የቀኝ አክራሪዎች እንቅስቃሴ በጀርመን
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 24 2004እጎአከ 2000 እስከ 2007 በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች ፣ 9 የውጭ ዜጎችና የአንድ የጀርመን ፖሊስ በህቡዕ በሚንቀሳቀስ የቀኝ ፅንፈኞች ቡድን ሳይገደሉ እንዳልቀረ ይፋ ከሆነ በኋላ ግድያውንን የሚያጣራ ኮሚቴ ተሰይሞ ምርመራው ቀጥሏል ። በመካከል ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የጀርመን የሃገር ውስጥ ስለላ መስሪያ ቤት ዋና ሃላፊና ሌሎችም ባለሥልጣናት ሥራቸውን ለቀዋል ። መስሪያ ቤቱምበቅርቡ አዲስ ሃላፊ ተሾሞለታል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በጀርመን የቀኝ ፅንፈኞች እንቅስቃሴልዩ ልዩ ገፅታዎች ላይ ያተኩራል ።
ከዛሬ 12 አመት አንስቶ እጎአ እስከ 2007 ዓም ድረስ 9 የውጭ ተወላጆችና አንድ ጀርመናዊ ፖሊስ በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች በነማን እንደተገደሉ እስካለፈው ህዳር ድረስ ሳይታወቅ መቆየቱ እስካሁን አነጋግሮ ያላበቃ ጉዳይ ነው ። ግድያውን ፈፅመዋል የተባሉትን በህቡዕ የሚንቀሳቀሰው የብሔራዊ ሶሻሊስት ቡድን አባላት የጀርመን የሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት በቅርብ አለመከታተሉና በነርሱም ላይ እርምጃ ያለ መውሰዱ ምክንያት 11 አባላት ባሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ እየተጣራ ነው ። የቱርኩ ተወላጅ አበባ ነጋዴው Envore Simsek በህቡዕ በሚንቀሳቀሰው በአሸባሪው ብሔራዊ ሶሻሊስት ቡድን እጎአ በ 2 ሺህ ኑርበርግ ውስጥ ተተኩሶበት የተገደለ የመጀመሪያው ሰለባ ነበር ።
ከዚያም ቡድኑ በቀጠሉት አመታት 7 የቱርክ እንዲሁም አንድ የግሪክ ዜጋ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ውስጥ ገድሏል ። የዚህ ተከታታይ ግድያ የመጨረሻዋና 10 ኛ ሰለባ እጎአ ሃይልብሮን ውስጥ የተገደሉት ጀርመናዊቷ ሴት ፖሊስ ሚሼል ኪዘቬተር ናቸው ። ከነዚህ ግድያዎች በስተጀርባ በውጭ ዜጎች ጥላቻ የተሞሉት 3 ቱ Beate Zschäpe ፣ Uwe Mundlosና Uwe Böhnhardt እንዳሉበት በአጋጣሚ የታወቀው ከ 12 አመት በኋላ በዚህ ዓመት በህዳር ወር ነበር ። የጀርመን ፖለቲከኞችና ህዝቡ የጀርመን የሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት የቡድኑ አባላት ከዓይኑ ስር ሆነው 10 ሰዎች ሲገድሉ እንዴት ላይታወቁ ቻሉ የሚለውን ጥያቄ ደጋግመው ማንሳታቸውን ቀጥለዋል ። የደህንነት ሠራተኞች 10 ን ሰዎች ማን እንደገደላቸው ለማወቅ ይህን ያህል ጊዜ መውሰዳቸው አስደንጋጭ ሆኖ ነው የተገኘው ። እስካሁን መልስ ያላገኙ የተለያዩ ጥያቄዎች በተነሳበት በዚህ ተከታታይ ግድያ ሰበብ ለረዥም ጊዜ የፌደራል ጀርመን የሃገር ውስጥ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ የነበሩት Heinz Fromm እድሜያቸው ሳይደርስ ጡረታ ለመውጣት ተገደዋል ። ከነገ ጀምሮም በFromm ቦታ Hanns Georg Maassen ይተካሉ ። Maassen በጀርመን ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሸባሪዎች ጉዳይ አጥኚ ናቸው ። አዲሱ ተሿሚ ለተሰጣቸው ሃላፊነት ብቁ እንደሆኑ የጀርመን የሃር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ፍሬድሪሽ መስክረዋል ።
« አንቱ የተባሉ አዋቂ ና ጎበዝ የህግ ባለሞያ ናቸው ። እንደኔ እምነት ባላቸው የማሳመን ችሎታ ሁላችንም በጋራ በፖለቲካ መድረኮች በምንስማማበት የተሃድሶ ለውጥ ተግባራዊ እንዲሆን ማብቃታቸው የማይቀር ነው ። በመሆኑም እንደኔ እምነት ለዚህ ቦታ የሚመጥኑ ትክክለኛ ሰው ናቸው »
በማሰን የተተኩት ፍሮም ሐምሌ መጀመሪያ ያወጡት ዘገባ የስለላው መስሪያ ቤት ግድያው በድብቅ በሚንቀሳቀሰው ብሄራዊ ሶሻሊስቶች ንቅናቄ በተሰኘው የአፍቃሪ ናዚዎች ቡድን የበላይነት ሳይፈፀም እንዳልቀረ ነው የሚገልፀው ። ጉዳዩን የተከታተሉት ባለሞያዎች 80 ገፅ ገደማ በሚሆን ሰነድ ያቀረቡት ዘገባ ከ1990 ዎቹ መግቢያ አንስቶ እስካሁን ያለውን የቀኝ አክራሪዎች እንቅስቃሴ የሚዳስስ ነው ። በዚህ ጊዜ በጨቅላ እድሜ ላይ የነበረው የአክራሪነት እንቅስቃሴ በሂደት የኃይል እርምጃን ወደ መውሰድ መሸጋገሩን ሰነዱ ያስረዳል ። ይሁንና ከአንድ አመት በፊት የጀርመን የሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት ይህን ቡድን የአሸባሪዎች መዋቅር ያለው ድርጅት መሆኑን እንደነበረ ለመግለፅ ይፈልግ እንዳልነበረ ነው የሚነገረው ።
የፌደራል ጀርመን የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ፍሪድሬሽ ስለ ሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊዎች አሰራር በሰጡት አስተያየት ፤ ባለሥልጣናቱ ቀኝ አይናቸውን መሸፈን ነበር የፈለጉት ይህ ደግሞ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት ። ከዚህ በመነሳትም አሰራሩ ተቀባይነት የለውም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል ። ከዚህ ጋር መስሪያ ቤቱ ስራውን በአግባቡ አልተወጣም ተአማኒነትንም አጥቷል ሲሉ ተናግረዋል ። የሃገር ውስጥ የስለላ ድርጅት የቀኝ አክራሪነትን የተለያዩ ህዋሳት ሳላየው ቀርቼ ነው ቢል ማንም አያምነውም የዶቼቬለው ማርሴል ፍሩስተናው እንደዘገበው ። ለብዙ አመታት ይህን በሚመለከት በሰፊው ዘገባዎች ይቀርቡ ነበር ። ሆኖም ጠበብቱ አደገኛነቱን ከመጠን በላይ አቃለው ነበር የተመለከቱት ። የፊደራሉ የአገር አስተዳደር ሚኒስትር እነዚህ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱት ብሄረተኞች ተግባር ሌሎች ወገኖች ሊያደፋፈር ስለሚችል በትጋት ክትትል ማደረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል ። በዓለም አቀፍ ደረጃም የትብብር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ነው ሃንስ ፔተር ፍሪድሪሽ ያስገነዘቡት
« ምን ጊዜም የሚቀርበው ጥያቄ የተደራጀ የኃይል እርምጃ መቼ ሊፈፀም ይችላል የሚል ሲሆን ያለምንም ጥርጥር ከብዙ አመታት አንስቶ የሚታወቅና ይህም በአሸባሪነት በኩል ሲከሰት የቆየ ጉዳይ ነው ። NSU ግድያ ከፈፀመ አንስቶ የታወቀ ነው ። እና እንደሚመስለኝም ይሄ ግድያ የመፈፀሙ ፍላጎት አሁንም ቢሆን አለ ። ስለሆነም ምንጊዜም በትጋት መከታተል አለብን ። ይህን በተመለከተም በአለም ቀቀፍ ደረጃ ተባብረን የቀኝ አክራሪነትንና በተመለከተ አብረን መሥራት አለብን ። በቀኝ አክራሪነት ላይም አለም አቀፍ ትግል እየተካሄደ ነው »
በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ቀኝ አክራሪዎች የሚያደርሱት ጥቃት መጠን ከቀድሞው ብዙም አልተለወጠም ። እጎአ በ 2011 ቀኝ አክራሪዎች 640 የአካል ጉዳት አድርሰዋል ። ይህም ከአቻምናው ጋር ሲነፃፀር በሁለት ይበልጣል ። በ 2011 ፣ 5 የ ግድያ ሙከራዎች ሲመዘገቡ ይህም ከ2010 በአንድ ያነሰ ሆኖ ነው የተገኘው ። በዚሁ አመት 16 ሺህ ሊያስቀጣ የሚችል ጥፋት ማድረሳቸውም ተመዝግቧል ። ከ በዚሁ ዘገባ እንደተመለከተው ከዚህ ውስጥ 70 በመቶው ፕሮፓንግዳ ነው ። የናዚዎች አርማ ያለበት ስንደቅ አላማ በይፋ ማውለብለብ አንዱ መሰል ድርጊት ነው ። የሃገር ውስጥ የስለላ ድርጅት እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ በመላ ጀርመን ያሉት የቀኝ ፅንፈኞች ቁጥር 22,500 ይደርሳል ። ይህም እ.ጎ.አ ከ 2011 በ10 በመቶ የቀነሰ ነው ። ቀኝ አክራሪዎቹ የሚወስዱት እርምጃ ደረጃም በጣም የተለያየ ነው ። ጠበብቱ ትንሽ ቀለል አድርገው የሚያዩትን ባህርያቸውን ያፈነገጠ ባህል በማለት ይጠቅሱታል ። የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች የቀኝ አክራሪዎች ሙዚቃ የሚያስፋፉ ሲሆን በዚህ ሙዚቃቸው አይሁዶችን የውጭ አገር ተወላጆችን ወይም የግራ ዘመም አቋም ያላቸውን የሚያጥላሉና የሚያንቋሽሹ ናቸው ። ሆኖም ነገ በአዲስ ሃላፊ የሚተኩት የቀድሞው የጀርመን የሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ ህይንዝ ፍሮም ምስክረነታቸውን እንደሰጡት የቀኝ አክራሪዎች ተከታዮች ቁጥር እየቀነሰ ነው
« አብዩ ችግር አክራሪ የኒዮ ናዚ ገፅታ ና አሁንም ቢሆን ያለው አፈንጋጭ ልዩ ባህርይ ያላቸው ክፍሎች ናቸው ። ይህም ከቀኝ አክራሪዎች እምነትና ፍልስፋና ጋር የተገናኘ ነው ። ከብዙ አመታት አንስቶ ስንከታተለው የቆየ ጉዳይ ነው ይሁንና የዚህ አፈንጋጭ ባህርይ ተከታዮች ቁጥር እየተመናመነ በመሄድ ላይ ነው »
።በክፍላተ ሃገር ያሉ መሰል ቡድኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድጋፍ እያጠጡ ነው ። የስለላው ድርጅት እንደመዘገበው ከሆነ አሁን የደጋፊዎች ቁጥር ከ 8300 ወደ 7600 ዝቅ ብሏል ። እነዚህ ቡድኖች ሃሳብ የሚለዋወጡበትን ቅስቀሳ የሚያካሂዱበት ዋናው መሣሪያቸው ኢንተርኔት ነው ። ራሳቸውን ሞት የማይደፍረን የሚሉት አክራሪዎች ይሄን የመገናኛ ዘዴ በሰፊው ይጠቀሙበታል ከአካባቢም አልፈው ድንበር ዘለል ተሰሚነት ለማግኘት በተጠናከረ መልኩ አላማቸውን ለማሳካት እየተጠቀሙበት ነው ።
« በኢንተርኔት በመጠቀም የመስፋፋት አላማቸውን እንደሚያሳኩ ያስባሉ ሲመለከቱዋቸው ችቦ የሚያበሩ ና ነጭ ጭምብል ያጠለቁ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰማሩ መስሎ ይታያል ። እንደ ነሱ እምነት የፈዘዘውን ህዝብ ጥፋት የሚያሰጋውን ህዝብ ለመቀስቀስ ና ለማሳየት ነው የሚጥሩት ። ይሁንና ከሚታሰበው በጣም ያነሱ ጥቂቶች ናቸው ። ነገር ግን በቪድዮ በመጠቀም ብዙ እንደሆኑና ትልቅ ንቅናቄ ያለ በማስመሰሉ ረገድ ተሳክቶላቸዋል ። » አላማቸው ህዝብ በብዛት እንዲከተላቸው ለማድረግ ይሁኑ እንጂ በጥቂት መቶዎች የሚቀጠሩ ብቻ እንደሚተባበሩዋቸው ነው ፍርም የሚናገሩት ።
እነዚህ ቡድኖች ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ያለ ፈቃድ በሌሊት ስብሰባ ሲያደረግ ቆይቷል ። ይህን መሰል እንቅስቃሴ ከጀመሩት መካከል ራሱን የደቡብ ብራብድንቡርግ ተፋላሚ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ቡድን ይገኝበታል ይህም በቅርቡ በብርንድቡርግ የሃገር ውስጥ አስተዳደር ሚኒስቴር በህግ ታግደል ። በሌላም በኩል 9 የውጭ ተወላጆችና አንድ የጀርመን ፖሊስ በቀኝ አክራሪዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ከታወቀ በኃላ በአንዳንድ ፌደራል ክፍላተ ሃገር መቀመጫዎች ለመያዝ የበቃው ቀኝ አክራሪውን የጀርመን ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲታገገድ የሚጠይቁ ልዩ ልዩ ውይይቶች ሲካሄዱ ከርመዋል ። በሚቀጥለው አመት በታህሳስ ወር ማብቂያ ላይም 16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ፓርቲው በህገ መንግሥታዊዊ ፍርድ ቤት እንዲታገድ ለ 2ተኛ ጊዜ ይሞክራሉ ። ፓርቲው ለማሳገድ እጎአ በ 2003 የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል ። ፎርም እንደሚሉት አልሆነለትም እንጂ ፓርቲው አላማውን ለማሳካት በየጊዜው የህዝብን ስሜት ሊያነሳሱ ይችላሉ ብሎ የሚያምንባቸውን አጀንዳዎች ይዞ ብቅ የሚል ፓርቲ ነው ።
« NPD እስልምናን በማጥላላት ሁል ጊዜ አንድ ርዕስ ይዞ ለመነሳት ይሞክራል ይeህን ጥላቻ መሰረት በማድረግ ይህን ለመጠቀም ይሞክራል ወደፊትም ቢሆን ይሄ በኤን ፒዴ መነጋገሪያ ሆኖ የሚቀጥል ነው ። ይህን በማስተጋባት በምርጫ የተሳካ ውጤትን ለማግኘት ሊረዳ ይችላል ። እስካሁን ድረስ አልተሳካላቸውም ግን በመሞከር ላይ ናቸው ። በጣሙን ይሄን ያህል አልተሳካላቸውም ። ስለሆነም በይበልጥ በእለታዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ በማትኮር ና ባልተለወጠው ርዕዮታቸውን አቅጣጫ ትግላቸውን እንደቀጠሉ ናቸው ሙከራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው ። »
የቀኝ ፅንፈኞችን እንቅስቃሴ መከታተልና በንቃት መጠባበቅ የጀርመን የሃገር ውስጥ የስለላ መስሪያ ቤት ዋነኛ ተግባራት ሆኖ ይቀጥላል ። አዲሱ የመስሪያ ቤቱ ሃላፊም ይህን ሃላፊነታቸውን በሚገባ ይወጣሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ