የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክስ ተጀመረ
ዓርብ፣ ጥር 30 200622ተኛዉ የክረምት ኦሎምፒክ በደቡባዊያ የሩስያ ከተማ ሶቺ ላይ በይፋ በድምቀት ተከፍቶአል። እስከ የካቲት 16 ቀን ድረስ በሚዘልቀዉ በዚሁ የክረምት ኦሎምፒክ ከ 87 የዓለም ሃገራት የተዉጣጡ 2900 ስፖርተኞች ለወርቅ፤ ለብር እና ለነሃስ ሜዳልያ እንደሚወዳደሩ ዘገባዎች,ቁመዋል። በሶቺዉ ኦሎምፒክ በ 98 የተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ዉድድሩ እንደሚካሄድ ታዉቋል። በሶቺዉ የኦሎምፒክ ዉድድር ከጀርመን ብቻ 153 ስፖርተኞች ለመካፈል ቦታዉ ላይ ተገኝተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩኤስ አሜሪካ የስለላ ድርጅት፤ ሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ የአሸባሪ ጥቃት እንዳይጣል ሲል ዳግም ትናንት ማስጠንቀቁዋ ይታወቃል። የክረምት ኦሎምፒክስ በሩስያ ሲካሄድ የዘንድሮዉ የመጀመርያ ሲሆን እንደ ፕሪዚዳንት ፑቲን የኦሎምፒክስ ዉድድሩ « ሩስያ ለዓለም ዘመናዊ ሆና በርዋን የምትከፍትበት መድረክ ነዉ»። በዚህም ዉድድሩ በከፍተኛ ጥበቃ እና ቁጥጥር ስር እንደሚሆን ፑቲን በተደጋጋሚ መናገራቸዉ ይታወቃል።
የሩሲያዋ በረዷማ ግዛት ሶቺ ይህን ስፖርታዊ ዉድድር ለማስተናገድ ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ መሰናዶ ስታደርግ ቆይታለች። ዘገባዎች እንደሚሉት ከዛሬ 7 ዓመት በፊት ሶቺ የተመለከተ ዛሬ ፍፁም አያዉቃትም፤ በዘመናዊና ዉድ የክረምት ስፖርት ማዘዉተሪያዎች ደምቃለች። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታስተናግደዉ ለሶቺዉ የክረምት ኦሎምፒክ ከፍተኛ ገንዘብ አዉጥቷል በሚል እየተተቸ ነዉ፤ 51 ቢሊዮን ዶላር። በመርሃግብሩ መሠረትም ዛሬ የሚከፈተዉ የክረምት ኦሎምፒክስ የካቲት አስራ ስድስት ያበቃል። የሎንደኗ ዘጋቢያችን ሃና ደምሴ ተከታዩን ዘገባ ልካልናለች
ሃና ደምሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ተክሌ የኋላ