1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅርስ ውድመት እና «አይሲሲ» ያሳለፈው ብይን

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት፡ «አይ ሲ ሲ» በጦር ወንጀል ክስ የመሰረተባቸውን አህመድ አል ፋቂ አል ማህዲን በዘጠኝ ዓመት እስራት እንዲቀጡ መበየኑ የሚታወስ ነው። ለወትሮው ዓመታት የሚወስድበት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት፡ በማህዲ ላይ ብይኑን ያስተላለፈው ካሁን ቀደም በታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ነበር።

https://p.dw.com/p/2QmjZ
Ahmad Al Faqi Al Mahdi Prozess Den Haag Strafgerichtshof Weltkulturerbe
ምስል picture-alliance/dpa/P.Post

Fokus Afrika _ A _ 01.10.2016 - MP3-Stereo

 

ይህ ሊሆን የቻለውም በሰሜናዊ ማሊ በተንቀሳቀሰው ፅንፈኛው የአንሳር ዲን አባል የነበሩት የ40 ዓመቱ የቀድሞ መምህር አል ፋቂ አል ማህዲ ከአንድ ወር በፊት ባለፈው ነሀሴ ችሎታቸው በተጀመረበት ጊዜ ጥፋተኝነታቸውን በማመናቸው ምክንያት ነው። የፅንፈኛው የሙስሊሞቹ የአንሳር ዲን ቡድን አባል የነበሩት አል ማህዲ በ 2004 ዓም፡ የክረምቱ ወራት በሰሜናዊትዋ የማሊ ከተማ፡ ቲምቡክቱ ይገኝ የነበሩ ቅርሶች ለወደሙበት ጥቃት ተጠያቂ ናቸው። በዚሁ ጥቃት በተመ የትምህርት፡ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፡ « ዩኔስኮ » በቅርስነት የተመዘገቡ ዘጠኝ ጥንታውያን መካነ መቃብሮች እና የብዙ መቶ ዓመት ዕድሜ የነበረውን አንድ መሰጊድ  አፈራርሰዋል።
የሰለባዎቹ ቅሬታ

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፍርድ ቤቱን ብይን በትልቅ ጉጉት ነበር ሲጠብቀው የቆየው፣ ምክንያቱም፣ ቅርስ ማውደም እንደ ወንጀል ሲቆጠር፣ በአጥቂዎቹ ፅንፈኞቹ ሙስሊሞች ላይ በ« አይ ሲ ሲ» ክስ ሲመሰረትባቸው፣ ተከሳሽም ጥፋተኝነታቸውን በማመን መፀፀታቸውን ሲገልጹ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይሁንና፣ ይኸው ችሎት ለማሊ ሕዝብ ቅድሚያ የያዘ, ጉዳይ እንዳልነበረ በመዲናይቱ ባማኮ የሚገኘው «ፍሪድሪኽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ» የተሰኘው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ኃላፊ ካትያ ሚውለር አስረድተዋል። 
« የአል ፋቂ አል ማህዲ ችሎት ሂደት ትልቅ ትኩረት ነበር ያገኘው። ስለዚሁ ጉዳይ ብዙ ተዘግቦበታል፣ ይሁንና ፣ በቲምቡክቱም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖሩት የማሊ ተወላጆች ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይ አልነበረም። በማሊ ቀውሱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ የተፈፀሙ ሌሎች  ድፍረትን፣ ግድያን፣ ቁም ስቅል ማሳየትን የመሳሰሉት ወንጀሎች ካለቅጣት መታለፋቸውን የማሊ ተወላጆች በፍፁም ሊረዱት አልቻሉም። ጥፋተኞቹን ለፍርድ ማቅረቡ በእርግጥ አዳጋች ነው፣ ምክንያቱም ይህ በነዋሪዎቹ የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል። እና በመሰረታዊ ወንጀል ሂደት ሰበብ በአል ፋቂ አል ማህዲ አንፃር የተካሄደው  የክስ ችሎት እና በርሳቸውም ላይ የተላለፈው ብይን፣ ባጠቃላይ ለሌሎች መቀጣጫ ሊሆን እንደሚችል ካስተላለፈው መልዕክት በስተቀር፣ ማሊ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ አልያዘም። »  
በቲምቡክቱ የባህል ቅርሶች ተመልካች መስሪያ ቤት ተጠሪ አል ቡክሀሪ ቤን ኤሳዩቲም እንደ ካትያ ሚውለር ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት። እርግጥ፣ የጥንታዊቱ ከተማቸው መታወቂያ ለሆነው ቅርስ ውድመት ተጠያቂው በህግ መቀጣታቸው ቢያስደስታቸውም፣ ማሊ ተወላጆች ላይ ከቅርስ ውድመት የከፋ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች አሁንም በከተማይቱ  በነፃ ሲዘዋወሩ ማየታቸው እሳቸውን ብቻ ሳይሆን በመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ላይ የመሳለቅ ያህል መመልከታቸውን ገልጸዋል።
« ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ባካባቢው ለተካሄዱት ሌሎች ወንጀሎችም ተጠያቂ የሆኑትን  ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር አውሎ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት በማሊ ብሔራዊ እርቀ ሰላማ ለሚወርድበት ድርጊት ሁነኛ ድርሻ ማበርከት በቻለ ነበር። »
ተጠያቂዎችን በኃላፊነት መጠየቁ ብዙ ጊዜ ይጠይቃል።
በ 2004 ዓም  በማሊ ፣ በተለይ፣ አሁንም ገና ሙሉ ለሙሉ ባልተረጋጋው ሰሜናዊ የሀገሪቱ ከፊል የሚታየው ተፈጥሮ የነበረው ቀውስ ሰለባዎች በዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የወሰደውን ርምጃ አጥጋቢ ሆኖ አለማግኘታቸውን እንደሚረዱት በኤርላንገን ዩኒቨርሲቲ  ጀርመናዊው የዓለም አቀፍ ወንጀል መቅጫ ጉዳይ ፕሮፌሰር ክርስቶፍ ዛፈርሊንግ ቢገልጹም፣ «አይ ሲ ሲ » ባለፈው ሰኞ ባስተላለፈው ብይን መደሰታቸውን ገልጸዋል። 
«  እርግጥ፣ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለይቶ  የቲምቡክቱ ቅርስ በወደመበት ወንጀል አንፃር ብቻ ችሎት በማካሄዱ  የማሊ ቀውስ ሰለባዎች ቅር መሰኘታቸውን መረዳት ይቻላል።  ይሁን እንጂ፣ በማሊ ለተፈፀሙት ወንጀሎች ሁሉ ተጠያቂ የሚባሉትን ጉዳይ የማየቱ ሂደት ገና አላበቃም።  የቅርስ ውድመትን ወንጀል በተመለከተው የሰሞኑ ችሎት ላይ ተጠርጣሪው ተከሳሽ በመጀመሪያው የችሎት ዕለት ጥፋተኝነታቸውን ያመኑበት ድርጊት ለፍትሑ ሂደት መልካም አጋጣሚ ነበር የፈጠረው። ችሎቱን ቶሎ ማጠናቀቅ አስችሏል። በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አሰራር ሂደት ላይ የታየው ፈጣን ችሎት ነበር። በሀገሪቱ የተፈፀሙትን ወንጀሎች የመመልከቱን ጉዳይ በሚመለከት ከሕዝቡ አሁን የሚጠበቀው  ትዕግሥት ነው። ተጠያቂዎችን በኃላፊነት መጠየቁ ብዙ ጊዜ ይጠይቃል። » 
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች  ድርጅት ፣ «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» በማሊ ቀውሱ ተጠናክሮ በቀጠለባቸው ዓመታት በስብዕና አንፃር ወንጀል የፈፀሙት ሁሉ ባፋጣኝ በሕግ እንዲጠየቁ ማሳሰቡን አላቋረጠም። በአል ፋቂ አል ማህዲ ላይ የተበየነው የዘጠኝ ዓመት የእስራት ቅጣት እርግጥ በሀይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጥቃት የሚጥል ማንኛውም ወገን ወይም ግለሰብ ወደፊት ካለ ቅጣት እንደማይታለፍ ማስጠንቀቂያ ያጎላ ምልክት መሆኑን «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።  የ«አምነስቲ ኢንተርናሽናል» መግለጫ፣ የ«አይ ሲ ሲ»  ብይን ያስተላለፈው አዎንታዊ መልዕክት በመቶዎች የሚቆጠሩ የማሊ ተወላጆች በፅንፈኞቹ ሙስሊሞች መገደላቸውን፣ መደፈራቸውን እና መሰቃየታቸውን ሊያስረሳ እንደማይገባ አሳስቦዋል።  ይህንኑ  ወንጀል በተመለከተ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እስካሁን አንድም የእስር ማዘዣ አለማውጣቱን «አምነስቲ » በጥብቅ ወቅሷል። ከ2004 ዓም ወዲህ በማሊ የተፈፀሙትን ወንጀሎች አካሂደዋል ተብለው የሚጠረጠሩት ግለሰቦች ሁሉ፣ እንዲሁም፣ በወንጀል የተሳተፉ የማሊ መንግሥት ወታደሮች ጭምር በሕግ ክትትል ሊደረግባቸው  እንደሚገባ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ጠይቋል። 
የቅጣት ብይን ማስተላለፍ በቂ አይደለም።
በኤርላንገን ዩኒቨርሲቲ  ጀርመናዊው የዓለም አቀፍ ወንጀል መቅጫ ጉዳይ ፕሮፌሰር ክርስቶፍ ዛፈርሊንግ  በአል ፋቂ አል ማህዲ ላይ የተላለፈውን ብይን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፅንፈኞቹ ሙስሊሞች በሚያካሂዱት የሽብርተኝነት ተግባር አንፃር በጀመረው ትግል ላይ ወሳኝ ርምጃ አድርገው ተመልክተውታል። በማሊ ይኸው ሽብር በተለይ የብዙ ዓመታት ቅርሶችን በማውደሙ ወንጀል ላይ አትኩሮዋል።
ይኸው ፀረ ነፃነት መንፈስ፣ ባህል እና የስነ ጥበብ ስራዎችን የማውደሙ ርምጃ በሕግ ፊት እንደዋዛ እንደማይታለፍ ግልጽ አድርጓል። »
አል ፋቂ አል ማህዲ ዘጠኝ ዓመት እስራት ይቀጡ መባሉን በሙስሊም ሽብርተኝነት አንፃር የተወሰደ ግልፅ ርምጃ አድርገው በተመለከቱት በፕሮፌሰር ዛፈርሊንግ አንፃር የቲምቡክቱ ምክትል ከንቲባ ድራዊ አሴኩ ማይጋ የእስራቱን ቅጣት ተከሳሹ ከፈፀሙት ወንጀል ጋር የሚመጣጠን  እንዳልሆነ ነው የገለጹት።
«  የቲምቡክቱ ተወላጆች ወይም ባጠቃላይ የማሊ ተወላጆች ይህንን ብይን በቂ ሆኖ አላገኙትም።  እርግጥ አል ማህዲ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይሁንና፣ ይህ ፣ ሕዝብ  የፈፀሙትን ዘግናኙን ወንጀላቸውን ሊረሳላቸው ይገባል ማለት አለመሆኑ፣  በግልጽ ሊታወቅ ይገባል። »
ከዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ዓመት የእስራት ቅጣትን ካላንዳች ተቃውሞ እና የይግባኝ ማመልከቻ  እንደሚቀበሉ ፣  ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ውሳኔውን በይፋ ከማሳወቁ በፊት ተናግረው የነበሩት፣  ተከሳሹ አል ፋቂ አል ማህዲ፣ ባለፈው መስከረም 16፣ 2009 ዓም በተላለፈው ብይን  ሳይደሰቱ እንዳልቀሩ በዘ ሄግ ችሎቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ገልጸዋል። 

Logo Amnesty International
Im Krieg zerstörte Kulturstätten Timbuktu
ምስል Getty Images/AFP

 

ክሪስቲነ ሀርየስ/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ