1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ

እሑድ፣ መስከረም 4 2012

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚገኙ አድባራት ገዳማት በቤተክርስቲያኗ እና በአገልጋዮች ላይ የሚፈፀመው ግፍና በደል ይብቃ በሚል በተለያዩ ከተሞች ዛሬ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3PdqA
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ

በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻና በሌሎች ከተሞች ቤተክርስቲያኗን ከጥፋት ለመታደግ የሚያመለክቱ፣ አንድነቷን የሚያጠናክሩና ለአገር የዋለችውን አስተዋፅኦ የሚያሳዩ መፈክሮችን እያሰሙ ማርፈዳቸውን በየሰልፉ የተገኙ የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ በስልክ ገልፀዋል፡፡
በጎንደር ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የ44ቱም አቢያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና እጅግ  ቁጥራቸው  የበዛ  ምእመናን ነጭ ልብሳቸውን ለብሰውና ቀሳውስትና ደቀመዛሙርት የዜማና የምስጋና መሳሪዎችን ይዘው ቅሬታቸውን ለመንግስት ማሰማታቸውን የሰልፉ አስተባባሪ ከሆኑት መካከል ቀሲስ ሰለሞን ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
በደብረታቦር ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተገኙ አንድ የሰልፉ ተካፋይ እንዳሉት አንድ የሆነውን ሲኖዶስ እንደገና ለመከፋፈል የሚደረገውን ተንኮልና  አንዳንድ “የውጭ አጥኝ ነኝ” ባዮች ቤተክርስቲኒቱን ለመከፋፈል የሚያደርጉትን ሴራ ለማክሸፍ የተደረገ ሰልፍ መካሄዱን አብራርተዋል፡፡
የኮምቦልቻ ወረዳ ቤተክርስቲያናት አስተዳዳሪ መላከ ህይወት ቆስሞስ አባ ተክለማሪያም በበኩላቸው ከ1983 ዓ ም ወዲህ በቤተክርስቲያናትና በአገልጋዮቻቸው ላይ ግፍ እየበዛና እየከፋ መምጣቱን ጠቁመው ይህን ለመቃወም ምዕመናን ሰልፍ ወጥተው ድርጊቱ እንዲቆም መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
14 አድባራትና ገዳማት የሚገኙባት ደሴ ከተማ ምዕመናንም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ገላው እንደገለፁት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አድሎ እየደረሰባት ነው፡፡

አለምነው መኮንን

ልደት አበበ