጠኞች አስረድተው ነበር።
ቻይና የግል ባለንብረትነትን መብት ታረጋግጥ ይሆን? ገበያዋንስ አውሮፓውያኑ ለርሷ በሚያደርጉት መጠን በአጸፋው ልትከፍትላቸው ዝግጁ ናት ወይ? እነዚህ ቁልፍ ጥያቄዎች በንግግሩ የተነሱ ሲሆን እርግጥ ቻይናም ቅድመ-ግዴታዎችን ማስቀመጧ አልቀረም። ሕዝባዊት ቻይና የአውሮፓ ሕብረት የገበያ ኤኮኖሚ ሥርዓት የሰፈነባት አገር አድርጎ ሙሉ በሙሉ ዕውቅና እንዲሰጣት ትጠይቃለች። ይህም ቻይና በአውሮፓ ገበዮች በርካሽ ዋጋ በምታራግፋቸው ምርቶች የተነሣ ከብራስልስ በኩል የሚሰነዘር የመቀጮ ዛቻም ሆነ የንግድ ገደብ ጨርሶ መወገዱን ይጠቀልላል።

ይሁንና የአውሮፓው ሕብረት ቻይና በወቅቱ የማሕበረ-ሕዝቡን መሠረታዊ ቅድመ-ግዴታዎች አታሟላም ሲል የገለጸው በቅርቡ ባለፈው ሣምንት ነበር። የኮሚሢዮኑ ፕሬዞደንት ባሮሶም ቢሆን በቤይጂንግ ያጠናከሩት ይህንኑ የብራስልስን አቋም ነው።

“እርግጥ ነው፤ ጊዜው ለዚህ ጉዳይ ገና የሰከነ አይደለም። ይሁን እንጂ በዚህ በኩል ብዙ ዕርምጃ መደረጉም ሃቅ ነው። በበኩሌ አሁን የሚቀጥለውን ዕርምጃ ለማየት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም አንድ ውሣኔ ማስተላለፍ የምንችለው ይህን ስናውቅ ነው። ግን መቼ ይህን ብዬ ለመናገር አልችልም።”

ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ከቤይጂንግ ባለሥልጣናት ባካሄዷቸው ንግግሮች የሰብዓዊ መብት ጉዳይንና የአውሮፓው ሕብረት በቻይና ላይ ጭኖ ያቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብም አንስተዋል። የጦር መሣሪያው ማዕቀብ ከ 16 ዓመታት በፊት በቤይጂንግ ገነተ-ሰላም አደባባይ በቲየን-አን-ሜን በሃይል የተቀጨውን መፍቀረ-ዴሞክራሲ ንቅናቄ አስመልክተው ከተጫኑት አሁንም ጸንቶ ያለው የመጨረሻው መሆኑ ነው። የአውሮፓው ሕብረት ቀደም ሲል ማዕቀቡን በዚህ በያዝነው ሐምሌ ወር ለማንሣት ውጥን ነበረው።
ይሁንና የቻይና መንግሥት አንድ አካሉ አድርጎ የሚመለከታት ታይዋን ለመገንጠል ብትፈልግ ይህንኑ በሃይል ለማስቆም የሚያስችል ሕግ ማስተላለፉ ጉዳዩን እንዳከበደው ይታወቃል። የአውሮፓው ሕብረት በተለይ አሜሪካ ጉዳዩ እንዲሸጋሸግ ያደረገችውን ግፊት ሊቋቋመው አለመቻሉ ታይቷል። የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ባሮሶ ማዕቀቡን ላለማንዋት ሌላም ተጨማሪ ምክንያት አለ ይላሉ።

“በጉዳዩ በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ አጠቃላይ የሃሣብ ስምምነት መገኘቱም ጠቃሚ እንደሆነ እናምናለን። 25 አገሮች፤ 25 የዴሞክራሲ መንግሥታት ነን። እና በዚህ ጉዳይ ከአንድ ውሣኔ ለመድረስም የመላው ይፋ አስተያየት ያስፈልገናል። አንዱ ጉዳይ ቻይና ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ውል ዕውቅና መስጠቷ ይሆናል። ሌላው ጠቃሚ ትልቅ የፖለቲካ እሥረኞች ሁኔታ ነው። ማንኛውም ሰው በግል አስተሳሰቡ የተነሣ ወህኒቤት ውስጥ መማቀቁን ተገቢ አድርገን አንመለከትም።”ብለዋል ባሮሶ!

በባሮሶ ዕምነት እንግዲህ ማዕቀቡ ለጥቂት ጊዜ ጸንቶ መቀጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። ሕዝባዊት ቻይና ሰፊ የኤኮኖሚ ትኩረትን የምትስብ አገር ብትሆንም በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ረገጣና የሞት ብያኔ በሰፊው የሚፈጸምበት ሌላ መሰል አገር በዓለም ላይ ተፈልጎ አይገኝም። የመንግሥት ተቃዊዎችና የውሁዳን ሃይማኖት ተከታዮች ይሳደዳሉ፤ የማሰቃየት ድርጊትና የፕሬስ ቁጥጥር እጅግ የጠበቀ ነው።

ማኑዌል ባሮሶ ብዙ ዴሞክራሲ ለፖለቲካ መረጋጋትና ላልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ነው ሲሉ በድሆችና በሃብታሞች መካከል ያለውን ልዩነት ለመቀነስ ይጠቅማልም ባይ ናቸው። የአውሮፓው ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ይህንኑ የፖለቲካ ለውጥ አስፈላጊነት ሃሣብ ቤይጂንግ ውስጥ ከማሕበራዊው ጠበብት አካዳሚ ፊት ቀርበው ባሰሙት ንግግር ለማስጨበጥ ሞክረዋል። ጥያቄው ምን ያህል ተደማጭነት አግኝተዋል ነው።

ለማንኛውም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ችግር ባያጣውም የኤውሮ-ቻይናው ትብብር እጅግ ጠቃሚ ስልታዊ ሽርክና ለመሆኑ ብራስልስና ቤይጂንግ የሚጋሩት ዕምነት ነው። ግንኙነቱ ተስፋፍቶ መቀጠሉንም ሁለቱም ወገኖች ይሻሉ። የአውሮፓው ኮሚሢዮን በወቅቱ ከቻይና የፋብሪካ ሠራተኞችን ደህንነት እንዲጠብቁ ሆነው የተሰሩ ጫፋቸው ላይ ብረታማ ልባስ ያላቸውን ጫማዎች ወደገበዮቹ የሚያስገባበትን ሁኔታ በመመርመር ላስ ይገኛል። ችግሩ ቻይና በተለያዩ መስኮች እንደሚታየው እነዚህን ምርቶች እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ ማቅረቧና የአውሮፓን አምራቾች የፉክክር አቅም የምታዳክም ሆና መገኘቷ ነው። ይህም እንዲሁ መፍትሄን ይጠይቃል።

የአውሮፓ ሕብረት ለቻይና ዋነኛው የንግድ ሸሪክ ነው። ቻይና ወደ ሕብረቱ ገበዮቹ ብዙ ምርት የምታስገባ ሲሆን የንግዱ ሂደትም እጅግ ፈጣን በሆነ መንገድ እያደገ ሲሄድ ነው የሚታየው። ስለዚህም በቅርቡ በጨርቃ-ጨርቅ ምርቶች ገበያ እንደታየው ለችግሮቹ አፋጣኝ መፍትሄ መሻቱ ግድ ይሆናል። ሁለቱ ወገኖች በዚህ ጉዳይ ከአስታራቂ መፍትሄ ከደረሱ በኋላ ቻይና የጨርቃ-ጨርቅ የውጭ ንግዷን በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት በተወሰነ መጠን ገድባ ለመያዝ ግዴታ ገብታለች።

የአውሮፓው ሕብረትም በበኩሉ ከ 2008 አንስቶ ገበዮቹን ለዚህ ምርት ሙሉ በሙሉ ለመክፈት ተስማምቷል። ቻይና የምትፈልገው የአውሮፓው ሕብረት ገበዮቹን በጠቅላላው እንዲከፍትላትና እንደ ንግድ ሸሪክ ሙሉ ዕውቅና እንዲሰጣት ነው። ይሁንና ባሮሶ በዚህ በኩል ለቤይጂንግ ባለሥልጣናት አረጋጊ ተሥፋ ከመስጠት አልፈው አወንታዊ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።
ይህንኑ የብራስልስን አቋምም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎና ከንግድ ሚኒስትሩ ከቦ ሺላይ ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩባቸው ወቅቶች በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርገዋል። ባሮሶ ዕውቅናው ገና የሁለቱን ወገኖች ጥረት በሚጠይቁ ቴክኒካዊ ችግሮች መፈታት ላይ ጥገና ነው ብለዋል። ይሁንና መጣራት የሚኖርባቸው ችግሮች ምን እንደሆኑ ቢቀር በይፋ አልገለጹም።

የባሮሶ ጉብኝት በአጠቃላይ ሲታይ የክብደቱን ያህል መሠረታዊ ለውጥ ወይም ዕርምጃ የታየበት አልነበረም። ሕዝባዊት ቻይና በተለይ ለግንኙነቱ መዳበር ቁልፍ በሆነው የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ላይ የማንንም ምክር ሆነ ግፊት እንደማትሻ ከዚህ ቀደም ደግሞ-ደጋግሞ የታየ ነገር ነው። በዚህ ጉዳይ ከአውሮፓም ሆነ ከአሜሪካ በየጊዜው የተሞከረውን ተጽዕኖ በቁጣና በቁርጠኝነት ስትቃወመው ነው የኖረችው።

በሌላ በኩል ምዕራባውያኑ መንግሥታትም ቢሆን የሰብዓዊ መብቶችን መረገጥ ጉዳይ አስመልክተው በቻይና ላይ አጠቃላይ ማዕቀብ ሊጭኑ ቀርቶ ጠንከር ያለ የወገዛ ቃል ለመሰንዘር እንኳ እምብዛም ሲደፍሩ አይታዩም። ከዚህ ይልቅ ጥቅማቸውን ማስቀደማቸው የሰብዓዊ መብትን ከበሬታ በሁለት መስፈርት እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። ይህም ባለበት የሚቀጥል ነው የሚመስለው።