1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦምብ ጥቃትና የመቅዲሹ የፀጥታ ሁኔታ

ዓርብ፣ የካቲት 7 2006

የተመድ መቅዲሹ አዉሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የደረሰ ፍንዳታ ህይወት አጥፍቶ ጉዳት ቢያደርስም የሶማሊያ መንግስት እንዲህ ያለ ጥቃትን ለማስቆም የሚያደርገዉን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥል አስታወቀ። ዋና ፀሐፊ ባን ጊሙን በጥቃቱ ህወታቸዉን ላጡት ቤተሰቦችና ለተጎዱት ሃዘናቸዉን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1B8vq
ምስል Reuters

መቅዲሹ አዉሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደዉ ፈንጂ ዒላማዉ የተመድ ሠራተኞች እና እነሱን ያጀቡ ወታደሮች እንደነበሩ ነዉ ጥቃቱን ያቀነባበረዉ አሸባብ የገለጸዉ። በጥቃቱ እንደአሸባብ ከሆነ የድርጅቱን 3 ሠራተኞች ጨምሮ 16 ነፍስ አጥፍቷል። የመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ኒኮላስ ኬይ ግን ከተሽከርካሪያቸዉ መጎዳት በቀር እንኳን የሞተ የቆሰለም ባልደረባ አለመኖሩን ነዉ ያመለከቱት። እነሱን አጅበዉ ከነበሩ አራት ወታደሮች መጎዳት በቀር። ጋዜጠኛ መሐመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለዉም እሱ ከስፍራዉ ያገኘዉ መረጃም ተመሳሳይ ነዉ፤

«ከአጀቡ መካከል የነበረዉና ከተመድ ተሽከርካሪዎች የአንደኛዉ ሾፋሪ ኢብራሂም ካሪን ማምሻዉን አነጋግሬዉ ነበር። እሱ እንደሚለዉ በተሽከርካሪዉ ዉስጥ የነበሩት የመንግስታቱ ድርጅት ባልደረቦችም ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸዉ። በእርግጥ እዚያዉ አደጋዉ በደረሰበት ስፍራ ሁለት የመንግስት ወታደሮች እና ስድስት ሲቪሎች ህይወታቸዉን አጥተዋል። 15 ሌሎች ተጎድተዋል።»

Somalia Autobombe in der Nähe von Flughafen Mogadishu
ምስል Reuters

የተመድ ጥቃቱን በማዉገዝ ሶማሊያ ይህን መሰሉን የሽብር ጥቃት ለመከላከል የምታደርገዉን ጥረት ማገዙን እንደሚቀጥል መግለፁን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ማርቲን ነስርኪ አስታዉቀዋል። ዘገባዎች እንደሚሉት ከትናንቱ የቦምብ ፍንዳታ አስቀድሞ ሌሊቱን ወደከተማዋ አዳፍኔ ሲተኮስባት አድሯል። ባለፈዉ ሳምንትም እንዲሁ ተመሳሳይ ተኩስ ተሰምቷል። ጋዜጠኛ መሐመድም ይህንኑ ነዉ ያረጋገጠዉ።

«ባለፉት ቀናት እስላማዊ ታጣቂዎቹ ወደከተማዋ የሚወነጭፉት አዳፍኔ ሲስተጋባባት ነበር። እንዲህ ያለ ነገር በሚከሰትበት የፀጥታ ኃይሎች ከተማዋን እየቃኙና እያሰሱ በርካታ ሰዎችን ማሰራቸዉ የተለመደ ነዉ።»

ይህ ሁኔታም ከተማዋ ተመልሳ የጦር መንደር ልትሆን ነዉ የሚል ስጋት እንደፈጠረ ተመልክቷል። የሶማሊያን እና ኤርትራን ጉዳይ የሚከታተል አንድ የመንግስታቱ ድርጅት ቡድን፤ ለመንግስታቱ ድርጅት ባቀረበዉ ዘገባ፤ የፀጥታዉ ምክር ቤት ሀገሪቱ ላይ የተጣለዉን የመሳሪያ እገዳ ማላላቱ ለአጉል ተግባር ዉሏል የሚል ጥርጣሬዉን አሰምቷል። ብድኑ በዘገባዉ፤ ባለስልጣናት የሚገዙት የጦር መሳሪያ አሸባብ እጅ ገብቷል ብሎ እንደሚያምን አመልክቷል። በተጨማሪም ዘገባዉ ከዩጋንዳና ጅቡቲ ወደሶማሊያ ከሚገባዉ የጦር መሳሪያ ሌላ ከባህረ ሰላጤዉ የአረብ ሀገርም በአዉሮፕላን መሳሪያ ወደሶማሊያ መግባቱን የሚያሳይ መረጃ እንዳለዉ ዘርዝሯል። ሶማሊያ የሚገባዉ መሳሪያም ከመንግስት ሠራዊት ጎን ለጎን የሠራዊቱ አካል ላልሆኑ የጎሳ ሚሊሺያዎችም እንደሚታደል እንደደረሰበት ገልጿል። ጋዜጠኛ መሐመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለዉም ከሆነ ዛሬ ዛሬ በድብቅ ካልሆነ በቀር እንደበፊቱ ባካራ ገበያም ሆነ በየጎዳናዉ መቅዲሹ ዉስጥ የጦር መሳሪያ መሸጡ ቀርቷል።

Somalia tödlicher Autobombenanschlag auf Hotel in Mogadischu
ምስል Reuters

«ከተማዉ ዉስጥ ወዲህ ወዲያ ማለትን አዘወትራለሁ፤ ነገር ግን እንዲህ ያለዉን ነገር የትም ቦታ አልተመለከትኩም። መንግስትም ቢሆን በይፋ ስለዚህ ያለዉ ነገር የለም። እርግጥ ነዉ ከዓመት ወይም ከወራት በፊት ባካራ ላይ ይሸጥ ነበር። አሁን ቢኖር እኳ ምናልባት በድብቅ ሊሆን ይችላል። በይፋ ግን የሚደረግ ሽያጭ የለም።»

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሶማሊያን መንግስት ከሚደግፉት ሃገራት አንዷ የሆነችዉ ቱርክ ለመንግስት የምትሰጠዉን የቀጥታ በጀት ድጋፍ ካለፈዉ የጎርጎሪሳዊ ዘመን ማለትም 2013 ማለቂያ አንስቶ ማቆሟን አስታዉቃለች። ከፍተኛ የተባለዉን ድጋፍ ቱርክ መስጠት የጀመረችዉ ከሶስት ዓመታት በፊት ሶማሊያ በድርቅ በተጎዳችበት ወቅት ነዉ። በርካታ ምዕራባዉያን የመቅዲሹን መንግስት በበጀት አይደግፉም፤ አንካራ ግን እስካሁን ስንት እንደለገሰች ባይገለፅም በጥሬዉ ስትሰጥ እንደነበር ነዉ የተገለጸዉ። የቱርክ የዉጭ ጉዳይ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደገለፁትም ዳግም እቀጥል እንደሁ ለጊዜዉ ማረጋገጥ ባይችሉም፤ ገንዘቡ ካለፈዉ ታህሳስ ወር ማለቂያ አንስቶ ተቋርጧል። ምክንያቱ በዉል ባይገለፅም ዘገባዎች እንደሚሉት በሙስና ግፊት የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ኃላፊ ሥራ ለመልቀቅ መገደዳቸዉን መግለፃቸዉ ምዕራባዉያን ደጋፊዎችን ቅር ሳያሰኝ አልቀረም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ