1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቴይለር ብይንና ምዕራብ አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ግንቦት 23 2004

ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀሎች ተመልካች ፍርድ ቤት ትናንት በቀድሞዉ የላይቤሪያ መሪ ቻርለስ ቴይለር ላይ ያሳለፈዉ ዉሳኔ የተለያዩ ምላሾችን እያስከተለ ነዉ። አንዳንዶች ፍርድ ቤቱ የ50ዓመት እስር ፍርድ ለእሳቸዉ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መቀጣጫ ነዉ

https://p.dw.com/p/1562j
ምስል AP

 ሲሉት፤ ገሚሱ ደግሞ ያንሳል ብለዉታል። ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ደግሞ ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ብይን ነዉ። የዶቼ ቬለዉ አሌክሳንደር ጎብል በተለይ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ኗሪዎች በብይኑ ላይ የሰጡት አስተያየት አሰባስቧ፤ ሸዋዬ ለገሠ ታቀርበዋለች።

«በጦርነቱ ጊዜ እንደተሰቃየ ሰዉ በተሰጠዉ ብይን ተደስቻለሁ፤ ሆኖም ሴራሊዮን ዉስጥ ሁላችንም ተሰቃይተናል፤ ከዚህ ስቃይ ያመለጠ ማንም የለም።»

በአዉሮፓዉያኑ 1998ዓ,ም ሴራሊዮን በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ በቻርለስ ቴይለር ይደገፋል በተባለዉ የተባበረዉ አብዮታዊ ግንባር በተሰኘዉ አማፂ ቡድን ግራ እጇ የተቆረጠ ፊናህ ካማራ ናት።

Charles Taylor Liberia Diktator Prozess Niederlande
ቻርለስ ቴይለርምስል picture-alliance/dpa

የቀድሞዉ የላይቤሪያ መሪ ቻርለስ ቴይለር ሴራሊዮን ዉስጥ በርካቶችን እጅና እግር አልባ ያደረገዉን አማፂ ቡድን ረድተዋል በሚል ክስ ጥፋተኛ ተብለዉነዉ የ50ዓመት እስራት ሲከናነቡ አስተዉላ ስሜቷን የገለፀችዉ። በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት የሴራሊዮን የጦር ወንጀል ተመልካች ልዩ ችሎት ጉዳያቸዉ ታይቶ፤ ጥፋተኛም ተብለዉ ይህ ብይን ሲሰጥ፤ 

ቴይለር ክሱን ከመቃወም በተጨማሪ ፍርዱን ይግባኝ እንደሚሉ ቢጠበቅም ብይኑ እንደካማራ ሁሉንም ያረካ አይመስልም። አብዛኛዉ የሴራሊዮን ህዝብ ፍርዱ ያንሳል በሚል እንዳልተደረሰተ ነዉ የራዲዮ ጋዜጠኛ የሆነዉ ሳሂር ጄምስ የጠቆመዉ፤

«ሴራሊዮን ዉስጥ አብዛኛዉ ህዝብ በብይኑ ያን ያህል አልተደሰተም፤ በተለይ ደግሞ እነዚያን አስራ አንድ ህግ አልባ መጥፎ ዓመታት ለማሳለፍ የተገደደዉ ወገን። እንደክሱ አብዛኞቹ ቢያንስ ቴይለር 80 ዓመት ይፈረድበታል የሚል ተስፋ ነበራቸዉ፤ ቅጣቱ በመቀነሱ ብዙዎች አልተደሰቱም።»

በአንፃሩ ሴራሊዮንም ሆነ ላይቤሪያ ዉስጥ ፍርድ ተዛብቷል፤ ችሎቱ በሚዛናዊነት ጉዳዩን አላየም የሚሉም አልጠፉም። የቴይለር አማች አርቱር ሳዬ ፍርዱ የማይገባ ነዉ ሲሉ፤ ሴራሊዮን ዉስጥ የሰዎችን እጅና እግር በመቁረጥ የሚከሰሰዉ አማፂ ቡድን የቀድሞ ቃል አቀባይ ኤልድራድ ኮሊስ ደግሞ አፍሪቃዉያን በራሳቸዉ ሐገር እና ችሎት እንጂ እንደሄጉ ባለ ዓለም ዓቀፍ የወንጀል ችሎት ሊዳኙ አይገባም ይላሉ፤

«ፍትህ የቱጋ እንደሆነ አይታየኝም። የምፈልገዉ ምንድነዉ፤ ከምዕራባዉያን ይልቅ አፍሪቃዉያን በራሳቸዉ ሐገር የራሳቸዉን ሰዎች የሚዳኙበት የራሳቸዉ ፍርድ ቤት ይኑራቸዉ።»

Prozess Charles Taylor Special Court for Sierra Leone
ሴራሊዮናዉያን ብይኑን ሲከታተሉምስል AP

እሳቸዉ እንዲህ ይበሉ እንጂ የችሎቱን የብይን ሂደት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ከሱራሊዮኗ ዋና ከተማ የተከታተሉ አብዛኞቹ እጅ፤ ወይም እንራቸዉን ኤልድራድ አባል የነበሩበት አማፂ ቡድን ያሳጣቸዉ ወገኖች ፍርዱ ማንም ቢሆን በሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈፅሞ በነፃነት ቀና ብሎ ሊሄድ እንደማይችል ያሳያል ነዉ ያሉት።

«ማንም ቢሆን የትኛዉም ከፍተኛ ስፍራ ላይ ቢቀመጥ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ከፈፀመ፤ ዓለም ዓቀፍ ህግን ከጣሰ፤ እኛ እንዳሳለፍነዉ ያለ ጥፋትን ከደገፈ፤ በመጨረሻ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም፤ እናም አሁን ጥፋት ፈፅሞ በነፃ መንቀሳቀስን ደህና ሰንብት ብለነዋል፤ ይህ ነዉ የሴራሊዮናዉያን ምላሽ፤ በጣም ተደስተናል፤ ዕለቱን ሞተዉም ቆመዉም የሚሰቃዩትን የጦርነቱን ሰለቦች እንዘክርበታለን።»

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ