1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዝያ ፀረ ሽብር ትግል እና ሰብዓዊ መብት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2008

ቱኒዝያ በተደጋጋሚ የአሸባሪዎች ጥቃት ደርሶባታል ። ሃገሪቱም አሸባሪነትን ለመታገል እየጣረች ነው። ይሁንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፀረ ሽብሩ ትግል ሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል የሚል ስጋት አላቸው። በዚህ የተነሳም የመብት ቷጋቾች «ሽብርን እንቃወማለን » « ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንፈልጋለን »የሚል ዘመቻ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/1IiPU
Tunesien Tunis Soldat eröffnet Feuer auf Kameraden
ምስል Reuters/Z. Souissi

[No title]

ተዋናዮችና ሙዚቀኞች የሚገኙበት ታዋቂ ቱኒዝያውያን «ሽብርን እንቃወማለን » « ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንፈልጋለን» በተሰኘው ዘመቻቸው በፀረ ሽብሩ ትግል ውስጥ ንፁሃን ዜጎች የሚደርስባቸው እንግልት እንዲቆም እየጠየቁ ነው ። ሂዩመን ራይትስ ዋችን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚሉት አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚወሰደው እርምጃ ሰበብ በህዝቡ እና በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ ጫናው በርትቷል ። የድርጅቱ የቱኒዝያ ተጠሪ ኤማ ግዌላሊ እንደሚሉት፣
«ከእያንዳንዱ የግድያ ሙከራ በኋላ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ደርሰንበታል። በህዝቡ ዘንድ ደግሞ በፀረ ሽብሩ ትግል ውስጥ ሰብዓዊ መብት መከበር የለበትም የሚል ግንዛቤ አለ ። ይህም እየተጠናከረ መጥቷል ። »
ከዚህ የባሰው ደግሞ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አሸባሪዎች የሚያደርሱትን ጥቃት እንደዘበት ያዩታል እየተባሉ መከሰሳቸው ነው ። የመብት ተሟጋቾች በአሸባሪነት ላይ የሚወሰደው ዘመቻ ተገቢ እና ህጋዊ እርምጃ መሆን አለበት፣ ያ ማለት ቁም ስቅል ድብደባ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ እሥራት መኖር የለበትም ይላሉ ። ቁም ስቅልን የሚቃወመው ድርጅት ባልደረባ ጋብርየል ራይተር እንደሚሉት በርካታ ቱኒዝያውያን የፀጥታ ጥበቃው ተጠናክሮ ማየት ነው የሚፈልጉት ።
«ህዝቡ መረጋጋት እና ፀጥታ እንዲሰፍን ፀጥታ አስከባሪዎች ተጨማሪ ሥልጣን እንዲሰጣቸው ይፈልጋል ። ሆኖም እነዚህ ኃይሎች ሥልጣናቸውን አለአግባብ ሲጠቀሙ አይቶ እንዳላየ ይሆናሉ ። እነርሱም የዚህ ችግር ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ አያስቡም ። »
ሁሴም ሃምዲ ማንኛውም ዜጋ ሊደርስበት የሚችለው ይህ ችግር ገጥሞታል ። አንድ ቀን ፖሊሶች ቤቱ መጥተው ሳያገኙት ቀሩ ። ሥራ ላይ ስለነበር ። በሌላ ቀን ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ለምን እንደሚፈለግ ሲጠይቅ ሙሉ ቀን አቆይተውት የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበውለታል ። ይፀልይ እንደሆነና እንዳልሆነ ፣ለምን ብዙ ጊዜ ወደ ውጭ እንደሚሄድ ሲጠይቁት ውለዋል ። በሌላ ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ገጥመውታል ።
« ያኔ ለሥራ ጉዳይ ወደ ግብፅ እበር ነበር ። በአውሮጵላን ማረፊያው ለ10 ሰዓትት አቆዩኝ ። ከዚያ በኋላ እንድበር የተፈቀደበት ወረቀት በፋክስ መጣ ። በማግስቱ ጠዋት በረርኩ ።ስመለስም እንደዚሁ ተመሳሳይ እንግልት ነው የደረሰብኝ ። የፀረ ሽብር ሠራተኞች ተጠርተው ስጠየቅ ነበር ፤ሙሉ ቀን ነበር አውሮጵላን ማረፊያ የዋልኩት ።»

ሁሴን ሃምዲ ይሄ ሁሉ የደረሰበት ስሙ ለቱኒዝያ ደህንነት ያሰጋሉ የሚባሉ ሰዎች ስም ዝርዝር በተያዘበት መዝገብ ላይ በመስፈሩ ነበር ።ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግን ስሙ ከመዝገቡ ውስጥ ተሰርዟል። በንፅጽር ሲታይ ሃምዲ የከፋ ችግር አልደረሰበትም ።የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚናገሩት በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ ጠንካራ ፍተሻዎች ይደረጋሉ ። ከዚሁ ጋርም ንጹሃን ሰዎች በየጊዜው ለእስር ይዳረጋሉ ። በእስር ቤቶችም አለአግባብ እንደሚያዙ ነው የሚነገረው ። ከዚህ በመነሳትም «ሽብርን እንቃወማለን » « ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንፈልጋለን »የሚለውን ዘመቻ የሚያካሂዱ የመብት ተሟጋቾች በአሁኑ ጊዜ አሸባሪነትን መታገልና ሰብዓዊ መብትን ማክበር በአንድ ላይ መሄድ የሚችሉ መሆኑን የማስገንዘብ ሙከራ እያደረጉ ነው። የሂዩመን ራይትስ ዋች ባልደረባ ኤማ ግዌላሊ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፀጥታ አስከባሪዎች ከባለሥልጣናት እና ከሠራተኛ ማህበራት እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ውይይት እንዲካሄድ ይፈልጋሉ ።

Sechs Tote bei Anti-Terror-Einsatz in Tunesien - Darunter fünf Frauen
ምስል Getty Images/AFP/Fadel Senna

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ