1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ምክር ቤት የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽንን ተቃወመ

ቅዳሜ፣ ጥር 18 2011

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አፀደቀ፡፡ምክር ቤቱ የኮሚሽን ማቋቋምያ አዋጁን ኢ-ሕገመንግስታዊ ብሎታል፡፡

https://p.dw.com/p/3CG5y
Äthiopien | Tigray region council meeting
ምስል DW/M. Haileselassie

የትግራይ ምክር ቤት የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽንን ተቃወመ

ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ የአምስተኛ ዘመን 14 መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የትግራይ ክልል ምክር ቤት በዛሬው የከሰዓት በፊት ውሎው በቅርቡ  በተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ መክሯል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ለማቋቋም የፀደቀው አዋጅ የሕገ መንግስት ጥሰት የተፈፀመበት መሆኑን ገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል ምክር ቤት ከፀደቁት የውሳኔ ሐሳቦች መካከል ቀዳሚው የፌደሬሽን ምክር ቤት ስለተፈፀመው የሕገ መንግስት ጥሰት ትርጉም እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ ሌላው የውሳኔ ሀሳብ የፀደቀው አዋጅ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ በአስቸኳይ እንዲታረም ጠይቋል። ሶስተኛው የውሳኔ ሀሳብ ደግሞ የትግራይ ክልል መንግስት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ጉዳዩን በዝርዝር አይቶ የትርጉም ጥያቄ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ ኃላፊነት የሚሰጥ ነው፡፡

Äthiopien | Tigray region council meeting
ምስል DW/M. Haileselassie

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው በትግራይ ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ታፈረ "የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መፅደቅ ኢ- ሕገ መንግስታዊ በመሆኑ የውሳኔ ሐሳቦቹ እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል፡፡ "ኮሚሽኑ ይፈፅማቸዋል የተባሉ ተግባራት በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት ለፌደሬሽን ምክር ቤት የተሰጡ ናቸው ያሉት"  የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሞገስ "የማንነት ይሁን ሌላ ጥያቄ ያለው ወገን ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ ምላሽ ያገኛል" በማለት ለDW ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው የክልሉ ምክር ቤት "አሁን ከቀረቡት በላይ" የውሳኔ ሐሳቦች ማቅረብ ይችላል ብለዋል፡፡ ዛሬ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት የክልሉ ምክርቤት "የወሰንና ማንነት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን በግልፅ ጥያቄ አቅርቧል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ እና አዋጁ አግዶ ይመረምረዋል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የቀረበለትን የወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን የሚጠይቀውን የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድጋፍ ነው ያፀደቀው፡፡

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ተስፋለም ወልደየስ