የተማሪዎች ግጭት በአክሱም ዩኒቨርሲቲ
ረቡዕ፣ ግንቦት 28 2011የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ እንደነገሩን የትላንቱ ክስተት መነሻ ምክንያት በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየታየ ካለው ግጭት ጋር የተያያዘ መሆኑ በመግለፅ በድርጊቱ ላይ ተሳተፉ የተባሉ አካላት እንደተያዙና የቀሩትም ለመያዝ እየተሠራ መሆኑን ለዶቼ ቨለ DW ገልፀዋል። የተፈጠረውን ሁከት ለማብረድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እና ፌደራል ፖሊስ ጣልቃ መግባታቸውን የገለፁልን ምክትል ፕሬዝደንቱ በዛሬው ዕለትም ተማሪዎች የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሁከቱ ጉዳት የደረሳቸው ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ሰምተናል። ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ክልል መንግሥት ኮምኒኬሽን ቢሮ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረው ነገር በማውገዝ ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ እንደሚሠራ ገልፅዋል። የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ እንደሚሰጡ ሰምተናል። የትናንቱ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ክስተት "ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት" በማለት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መግለፃቸውን ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ዘጋቢያችን ሚሊዮን በላከልን ዜና አመልክቷል። ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ዛሬ አመሻሹ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጊቱን የፈፀሙትን ወንጀለኞች የክልሉ መንግሥት አድኖ ለሕግ እንደሚያቀርባቸውም ገልጸዋል። ዝርዝሩን የመቀሌው ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ልኮልናል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ