የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቃዮች ሰሚ ያጣ እሮሮ
ማክሰኞ፣ ጥር 18 2013ማስታወቂያ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እና ዘር ተኮር ጥቃት መንግሥት የክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ካላደረገ አይቆምም ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩና ቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው የመተከል ዞን ተወላጆች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። የሃይማኖት መሪዎችና መገናኛ ብዙኃን እየደረሰ ያለውን ግፍ በቸልታ እየተመለከቱት ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ እየተላኩ ያሉ የሰብአዊ ድጋፎችም አንድም በፀጥታ ሥጋት በፍጥነት እየደረሱ አይደለም፣ በሌላም በኩል ግብአቶቹን አዘጋጅቶ ለመጠቀም የመብራትና የውኃ እጥረት ፈተና ሆኗል ብለዋል። በመንግሥት ላይ ያጣነውን እምነት የሃይማኖት አባቶች እና የመገናኛ ብዙኃንም ነፍገውናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ይኽ ሁሉ ግፍ እና ጭካኔ በመቶ ሺህዎችን ሲበላ የታሉ ሲሉም ምሬታቸውን ገልጠዋል። በቤንሻንጉል ክልል የብሔር ጥቃት ኼድ መለስ ቢልም በተደራጀ መልኩ እና ስውር ተልዕኮ እንዳለው በሚያሳይ መልኩ ተጠናክሮ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሲከናወንም ስድስት ወር ሊሆነው እንደሆነ ነዋሪዎች አቤት ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ