1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአ.አ የቤት ተከራዮች፤ የጠ/ሚ ዐብይ የሩዋንና ጉብኝት፤ ከ 7 ሺህ ት/ቤት መዉደም

ዓርብ፣ ነሐሴ 28 2013

«ዉሳኔዉ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የቤት ባለቤቶች ጉዳይ በጣም ፍትህ አልባ ነው።  ኩሽና የምትመስል ቤት አንድ ሺ ብር እያሉ በዚ ላይ የውኃ ክፈሉ የመብራት ክፈሉ እያሉ ደሀውን ያስጨንቃሉ።  ምስኪኑ ህዝብ የት ሄዶ ይኑር ነዉ የምትሉት !? ....አከራዮች ሞት እንዳለ አትርሱ»

https://p.dw.com/p/3zq1G
Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በዚህ ዝግጅት ሦስት ርዕሶችን መርጠናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በቀጣዮቹ ሦስት ወራቶች የቤት ኪራይ ዋጋን መጨመርንም ሆነ ተከራይን ቤት ማስለቀቅ የሚከለክል ደንብ ተግባራዊ ማድረጉን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝትን፤ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደዉ ጦርነት ከ 7000 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል መባሉን ይመለከታሉ።  

በኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባስ ብሎ እየተስተዋለ ለመጣው የኑሮ ውድነት የተለያዩ ምክኒያቶች ይሰጣሉ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ በየአከባቢው የሚፈጥሩት ግጭቶች የሚያስከትሏቸው አለመረጋጋቶች ተጠቃሾች ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት የቤት ኪራይ ዋጋን መጨመርንም ሆነ ተከራይን ቤት ማስለቀቅ የሚከለክል ደንብ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ሰሞኑን ጎልተው ከወጡ ክንዉኖች አንዱ ነዉ።  የአዲስ አበባ አስተዳደር ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ደረስኩባቸው ባላቸው የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱንም አስታውቋል።

Symbolbild Jobsuche Social Media
ምስል Fotolia/Photo-K

ፋሲካ ቦልካ የተሰኙ የፌስቡክ ተከታታይ፤ «ህዝባችንን ከስግብግቦች ለመታደግ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል ይህ ቀዳሚ መሆኑ ይበል ያሰኛል። ግን እጅግ ብዙ ተግባራት ይቀራሉ» ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

«መንግስት ነጻ ገበያ ፖሊሲ አራምዳለሁ ካለ በኋላ ጨምሩ አትጨምሩ ማለት አይጠበቅበትም፤ የሚሉት ሮብሶን መርጋሳ ናቸዉ።  ይልቁንም ይላሉ በመቀጠል ፤ በአግባቡ ግብሩን ሰብስቦ በየሜዳው 10/90, 20/80, 40/60 ተብሎ በወጉ ያልተሰሩትና ቆመው ቀናቸውን እየቆጠሩ ያሉ ኮንደሚኒየም ቤቶችን፤ በፍጥነት አጠናቆ ለባለ እድለኞች ያድል፤ ሲሉ ሮብሶን መርጋሳ አሳባቸዉን ይቋጫሉ።  

እንደ ሮብሰን መገርሳ ሁሉ፤  ማናማዊት የሰዉዘር  የተባሉ የፊስቡክ ተጠቃሚ አስተያየታቸዉን ዘርዘር አድርገዉ አስቀምጠዋል።« የቤት ኪራይ ለ3 ወራት አለመጨመር የሚለዉ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። ከዚህ ይልቅ መስተዳደሩ ያላያቸዉ አማራጮች አሉ። ለምሳሌ ከ 70 ቢልየን ብር በላይ ወጪ ወጥቶባቸዉ ግንባታቸዉ ከፊል ተጠናቀዉ በመሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ሰዉ አልባ ሆነዉ የተቀመጡ ከ90 ሺህ በላይ  የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች፤ በቦሌ አራብሳ ሳይት እና በኮዬ ፈጬ ሳይት ይገኛሉ። እነኝህን ቤቶች መሰረተ ልማቱን በቀላል ወጪ እና በጊዚያዊነት መፍትሄ ትኩረት ተሰጥቶት ሰዉ እንዲገባበት ቢደረግ ከ200 ሺ በላይ የነዋሪዎችን ችግር ከመቅረፉም በላይ እየታየ ያለዉን የቤት ኪራይ ጭማሪ ሁነኛ ማስታገሻ ነበር። ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ እንደማይፈልጉ በተለያየ አጋጣሚ ለመታዘብ ችለናል ።ለዚህ ዋነኛዉ ምክንያት በዚህ ቢሮክራሲ በበዛበት አሰራር የግል ጥቅማቸዉ የሚነካ አመራሮች እንዳሉበት ለመታዘብ ችለናል። ስለዚህ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ክልከላ ገደብ ለማስመሰል ካልሆነ በቀር፤ መፍትሄ አያመጣም። መፍትሄዉ ለሁሉም ሰዉ ግልጽ ነዉ። አቅርቦት መጨመር ነዉ »፤ ብለዋል፡፡

ዳግማዊት ተሰማ የተባሉ የማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ «ያኔ ደርግ 7 እንቁላልን በስሙኒ ሽጡ ብሎ አውጆ ነበር፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ።  ደርግ 7 እንቁላልን በስሙኒ ሽጡ ብሎ አውጆ ነበር። ይህን የሰማ ሸማች ገበያ ወጥቶ በስሙኒ (25 ሳንቲም) ሊገዛ ሲጠይቅ፣ ነጋዴው ምን ቢመልስለት ጥሩ ነው? አይ እሱ እንቁላል የለንም። የደርግ ዶሮ ስታሽካካ ብቅ በል አለው። የአሁኑ አዋጅ ይህን ነው ያስታወሰኝ። ለችግራችን ትክክለኛ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ዙሪያ ገባውን እንዳክራለን፤» ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

አቤኔዘር ካሳ ደግሞ ፤ ዉሳኔዉ ጥሩ ነዉ ሲሉ ነዉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት። «ጥሩ ነው ክልከላው ቀጣይነት ቢኖረው በተለይ የቤትኪራይ ቋሚ ቢሆን አሪፍ ነው።  በየጊዜው የሚጨመርብን የቤትኪራይ በፍፁም ከምናገኘው የወር ደመወዝ ጋር የማይገናኝ ነው። ናላችን ዞሯል። በቤት ኪራይ በተለይ እኛ የመንግስት ሰራተኞች መኖር አልቻልንም። ደመወዛችን አይጨምርም። ነገሮች በየጊዜው ጣራ የነካ ጭማሪ ይጨምራሉ። በእውነቱ ነጋዴዋች በጣም ጨክነውብናል። በዚህ ከቀጠለ ጎዳና ላይ መውጣታችን የማይቀር ነው። በዚህም መንግስት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። በተለይ የአዲስአበባ የመንግስት ሰራተኛ ተጨቁኖ ነው ያለው። የቤት ክራይ ዋጋ ምደባ ሊሰጠው ይገባል። የዘይትና ስኳር ድጋፍ ያስፈልገዋል። ጅምሩ ጥሩ ነው። በሀሳባችሁ በርቱ። ብቻ ችግራችን ተወርቶ አያልቅም ዝም ይሻላል፤» ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ሸዋዬ ሽዋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «እባካችሁ ተዉን ይላሉ በአስተያየታቸዉ መጀመርያ። ባትነካኩን ይሻላል ነበር።  ከ90ቀን በኋላ አከራዮቻችን እልሃቸውን ነው የሚወጡብን። ከዚህ በፊት 350 ብር የነበረውን ዘይት ነካክታችሁ ይኸው 700 ብር አስገቡት። ዘላቂ መፍትሄ ላታመጡ አትነካኩን እባካችሁ »ሲሉ ተማፅኖ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። «በ3ወራት ውስጥ በካሬ ተመን ማውጣት ይኖርባችኋል። ካልሆነ ግን፤ ሆን ብላችሁ ደኃውን ከከተማ ለማስወጣትና አከራዮች ቀጣይ እንዳሰኛቸው እንዲጨምሩ ለማነሳሳት የተወሰነ ውሳኔ ይመስላል፤» ያሉት ደግሞ፤ ዳመነ ሰመያዩ የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።

ወሎ ቤተ-አማራ የተሰኙ የፌስቡክ ተከታታይ« ጊዜያዊ ገደብ ከመጣል ይልቅ መንግስት የቤት ኪራይ ላይ የካሬ ተመን አውቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖረው ቢሰራ እንጂ የተሻለ የሚሆነው፤ 3ወር ኪራይ ጭማሪ እገዳ ጥሎ 3ወሩ ካለቀ በኋላ፤ የለመዱትን እጥፍ ጭማሪ ማድረጋቸው የማይቀር ነው፤ »የሚል አስተያየታቸዉን ነዉ ያስቀመጡት።

ሩታ አርሴናል የተባሉ የፊስቡክ ተጠቃሚ አስተያየታቸዉን በቀጥታ ለአከራዮች ያስቀመጡ ይመስላል። «ዉሳኔዉ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የቤት ባለቤቶች ጉዳይ በጣም ፍትህ አልባ ነው።  ኩሽና የምትመስል ቤት አንድ ሺ ብር እያሉ በዚ ላይ የውኃ ክፈሉ የመብራት ክፈሉ እያሉ ደሀውን ያስጨንቃሉ።  ምስኪኑ ህዝብ የት ሄዶ ይኑር ነዉ የምትሉት !? ....አከራዮች ሞት እንዳለ አትርሱ»ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሳምንቱ መጀመርያ በርዋንዳ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አካሂደዋል።  ጠቅላይ ምኒስትሩ ሩዋንዳ  ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ጽፈዋል ። ዐቢይ ወደ ሩዋንዳ ከማቅናቸው በፊት በኢንቴቤ ቤተ-መንግሥት ከዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዉም ነበር። እጃጆ ኮቴ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ፤ «ጥሩ እንዲህ አፍሪካዊን ወዳጅነትን ማጠናከር ወሳኝ ነው። በተለይ በዚህ ግዜ አሰፈለጊ ግዜውን የጠበቀ ጉብኝት ነው »ሲሉ የዐቢይን የምስራቅ አፍሪቃ ጉብኝት አወድሰዋል።

ለም ኢትዮጵያ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤« እኚህ የሩዋንዳ ፕሬዜዳንት ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡና የዘር ክፍፍል አደገኛነትን ለኢትዮጵያውያን ቢነግሩ ጥሩ ነበር:: እኛ አጥተነው ሳይሆን ከሌላ ሰው ስንሰማ ትንሽ የሚክብደን ከሆነ ብዬ ነው።» ሌላው ይላሉ በመቀጠል «ይቺን የወያኔ ባንዲራ አስወግዳችሁ የመላው ኢትዮጵያ ንብረት የሆነውን የአባይን ግድብ መሃል ሰንደቅዓላማ ላይ አድርጉልን»፤ብለዋል።

Symbolbild Deutsche Sprache beim Chatten
ምስል picture-alliance/dpa/I. Wagner

ሃዋ ሃዋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ «ህዝባችን እያለቀ አንተ ብዙ ቦታ ጉብኘት ትሄዳለህ ግን ለምንድን ነዉ የወሎ ህዝብ የሚያልቀዉ። ስራህን እና ሃላፊነትህን እርሳህው እኮ አብይ አህመድ አላህን ፍራ ህዝባችን አለቀ ዝም አትበል መላ ፍጥር »ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

አብቹ አይዞን ለባንዳው እራስ ምታት ለኢትዮጵያውያን ደግሞ አንጀት አርስ የሆኑ ተግባራትን እየሰራህ ነው።  የኢትዮጵያ አምላክ ከአንተ ጋር ይሁን ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት አማረ አያና ናቸዉ። ታሪክ ሰዉ የተባሉ ተከታታይ ደግሞ ፤ «እኛ የናፈቀን ወሬ ጁን ታውን ጨረስን እንጂ አብይ ጉብኝት አይደለም ።» 

ኢትዮጵያን እያመሰ በሚገኘው የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ጦርነት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሞተዋል። ብዙዎችም የአካል ጉዳት ሰለባዎች ሆነዋል። በጦርነቱ ከደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ባለፈ የሐብትና ንብረት ውድመትም ተከስቷል። የመንግሥትና የግል ተቋማት መዉደማቸዉ ታይቷል። የትምህርት ሚኒስቴር እንደሚለው በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ትምህርት ቤቶችን ማውደም ኢትዮጵያ የምትከተለውን ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶቿን ያልተቀበለ የትምህርት ሥርዓት ውጤት ነውም ሲሉ አስተያየታቸዉን የሰጡ ጥቂቶች አይደሉም።  

አህመድ ግራን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤«የጦርነት ውጤቱ ይህ ነው።  አሁንም በጦርነት እንቀጥላለን ካልን ውድመቱም እየጨመረ ይመጣል። ሰለዚህ መፍትሄው ጦርነቱን መቆም እና በጠረጴዛ ዙሪያ ችግራችንን መፈታት አለበን ብለዋል። እማተኩር የማርያም ልጅ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ «የዚህ ሁሉ ትምህርት ቤት ወድመት ጀንታው ሳይሆን ተጠያቂው መንግስት ነው።  ምክንያቱም አጥፊዎችን እሽሩሩ እያለ እርምጃ አለመወሰዱ ነው፤ ለዚህ ሁሉ ጥፋት የበቃዉ። አሁንም እሽሩሩ እያለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። የአማራ እና የአፋር ክልል ልጆች እንደይወጡ እንደይማሩ ተደርጎ የተሰራ ሴራ ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን ይደመድማሉ።

ጌታቸዉ ሞገሴ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤« ከዚህ የበለጠ ውድመትና ኪሳራ ሳይደርስ መንግስትና ህዝብ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል። ይሄ አሸባሪ ቡድን እድሜ በተሰጠው ቁጥር በዚች ድሃ ሀገር ላይ ገና ብዙ ነገር እያወደመ ይቀጥላል ፣ ለዚች ሀገር ፈጣን እድገትና ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ በአጭር ቀን ውስጥ ይሄን ቡድን ከነተከታዮቹ ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ማስዎገድ ያስፈልጋል »ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት ደግሞ ያሬድ ፍስሃ ናቸዉ።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

በድሩ መሐመድ ደግሞ ይህ ሁሉ ዉድመት እንደቀላል መታየት የለበትም ይላሉ አስተያየታቸዉን ሲጀምሩ «ይህ ውድመት በመረጃ የተደገፈ ሆኖ ለሕዝብ ተደራሽ መደረግ አለበት። ዘገባዉ አልገባኝም ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት መብራቱ ደረሰ፤ «እና ጦርነት ተጨማሪ ትምህርት ቤት ይገነባልናል ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር?» ሲሉ ጠይቀዋል።

አድማጮች አሁን አሁን በማኅበራዊ  መገናኛ ዘዴዎች ላይ ገንቢ ወይም ስርዓቱን የጠበቀ ነቀፊታ አስተያየቶችን ማግኘት እጅግ ከብዶአል። ዘለፋ ስድብ ይበዛዋል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሃሳብን ለማንሸራሸር መረጃ ለመለዋወጥ፤ ብሎም ገንቢ አስተያየቶች የሚሰጡበት ቢሆን ማኅበረሰብ ሊማርባቸዉ ይችላል የሚል አስተያየት አለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ