የሶሪያ ጦርነትና ዲፕሎማሲዉ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2005
13 12 12
የሶሪያ ፖለቲካዊ ዉዝግብ ከዲፕሎማሲያዊዉ መፍትሔ ይልቅ በጦርነቱ ዉድመት እንደቀጠለ ነዉ።ትናንት ማራኪሽ-ሞሮክ የተሰበሰቡት የምዕራባዉያንና የአረብ ሐገራት መልዕክተኞች የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለሚወጉት አማፂያን እዉቅና መስጠታቸዉ ለአማፂያኑ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ድል ታይቷል።የሶሪያ መንግሥትን ትደግፋለች የምትባለዉ ሩሲያ ግን በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ለአማፂያኑ ዕዉቅና መስጠቷን አጥብቃ ተቃዉማዋለች።ለአማፂያኑ ዕዉቅና መሰጠቱም ሆነ ተቃዉሞዉ ሶሪያን የሚያወድመዉን ጦርነት የመለወጥ አዝማሚያ አላሳየበትም።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።
ጦርነቱ ቀጥሏል።መንደሮች፥ አነስተኛ ከተሞች፥ መንገድ-ማሳዎችን እያወደመ፥ ከታሪካዊያኑ ትላልቅ ከተሞች አሌፖን ደፍጥጦ፥ ደማስቆን ባለፍ-አገደምም ቢሆን እያንቀረቀባት ነዉ።ሃያ-አንደኛ ወሩ።በትንሽ ግምት አርባ ሺሕ ሕዝብ አልቋል።የቆሰለዉ በብዙ መቶ ሺሕ ይገመታል።ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተሰድዷል።በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከወደመ፥ ወይም በከፊል ከጠፋ ቤን ንብረት፥ ቀዬዉ ተፈናቅሏል።
እንደ ሶሪያ የታሪክ ዘመን ብዛት እብዙ ቦታ የተሰነጣጠቁት አማፂያን ከዚሕ ቀደም የመሠረቱትን ሕብረት አፍርሰዉ በቅርቡ አዲስ መመሥረታቸዉ-አንድ፥ ትናንት ማራኪሽ-ሞሮኮ የተሰበሰቡትን የዓረብ እና የምዕራብ ሐገራትን ዕዉቅና ማግኘታቸዉ-ሁለት፥ምክንያት የሚጠቅሱት-እራሳቸዉ አማፂያኑና አደራጆቻቸዉ እንደሚሉት ለነሱ የድል-ጭላጭል ብርቀት፥ ለአሰድ ስርዓት የዉድቀት ምልክት ነዉ።
የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ ነቢል ኤል አራብይ ትናንት እንዳስታወቁት ደግሞ ሊጋቸዉ የሚደግፋቸዉ አማፂያን በዲፕሎማሲዉ ብቻ ሳይሆን በጦር አዉዱም ከድል አፋፍ ላይ ናቸዉ።
«አዲስ ብሔራዊ አመራር አለን።አዲስ ወታደራዊ አመራር አለን።በዚሕ መሐል ዉጊያዉ ደማስቆ ደርሷል።ይሕ አሁን ያለዉ ሥርዓት ከፍፃሜዉ ከሚደርሰዉ የመጨረሻ ፉሮጎ ላይ መሳፈሩን አመልካች ነዉ።»
ይሁን እንጂ አማፂያኑ ያገኙት ዕዉቅና የእልቂት፥ ጥፋት፥ ዉድመቱን ግመት አናረዉ እንጂ አላረገበዉም።ጥንታዊቱን ሐገር ወደ ትቢያ መከመሪያነት ቀየራት-እንጂ የአረብ ሊጉ መሪ እንዳሉት አማፂያኑን የደማስቆ ቤተ-መንግሥትን ከሚቆጣጠሩበት ደረጃ አላቃረባቸዉም።ደእንዲያዉያም ከተፋላሚ ሐይላት የአሸናፊና ተሸናፊዉን ማንነትን መገመት ከሚያስችልበት ደረጃ ገና አልተደረሰም።
የማራኪሽ ጉባኤተኞች ያሰለፉትን ዉሳኔ በተለይም ለአማፂያኑ ዕዉቅና መሠጠቱን ሩሲያ ተቃዉማዋለች።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ለአማፂያኑ ዕዉቅና የሰጠችዉ ከሰወስት ቀናት በፊት ከሩሲያ ጋር የደረሰችበትን ስምምነት አፍርሳ ነዉ።
«ዕዉቅና መሰጠቱ ጄኔቭ ላይ የተደረሰበትን የጋራ አቋም የሚፃረር ነዉ።የጄኔቩ የጋራ አቋም በሶሪያ መንግሥትና በተቃዋሚዎች ተወካዮች መካካል አጠቃላይ ድርድር እንዲደረግ ነበር።ከሰወስት ቀናት በፊት ጄኔቭ ላይ ባደረግነዉ ምክክር መሠረት የሶሪያ መንግሥትም የሚሳተፍበት አጠቃላይ ድርድር በማድረጉ ጥረት አስፈላጊነት ከአሜሪካዉያን ጋር ተግባብተን ነበር።»
አልሆነም።ዩናይትድ ስቴትስ እንደ አዉሮጳና እንደ መካካለኛዉ ምሥራቅ ሸሪኮዎችዋ ሁሉ የሶሪያ አማፂያን የሶሪያ ብቸኛ ተወካይ ለመሆናቸዉ ዕዉቅና ሰጥጣለች።ጦርነት፥ እልቂት፥ ጥፋቱም ቀጥሏል።ዛሬም ጭምር።
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ