1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ እጩ ፔር ሽታይንብሩክ

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2006

ከዋነኛዎቹ የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመራሄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ እጩ ፔር ሽታይንብሩክ፤ ጥሩ የንግግር ተሰጥዎያላቸዉ፤ ብልህና በፋይናንስ ምሁርነት ይታወቃሉ።

https://p.dw.com/p/19hwk
SPD-Kanzlerkandidat Peer Steinbrück spricht am 15.08.2013 in Berlin zum Thema Energiepolitik. Foto: Maurizio Gambarini/dpa
ምስል picture-alliance/dpa

ምንም እንኳ በበቅርቡ በሳቸዉና በክርስቲያን ዲሞክራት ሕብረት ፓርቲ እጩ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል መካከል የተካሄደዉ የክርክር መድረክ፤ ዉጤት ባይሸናነፉም፤ ፔር ሽታይንብሩክ፤ ምርጫዉን አሸንፋለሁ የሚል እምነት የላቸዉም፤
የስድሳ ስድስት ዓመቱ የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ እጩ ፔር ሽታይንብሩክ፤ በምርጫ ዘመቻ ወቅት፣ ጠንካራ፣ ቆራጥ ሆነዉ ነዉ የሚታዩት። ስለ ክርክሩ ዉድድሩ ሁኔታ ማዉራትን አይወዱም። በንግግራቸዉ ነገር ከማንዛዛት ይልቅ አጠር መጠን አድርገዉ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ መግባት ይመርጣሉ፤
«የፊደራል ጀርመን መራሄ መንግስት መሆን እሻለሁ»
የሃንቡርግ ከተማ የአንድ ነጋዴ ቤተሰብ ልጅ የሆኑት የ66 ዓመቱ የመራሄ መንግስት እጩ ፔር ሽታይንብሩክ፤ ለአስርተ ዓመታት በሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አባልነት የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸዉ ይታወቃሉ። በብሔራዊ ኤኮነሚ ጉዳይ ሞያ የከፍተኛ ትምህታቸዉን እንዳጠናቀቁ፤ በመራሄ መንግስት ጽ/ቤት ረዳት የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለሞያ ሆነዉ ሰርተዋል። ሽታይንብሩክ በተለያዩ የመንግስት መስርያ ቤቶች እና ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች በተለያየ ማዕረግ ከሠሩ በኋላ የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነዉ በማገልገላቸዉም ይታወቃሉ። ሽታይንብሩክ ቀደም ሲል ለገንዘብ ሚንስትርነት ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንደገና በእጩነት ቀርበዉ ባይመረጡም ቅሉ፤ ለአምስት ዓመት የኖርድራይን ዌስትፋለን ፊደራል ክፍለ ሀገር ጠ/ሚ ሆነዉ አገልግለዋል።
በጎ,አ 2005 ዓ,ም ሽታይንብሩክ የሚከተሉት የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ SPD በመራሂተ መንግስት ለሚመራዉ ጥምር መንግስት የገንዘብ ሚኒስትር ሆነዉ እንዲሰሩ መድቦአቸዉ አገልግለዋል። በገንዘብ ሚኒስትር ሥልጣናቸዉ ዘመን ሽታይንብሩክ ከመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በገራ ሀገሪቱ ከገባችበት የፋይናንስ ቀዉስ እንድትወጣ ታግለዋል። ስለዝያ ግዜዉ የጋራ ተግባር ሽታይንብሩክ ዛሪ እንዲህ ይላሉ፥
« ባቀረብነዉ መረሃ ግብር አስተዳደረች እንጂ ፅንሰ ሃሳቡን እስዋ አላፈለቀችዉም። የዚህ መረሃ ግብር አርቃቂ የሶሻል ዴሞክራቱ ህብረት ነዉ»
መረሃ-ግብር አርቃቂና እንደ አድራጊ፤ ሆነዉ መታየት የሚፈልጉት ፔር ሽታይንብሩክ ግን ፤ በዚህ የምረጡኝ ዘመቻ አንድ ችግርም ገጥሞአቸዋል። የሚያራምዱት የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲያቸዉ፤ በጎ,አ 2012 ዓ,ም ለመራሄ መንግስትነት በእጩነት ከመምረጣቸዉ በፊት፤ ሽታይንብሩክ በፓርላማ አባልነት ካላቸዉ ሥራ ጎን፤ በባንክ ዉስጥ ተቀጥረዉ፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በፋይናንስ ጉዳዩች ላይ ትምህርት በመስጠት እጅግ ብዙ ገንዘብ አግኝተዋል፤ በሚል የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸዉ እና የሀገሪቱ ነዋሪዎች ጥያቄ አንስተዉባቸዋል። ሽታይንብሩክ ኪሳቸዉ ያስገቡት ከአንድ ሚሊዮን ይሮ በላይ ነዉ ተብሎአል። ከባንኮች ብዙ ገንዘብን ያገኘ የአንድ የመራሄ መንግስት እጩ፤ ስግብግብ ባንኮች ያላቸዉን የፋይናንስ አሰራር እንዲት ሊቃወም ይችላል በማህበረሰቡ ዘንድስ እንዴት ታአማኒነትን ያገኛል ሲሉም የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸዉ እና የሀገሪቱ ነዋሪዎች ይጠይቃሉ።
በአንድ የምረጡኝ ዘመቻ መድረክ የእጩ መራሄ-መንግስት ሽታይንብሩክ ባለቤት ተገኝተዉ፤ ባለቤታቸዉ ፤ እንደሚባለዉ ሳይሆን በጣም ጥሩ ሰዉና ታዓማኒ ነዉ ሲሉ ደግፈዋቸዋል። በመድረኩ አንድ ጋዜጠኛ፤ ስለ ሽታይንብሩክ የሚባለዉን በማንሳት ይህን ያህል ከሰሩ ለምን መራሄ መንግስት መሆን ፈለጉ ብሎ በጠየቃቸዉ ግዜ ሽታይን ብሩክ የእንባ ሲቃ ይዞአቸዉ መልስ መስጠት አቅቶአቸዉ ታይተዉ ነበር፤
« ስለዚህ ነገር እኔን ተረድታኛለች የምላት ባለቤቴ በአጭሩ ተናግራዋለች። በዉጭ የሚያዉቁኝ ስለኔ፤ ስሜት የሌለኝ ቀዝቃዛ አድርገዉ ያስቡኛል፤ እኔ ግን እንደዛ እንዳልሆንኩ እና በስሜት ልነካ የምችል ሰዉ መሆኔን፤ ባለቤቴ ስለኔ ንግግር ባደረገችበት ወቅት፤ ታይቶአል»
ሽታይን ብሩክ ብዙም ሳይቆዩ ካነቃቸዉ የለቅሶ ሲቃ፤ እንደምንም ታግለዉ እራሳቸዉን ተቆጣጠሩና ወደ ጀመሩት ዉይይት፤ ጥያቄና መልስ ተመለሱ። ሽታይንብሩክ ጎበዝ እና ብሩህ ጭንቅላት ያላቸዉ፤ ግን ትንሽ ጠጣር፤ ማስተማር የሚወዱ፤ የዲፕሎማሲ ክህሎት የሚያንሳቸዉ መሆናቸዉ ይነገርላቸዋል። የምረጡኝ ዘመቻ ዋና መርሐቸዉ ደግሞ፤ በባለሃብቱ ላይ የቀረጥ ጭማሪ በማድረግ፤ የሚገኘዉን ለጋራ ፍትሃዊነት ለህብረተሰቡ ማዳረስ ነዉ፤
«ሌላዉ ባሳለፍነዉ ዓመታት እየጎላ የመጣዉ የግል ሃብት ጉዳይ ነዉ። ሃብታሞች ሃብታም እየሆኑ፤ ድሆች ደግሞ በድህነት ላይ ድህነት እየጨመረባቸዉ መጥዋል። ይህ ሽታይንብሩክ ወይም የሶሻል ዴሞክራቲዉ ፓርቲ SPD የፈጠሩት ሳይሆን፤ ይህ የፌደራል ሪፐብሊኩ የመዘርዝር ጥናት የሚያሳየዉ ጉዳይ ነዉ። ስለዚህ ከዚህ ሃብት በከፊል፤ ለትምህርት፤ ለመሠረተ ልማት ወይም የሀገሪቱን እዳ ለመቀነስ ፤ ኤኮኖሚዉን ለማጠንከር መዋል አለበት። ይህ ነዉ የእኔ አቋም»
ሽታይንሩክ በጀርመን ዙርያ ያለዉን አነስተኛ የደሞዝ መጠን ማስተካከል፤ የበለጠ የሥራ እድል መፍጠር፤ እንዲሁም ለሰራተኛ ሴቶች ድጋፍን፤ መስጠት ይፈልጋሉ። ከዓመታት በፊት ሽታይንብሩክ በስልጣን ላይ ሳሉ ጠንካራ የፋይናንስ ተሃድሶን ማድረጋቸዉ ይታወሳል፤
«የቀድሞ መራሄ መንግስት ጌሃርድ ሽሮደር ያወጡትን የኤኮኖሚ ተሃድሶ መረሃ-ግብር እደግፋለሁ። በዚህም ምክንያት ነዉ የኤኮነሚ ደረጃችን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኘዉ። ነገር ግን በዚህ ተሃድሶ መረሃ-ግብር ዉስጥም ሊሻሻሉ ወይም ሊታረሙ የሚገባቸዉ ስህተቶች አሉ። ይህ የኔ አቋም እና፤ ሊደረግ የሚችል ነገር ጉዳይ ነዉ»
ሽታይንብሩክ በትግል ላይ ናቸዉ፤ በህዝብ ዘንድ የበለጠ መራጭ ማን አለዉ የለዉም የሚለዉ ጥያቄን ወደጎን ገሸሽ አድርገዉ መተዉ ይችላሉ። አሁን በዉስጣዊ ፖለቲካ ጉዳዮች አመኔታ አሳድረዉ፤ ዉሳኔ ላይ ያልደረሱ መራጮችን መሰብሰብና በጃቸዉ ማስገባት ይፈልጋሉ። እጅግ አስፈላጊ የሚሏቸዉ የዉጭ ፖለቲካ ርዕሶቻቸዉ ደግሞ፤ የዉጭ የስለላ ድርጅቶች በጀርመን ያለ የግል ሚስጥራዊ መረጃ ህግን እንዲያከብሩ ማድረግ ፤ ቱርክ የአዉሮጳዉ ህብረት አባል እንድትሆን፤ በሩስያ የሰብዓዊ መብት እንዲሻሻል፤ እንዲሁም በደቡብ አዉሮጳ በሚገኙ፤ በኤኮኖሚ ደካማ የሆኑ ሀገራት ላይ የተጣለዉ ጠንካራ የቁጠባ መርህ እንዲላላ የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ ሽታይን ብሩክ ተጨማሪ ተህድሶ እንዲደረግ ይወተዉታሉ፤
«እንደኔ እምነት ይህ የኤኮነሚ ድጋፍ አንዳንድ ሀገሮችን ጥፋት ላይ ነዉ የሚጥላቸዉ። በዚህ በሚሰጣቸዉ እርዳታ እያስቆለቆሉ ከመሄድ በቀር ማገገም እና ከዉድቀታቸዉ ማንሰራራት አይችሉም»
ፔር ሽታይንብሩክ አስፈላጊ የፖለቲካ እዉቀትን የ21 ዓመት ወጣት ሳሉ ነዉ ያገኙት። የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አራማጁ ሽታይንብሩክ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ሶሻሊስት ሀገራትን ከጀርመን ጋር ለማቀራረብ ጉልህ ፖለቲካዊ ሚና በመጫወት በዓለም ደረጃ ጀርመን ጥሩ ገጽታ እንዲኖራት ያበቄት የቀድሞዉን መራሄ መንግስት የቪሊ ብራንድን መርሕ በማየት ነዉ ወደ ፖለቲካዉ ዓለም ለመግባት የበቁት።
«ምንም ሳያደርጉ አንድ ነገር ማግኘት አይቻልም። ጥሩ ነገር ላይ ለመድረስ በጣም መታገል ያስፈልጋል። አዉሮጳ ዉስጥ ሰላም እንዲሰፍንና፤ በማሕበረሰቡም መካከል ጥሩ ጉርብትና እንዲኖርና፤ ሰላም የሰፈነበት አካባቢን ለመፍጠር መስራት እና መታገል ይኖርብናል»
ሽታይንብሩክ፤ በመራሄ መንግስትነት ሲያገለግሉ ይህንን መፈፀም ነዉ የሚሹት፤ ግን ሜርክል ከሚመሩት ከክርስትያን ዲሞክራት ፓርቲ ጋር መጣመርን አይሹም።.
«እኛ ሌሎች የሚጠቀሙብን ሞኞች አይደለንም»

አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ

Katrin Goering-Eckart of Germany's environmental party Die Gruenen (The Greens) and Chancellor candidate of the Social Democratic party (SPD) Peer Steinbrueck address a news conference in Berlin July 11, 2013. REUTERS/Tobias Schwarz (GERMANY - Tags: POLITICS)
ምስል Reuters
Katrin Goering-Eckart of Germany's environmental party Die Gruenen (The Greens) and Chancellor candidate of the Social Democratic party (SPD) Peer Steinbrueck address a news conference in Berlin July 11, 2013. REUTERS/Tobias Schwarz (GERMANY - Tags: POLITICS)
ምስል DW/W. Dick
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ