የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ዘገባ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 2004በየሃገሩ ሙስና የሚገኝበትን ደረጃ የሚገመግመው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ዘንድሮ በትላልቅ ኩባንያዎች ደረጃ ሙስና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የመረመረበትን ዘገባ አቅርቧል ። በዚሁ ምርመራ ተቋሙ ግዙፍ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ሙስናን ለመከላከል ስለ ሚወስዷቸው እርምጃዎች ና የገንዘብ ዝውውራቸው ምን ያህል ግልፅ አሰራርን እንደሚከተል ጥናት አካሂዷል ። የዶቼቬለው ማቲያስ ቦሊንገር የጥናቱ ውጤት ላይ ያተኮረ ዘገባ አሰናድቷል ። ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሙስና በየሃገሩ የሚገኝበት ደረጃ ላይ ማትኮሩን ትቶ በኩባንያዎች ምን ዓይነት ባህርይ እንዳለው ዝርዝር ጥናት ሲያቀርብ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው ። ጥናቱም ነው ጥናት በ200 አገሮች ውስጥ በሚሰሩ 105 ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ላይ ነበር ያተኮረው ። የትርንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ ሊቀመንበር ኤዳ ሙለር እንደሚሉት በተለይ በድሃዎቹ አገሮች አሰራሩ ግልፅነት ይጎድለዋል ።
« እነዚህ ኩባንያዎች ንግድ በሚያካሂዱባቸው አገሮች ስለሚያገኙትኝ ትርፍና ስለ ሚከፍሉት ቀረጥ በግልጽ የሚታወቀው በአማካይ ጥቂት ነው ። ይህ የሚከሰተውም ብዙውን ጊዜ እጅግ በደኽዩና አጠያያቂ መንግሥታዊ መዋቅር ባላቸው ሃገራት ነው »
ፎርብስ በተባለው የአሜሪካን መፅሄት ላይ የተዘረሩ 105 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኩባንያዎች ፣ በንግድ ያገኙትን ገቢ ና የሚከፍሉትን ቀረጥ በግልፅ ያሳውቁ እንደሆነና ምን ዓይነት የሙስና መከላከያ መርሃ ግብር እንዳላቸው ነበር ጥናቱ የገመገመው ። መረጃዎቹ የተሰበሰቡትም የኩባንያዎቹን ድረ ገጾች ከመሳሰሉ ምንጮች ነው ። በግምገማው መሰረት የኖርዌዩ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ Statoil ና የብሪታኒያና የአውስትሬሊያው ማዕድን አውጭ ኩባንያ ሪዮ ቲንቶ አንድኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል ።የቻይናውያኑ ባንክ ኦፍ ኮምዩኒኬሽን ና የቻይና ባንክ የመጨረሻ ደረጃ ነው የተሰጣቸው ።ሮቢን ሁድስ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የጥናት ክፍል ባልደረባ ምክንያቱን ያስረዳሉ ።
« ያየነው ምንድን ነው በመዘርዝሩ ጠርዝ ላይ ያሉት ቻይናን የመሳሰሉ አገሮች የዓለም ዓቀፍ ደንብና ደረጃን አሟልተው ለመገኘት በአዲስ መልክ ሥራቸውን ማካሄድ አለባቸው ። ግን ደንቦቹ በአፋጣኝ ይለዋወጣሉ ። ባለፈው ዓመት ቻይና በተለይ ችግሩን በውጭ አገር ለመከላከል ፀረ ሙስና ህግ አውጥታለች ። ይህም ከ ከኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ፀረ ሙስና ህግ ጋር እንዲጣጣም አድርጋ ነበር ። ስለዚህ በነዚህ ኩባንያዎች ላይ ጫና በማድረግ ሙስናን ለመታገል ዓለም ዓቀፉን ግፊት ማጠናከር ጠቃሚ ነው ።
የአዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ባለቤቶች እንደ ጉግል አፕል ና አማዞን የመሳሰሉትም ደካማ ሆነው ነው የተገኙት ። እነዚህ ኩባንያዎች በመዘርዝሩ ከመጨረሻዎቹ 5 ኩባንያዎች በላይ ደረጃ ነው ያገኙት ። በፋይናንሱ ዘርፍ የሚገኙ ኩባንያዎችም የተሻለ ደረጃ ላይ አልተገኙም ። ግዙፎቹ የገንዘብ ተቋማት ጎልድማን ሣክስ ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ እንዲሁም ቪዛና ሲቲ ግሩፕ በመዘርዝሩ ከመጨረሻዎቹ 3 ኩባንያዎች በፊት ያሉትን ቦታዎች ነው የያዙት ደረጃ ላይ ናቸው ። እንደገና ሙለር
« እንደኛ አመለካከት ጥናቱ ያሳየው በተለይ ለፋይናንሱ ዘርፍ ተጨማሪ ደንቦችና አሰገዳጅ የሆነ መደበኛ ዘገባዎች ማቅረብ አስፈላጊ ነው ። ባናኮች የሚሳተፉበትን መመሪያ ና የገንዘብ ድርሻቸውን በግልፅ ማሳየት አለባቸው ። የመታደጊያ ገንዘብ ከቀረጥ ከፋዩ ወስዶ በያንዳንዱ ሃገር በአግባቡ ቀረጥ መከፈሉን ማረጋገጥ የሚያስችለውን ሰነድ በይፋ ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆን የሚያስኬድ አይደለም ። »
በጥናቱ ከተካተቱት 7 የጀርመን ኩባንያዎች ውስጥ ሶፍትዌር አምራቹ SAP የኬሚካል ኩባንያው BASF ና የመድን ዋስትናው ኩባንያ Allianz ጥር ደረጃ አግኝተዋል ። ሰባቱ የጀርመን ኩባንያዎች በደረጃው ሰንጠረዥ ከአንደኛ ሶስተኛዎቹ በላይ ነው የተቀመጡት ። ይሁንና ኤዳ ሙለር የጀርመን ጥሬ አላባ አምራች ኩባንያዎች በአውሮፓ በተደነገገው ህግ መሰረት ገቢና ወጪያቸውን በግልፅ እንዲያሳውቁ ባለማድረግ የፌደራል ጀርመን መንግሥትን ተችተዋል ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሰ