1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማልያ ጋዜጠኞችና ተቃውሞአቸው፧

ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2000

ሦስት የሶማልያ የግል ራዲዮ ጣቢያዎች፧ ከማሠራጨት ከታገዱና፧ አንድ በትርፍ ጊዜው ለጋዜጣዊ ሥራ ፎቶግራፍ በማንሣት የተሠማራ ባለሙያም፧ በፖሊስ ተይዞ ከታሠረ ወዲህ፧ ጋዜጠኞቹ፧ በኅብረት ለመንግሥት ተቃውሞ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/E0Xx
የሶማልያ ስደተኞች በኬንያ
የሶማልያ ስደተኞች በኬንያምስል AP
በዚሁ በፕረስ ነጻነት ላይ የተወሰደውን እርምጃ ባለመደገፍ፧ ያልተከለከሉ የራዲዮ ጣቢያዎችና አንድ በሞቐዲሹ የሚሠራ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጭምር ከታገዱት የሙያ ባልደረቦቻቸው ጎን በመቆም፧ ትናንት ከቀትር በኋላ፧ ሥርጭታቸውን በጠቅላላ እስከማቆም ማደማቸው ታውቋል።....ተክሌ የኋላ...
በመዲናይቱ በሞቐዲሹ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች፧ መንግሥት፧ በፕረስ ነጻነት ላይ የወሰደውን የማረቅ እርምጃ በመቃወም ትናንት ሥርጭታቸውን ለ ኻያ ዐራት ሰዓት ማቋራቸውን የማሠራጭ ጣቢያዎቹ ሥራ አስኪያጂዎች አስረድተዋል። ባለፈው ሳምንት ሦስት ራዲዮ ጣቢያዎች፧ ራዲዮ ሸበሌ፧ ራዲዮ ባናዲርና ራዲዮ ሲምባ፧ ከታገዱ ወዲህ፧ ሌሎች ስድስት ራዲዮ ጣቢያዎችና HornAfrik የተሰኘው የቴሌቭዝን ጣቢያ፧ ትናንት ከቀትር በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት አንስቶ ለኻያ ዐራት ሰዓት ሥርጭት እስከማቋረጥ ያደረሰ እርምጃ ወስደዋል። የራዲዮ ሸበሌ፧ ጥብቅ ዋና ሥራ አስኪያጅ፧ ሙክታር ሙሐመድ ሂራቤ እንደገለጹት የተቃውሞ እርምጃ የተወሰደው፧ የነጻውን መገናኛ ብዙኀን አሠራር የሚጻረር ተግባር በመፈጸሙ ነው። የ HornAfrik TV ሥራ አስኪያጅ ሰዒድ ጣህሊል፧ «ከታገዱት መገናኛ ብዙኀን ጎን በመቆም ኅብረትን ማሳየት ይኖርብናል!« ባይ ናቸው። የታቃውሞ ድምፅ ካሰሙት መካከል የታገደው ከራዲዮ ሲምባ ሥራ አስኪያጆችና ጋዜጠኞች አንደኛው፧ ሞሀመድ ሺል ሐሰን.......
«የኅብረት፧ የመተባበር እርምጃ ነበረ የታየው። የታገዱትን ሦስት ራዲዮ ጣቢያዎች በተመለከተ ማለት ነው። የሌሎቹ የዜና ማሠራጫ አውታሮች ባላቤቶችና ሥራ አስኪያጆች፧ (ሥርጭታቸው ያልታገደባቸው)ከረጅም ጊዜ ውይይት በኋላ፧ በሞቐዲሹ የሚሠሩ ራዲዮ ጣቢያዎች ሁሉ ሥራ እንዲያቆሙ ተስማማን። ባለሥልጣናቱ እስካሁን ምንም አላሉም። በመሆኑም፧ እንደአገሬው ሰዓት አቆጣጠር፧ ከሰዓት በኋላ፧ ሦስት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እንጠብቃለን። ምላሽ ካልሰጡ፧ ሥርጭት የማቆሙን እርምጃ እንገፋበታለን።«
የሞቐዲሹ ከንቲባም ሆኑ የአካባቢ ባለሥጣናት የሦስቱን የራዲዮ ጣቢያዎችተግባር በማገድ የወሰዱትን እርምጃ ህገ ወጥ ነው ያለው ሞሐመድ ሺል ሐሰን ምክንያቱን ሲያስረዳ...
«ይህ ጉዳይ የአካባቢ፧ ባለሥልጣናትን አይመለከትም። የሚያገባው የማስታዋቂያ ሚንስቴር ነው። ራዲዮ ጣቢያዎቹ፧ ተግባራቸውን ያከናውናሉ፧ አያከናውኑም፧ የሚወስነው፧ ማስታወቂያ ሚንስቴር ነው።«
ባለፈው ሳምንት፧ በሶማልያ ሦስት ራዲዮ ጣቢያዎች ሥርጭታቸው እንዲያቋርጡ የተወሰደውን እርምጃ፧ የፕረስ ነጻነት ተቆርቋሪ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአውሮፓው ኅብረት፧ በጥብቅ መቃወማቸው አይዘነጋም። የፕራስ ነጻነት ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ይዞታም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በመጠቆም ላይ ናቸው። የሶማልያ ባለሥልጣናት፧ ነጻው መገናኛ ብዙኀን፧ በመዲናይቱ በሞቐዲሹ ውዝግብ እንዲባባስ፧ በተለይ ፀረ-መንግሥት ወገኖችን እየጠየቁ ፕሮፖጋንዳ ያሠራጫሉ፧ የአመጽ ተግባር እንዲንቀሳቀስም ያደርጋሉ በማለት ይከሳሉ።
ከሶማልያ መንግሥት ወታደሮች ጎን-ለጎን ጦሯንአሰልፋ አማጽያንን የምትዋጋው ኢትዮጵያም፧ የሶማልያ መገናኛ ብዙኀን፧ በፕሮፖጋንዳ የተመሉ ናቸው ማለቷን AFP ጠቅሷል። የሶማልያ ባለሥልጣናት፧ በፕረስ ነጻነት ላይ ያሳረፉትን ጫና እንዲያነሱ የፕረስና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላቀረቡላቸው ጥሪ፧ ጆሮ ዳባ-ልበስ እንዳሉ ናቸው። ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ እስከቅርብ ጊዜ ሶማልያ ውስጥ ቢያንስ 8 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፧ ከዚያ በርከት ያሉ ደግሞ መታሠር፧ መታፈንና መዘረፍ ዕጣቸው ሆኗል። ለፕረስ ነጻነት የቆሙ ድርጅቶች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፧ ከኢራቅ ቀጥሎ ለጋዜጠኞች የምድር ሲዖል የሆነች ሀገር፧ ሶማልያ ናት።