1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበለጸጉ አገሮች፤ የሕዝብ ቁጥር መቀነስና የኤኮኖሚ መዘዙ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5 1998
https://p.dw.com/p/E0dr

የአውሮፓ የምጣኔ-ሐብት ጠበብትና ፖለቲከኞች ለአሠርተ-ዓመታት ሲነጋገሩ የቆዩት የዓለም ሕዝብን ቁጥር መናር እንዴት ለመቋቋም እንደሚቻል እንጂ በዚህ በተጻራሪው ሁኔታ አልነበረም። ዛሬ ጀርመንን ጨምሮ በበለጸጉት አገሮች የሚወለደው ሕጻን ጥቂት ነው። በአንጻሩ ያረጀውና የሚሞተው ሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ነው የሚታየው። ይህ ደግሞ በሥራ ገበያው፣ በኤኮኖሚው ዕድገትና በማሕበራዊው ዋስትና ሥርዓት፤ በአጠቃላይ በሕብረተሰቡ መዋቅራዊ ይዞታ ላይ የሚኖረው ተጽልኖ ቀላል አይሆንም።

ወደፊት ዛሬ በየትምህርት ቤቱ የሚሰማ የሕጻናት ጫጫታ እየቀነሰ መሄዱ ላይቀር ነው? ጉዳዩ ሁል-አቀፍና የረጅም ጊዜ መፍትሄን የሚሻ ይመስላል። የሕብረተሰቡ ቁጥር አቆልቋይ ሂደት ግን በአንዴ ተገትቶ ወዲያው የሚለወጥ እንደማይሆን ከአሁኑ ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከጀርመን 82 ሚሊዮን ሕዝብ ከ 70 በመቶ የሚበልጠው ተጣሪ ወይም ወደዚያው የተጠጋ ሆኖ ነው የሚገኘው። ሠርቶ የማሕበራዊውን ዋስትና ስርዓት የሚደጉመውና ለመንግሥት ግብር የሚከፍለው የሕብረተሰቡን ሲሦ እንኳ አይሞላም።
ይህ ቀላል ችግር አይደለም። አጠቃላዩን የሕብረተሰብ መዋቅራዊ ይዞታ ከሥር መሠረቱ እየለወጠ ያለ ሁኔታ መሆኑ ከመቼውም በላይ በግልጽ መታየት መያዙ አልቀረም። እንደዛሬው ያለው ትውልድ የሕዝቡን ቁጥር ቢቀር ጠብቆ ለማቆየት በሚያበቃ መጠል ልጅ እስካልወለደ ድረስ ሕብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ እየመነመነ መሄዱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም ገና ያልተወለዱት ወደፊት ለዕናትነት መብቃት ያለባቸው ሴት ልጆች ይጎላሉና።

ለነገሩ በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት የዓለም ሕዝብ ቁጥር ባለፉት 48 ዓመታት ከ 2.5 ወደ 6 ሚሊያርድ ከፍ ብሏል። ግን ዕድገቱ በበለጸጉት አገሮች ሣይሆን በታዳጊው ዓለም ነው። ጀርመንን ብንወስድ በ 50ኛና በ 60ኛዎቹ ዓመታት አንዲት ዕናት ከሁለት በላይ ልጆች ትወልድ ነበር። ከዚያ በኋላ የወሊድ መቆጣጠሪያው ክኒን ይመጣና አሃዙን ከሁለት በታች ያደርገዋል። ይህ የአዲስ ትውልድ መቀነስ ደግሞ ዛሬ በሠርቶ አደሩ የጋራ አስተዋጽኦ ላይ የተመሠረተውን የማሕበራዊ ዋስትና ሥርዓት ታላቅ ፈተና ላይ ሊጥለው በቅቷል።

ተጧሪውን ማን ሰርቶ ይደጉመው? ይህ ዛሬ መላ የጠፋለት አሳሳቢ ችግር ነው።
በጀርመን በተለይ የወሊዱ መጠን በጣሙን በቀነሰበትና ከውሕደቱ በኋላ ብዙዎች ወደ ምዕራብ በፈለሱበት በምሥራቁ ክፍል ችግሩ ከአሁኑ ጠንከር ብሎ መታየት ይዟል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍላት የመጤዎች መታከል ጉዳዩን ባያለዝበው ኖር እንዲያውም ዛሬውኑ ከበድ ያለ ሁኔታን ባስከተለ ነበር።

ቁጥሩ እየመነመነ የሚሄድ ሕዝብ በመሠረቱ መንግሥትን ከብዙ ወጪ የሚገላግል ነው የሚመስለው። ግን ሃቁ ይህ አይደለም። ብዙ የማጣጣም ለውጥን፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰፊ ወጪን የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ የመጠጥ ውሃና የቆሻሻ ማጣሪያ ዘዴን በሕዝቡ ቁጥር መጠን አሳንሶ በአዲስ መልክ ማቀናጀት ግድ ይሆናል። ከመጠን በላይ የሆነ የመጠት ውሃ ማከማቻ ውስጥ ቢቀመጥ የሚበከል ነው የሚሆነው። የቆሻሻ መተላለፊያዎችም በዝገት ሊበላሹ ይችላሉ።
ለዚህም ነው ከሕዝቡ መጠን ተጣጥመው መሰተካከል ያለባቸው። የጀርመን የገንዘብ ተቋም ዶቼ ባንክ የሚገምተው ይህን መሰሉ የውሃ መተላለፊያ ዘዴ ጥገና ብቻ 45 ሚሊያርድ ኤውሮ ወጪን መጠየቁ እንደማይቀር ነው። የሕዝብ ቁጥር ማቆልቆሉ ሂደት በጣም የተፋጠነ የሆነባት የምሥራቃዊቱ ሣክሶኒያ ፌደራል ክፍለ-ሐገር አስተዳዳሪ ጌኦርግ ሚልብራት ችግሩ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ባይ ናቸው።

“ችግሩ አፍጦ እስከሚመጣ ድረስ ረጅም ጊዜ መጠበቅ የለብንም። እንደዚያ ከሆነ በቀላሉ መፍትሄ ለማግኘት ጊዜው የሚዘገይ ነው የሚሆነው። የመዋቅራዊው ለውጥ መሸጋሸግ ክምር መሰብሰብ እንጂ ለዘለቄታው ችግሩን ማስወገድ ማለት አይደለም። የለውጡ ሂደት ከፖለቲካው ቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን መጠንቀቅም አለብን” ብለዋል የሣክሶኒያው አስተዳዳሪ!

የሕዝብ ቁጥር መቀነስ በሥራ ገበያ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። የመጀመሪያው የጥቂት ዓመታት ሂደት የሥራ-አጡን ቁጥር የሚቀንስ በመሆኑ በጎ ገጽታው ነው። በሌላ አነጋገር ኩባንያዎች ወጣትና በሙያ የሠለጠነ ሙያተኛ የመቅጠራቸው ዕድል የላቀ ነው የሚሆነው። አዋቂዎች የሚናገሩት በዚህ መንገድ የሥራ አጡ ቁጥር እስከ 2020 ዓ.ም. በጀርመን ምዕራብና ምሥራቅ በአጠቃላይ ከዛሬው አምሥት ሚሊዮን መጠኑ በግማሽ ሊያቆለቁል እንደሚችል ነው።

ሆኖም በሌላ በኩል የጀርመን የሥራ ተቋም የሙያና የገበያ ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ሃላፊ ኡልሪሽ ቫልቫይ ለየት ያለ አመለካከት አላቸው። በርሳቸው አስተሳሰብ የሥራ ገበያው ችግር በሕዝብ ቁጥር መቀነስ የተነሣ ብቻ የሚለወጥ አይሆንም። ስለዚህም የሥራ መስኮችን የመክፈት የፖለቲካ ግፊት ያስፈልገዋል። ልዩነት ቢኖር በሚቀጥሉት ዓመታት የሥራ ጉልበት አቅርቦት የማይጨምር መሆኑ ነው። ባለፈው ጊዜ ግን የሥራ ጉልበት እያደገ መጥቷል። ግን ቀጠራው በዚያው መጠል ሊራመድ አልቻለም።

ቫልቫይ እንደሚሉት በሚቀጥሉት ዓመታት የሥራ ጉልበት አቅርቦት ቢቀር አስከ 2015 ባለበት ጸንቶ የሚቆይ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚያስወግድ ወይም እንደሚያጠበው አንድና ሁለት የለውም። ይሁንና የመጪዎቹ ዓመታት አመቺ የሥራ ገበያ ሁኔታ በሚቀጥሉት ሶሥትና አራት አሠርተ-ዓመታት ተለውጦ ዕውነተኛ ችግር መፍጠሩ የማይቀር ነው። የፌደራላዊ የሥራ ተቋም ኢንስቲቲቱት የምርምር ውጤት ዕውን ከሆነ የጀርመን ሕዝብ ቁጥር እስከ 2050 ዓ.ም. በ 12 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱ አይቀርም።

ታዲያ የአሥር ሚሊዮን ያህል ሠርቶ-አደር መቀነስ ለመንግሥት አሥር ሚሊዮን ግብር ከፋይ፣ የጡረታ ሥርዓት ደጓሚና ለኤኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ የሆነ ምርት አንሺን ማጣት ማለት ነው። ከዚህ አንጻር ጀርመን መቋቋም ያለባት የሕዝብ ቁጥር መቀነስንና የሕብረተሰብን ማርጀት ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ የኤኮኖሚ ምንማኔን ጭምር መታገሉ ግድ ነው። ይህም ሆኖ ግን የሥራ ጉልበት መመንመን የሚያስከትለውን ችግር መታገል የሚቻልባቸው ዘዴዎች እንደማይጠፉ ነው ቫልቫይ የሚናገሩት።

“የሥራ ገበያን በተመለከተ ሂደቱን የሚያረጋጋ ተጠባባቂ ሃይል አለ ለማለት ይቻላል። ይህን በተመለከተ በተለይ በብዛት በሥራ ተሰማርተው የማይገኙትን አንጋፋ ዜጎችን መጥቀስ ይቻላል። ሥራና የቤተሰብ እንክብካቤን ለማጣጣም አመቺው ሁኔታ ከተፈጥረ የቤት ሴቶችም አሉ። መጤዎችን በአቅድ ወደ አገር ማስገባቱም ሌላው ልንነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ጀርመን በዓለም ላይ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ፉክክር ማራኪ መሆን ይኖርባታል” ባይ ናቸው።

አንጋፋ ዜጎችን ለሥራ መሳብ፣ ለሴቶች የሥራና የቤተሰብ ይዞታ ሁኔታን ማቃለል፣ መጤዎች አቅድ ባለው መንገድ አገር የሚገቡበትን ሁኔታ ማራመድ፤ የጀርመን ፖለቲከኞች የመጪዎቹ ዓመታት የሕዝብ ቁጥር መቀነስ የሚያስከትለውን ችግር ለማለዘብ ለእነዚህ ሶሥት ጉዳዮች ከአሁኑ ትኩረት መስጠት ጀምረዋል። በሌላ በኩል የመጤዎች መታከል ብቻውን ችግሩን ሊፈታ እንደማይችል የሣክሶኒያው አስተዳዳሪ የጌኦርግ ሚልብራት ዕምነት ነው።

“እስካሁን ለረጅም ጊዜ የነበረውን ሂደት ከተመለከትን የመጤዎች ጉዳይ ገና በሚገባ ግልጽ ያልሆነ ነገር ነው። እርግጥ በመጤዎች መግባት ለውጥ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ቢቀር በወቅቱ ችግሩን ከማለዘብ አልፎ መፍትሄ ሊሆን መብቃቱ አይታየኝም።” ይላሉ።

መረጃዎችን ለመጠቃቀስ ያህል ጀርመን፤ ማለት ምዕራብ ጀርመን ከ 1965 እስከ ውሕደቱ እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ በየሺህ ነዋሪው በአማካይ ሶሥት መጤዎችን ስትቀበል ቆይታለች። ይህም በዓለም አቀፍ መስፈርት ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ አሃዝ መሆኑ ነው። በሌላ በኩል የቅርብ ጥናቶች የሚያመለክቱት በሚቀጥሉት ዓመታት በያመቱ መቶ ሺህ ገደማ የሚጠጉ የውጭ ዜጎች ወደ ጀርመን እንደሚመጡ ነው።
ይሁንና መንግሥት የሥራ ሃይል ማቆልቆልን ለመቋቋም ከሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ጋር ተጣምረው የጎደለውን እንዲያጣጡ በያመቱ 300 ሺህ መጤዎች የግድ ያስፈልጋሉ። ታዲያ ይህን ያህል የሥራ ሃይል ማግኘት ከናካቴው መቻሉ ራሱ አጠያያቂ ነው። እስካሁን እንግዳ ሠራተኞች የሚመጡባቸው ዋነኞቹ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ራሳቸው በከፊል ከጀርመን ባነሰ የወሊድ ድቀት ሁኔታ መገኘታቸው ችግሩን ቀላል አያደርገውም።

በመሆኑም የሥራ ጉልበት እጥረት በሚፈጠርባቸው ቦታዎች አንጋፋ ሙያተኞች ምናልባት ከአሥር ከአሥራ አምሥት ዓመታት በኋላ እንደገና እጅግ ተፈላጊ ሊሆኑ ነው። ዛሬ ያለው ሃቅ ከዚህ የተለየ ነው። አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከሃምሣ በላይ የሆነ ሥራ አጦች ሥራ የማግኘት የረባ ዕድል የላቸውም። ኩባንያዎች ሥራ ያላቸውንም ቀድሞ ወደ ጡረታ ለመሸኘት ሲጋፉ ነው የሚታየው። ከመጪዎቹ ዓመታት ችግር አንጻር ይህ ዘዴ ብልህ መሆኑ ሲበዛ ያጠራጥራል።

በሌላ በኩል በሥራ ገበያ፣ በኤኮኖሚ ዕድገትና በማሕበራዊ ዋስትናው ሥርዓት ላይ የተደቀነውን ችግር ለመቋቋም የሚታሰበው ዕርምጃ ሁሉ የሕዝብ ቁጥር ማቆልቆል ሂደትን ለመግታት ተጽዕኖ ሊኖረው መቻሉ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ አይደለም። ቁልፉ ጉዳይ፤ ይሄውም በሕብረተሰብ ውስጥ ቤተሰብ ምሥረታና ልጆች የመውለድ ፍላጎት እንደገና የሚያንሰራራበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ የሚገባውን ያህል አስፈላጊው ሁኔታ ሲመቻች አይታይም።

ለዘለቄታው ዋናውና ፍቱኑ መፍትሄ ይህ ሲሆን እስካሁን በበለጸገው ሕብረተሰብ ውስጥ ልጆች እንዳይወለዱ ተጽዕኖ የሚያደርጉትን ማሕበራዊ ምክንያቶች በሚገባ ለይቶ ማስቀመጥና ጭብጥ መፍትሄም መሻት ካልተቻለ ሌላው መንገድ በቂ ምላሽ መሆኑ ያጠያይቃል።