የሶማሊያ ሁኔታና ኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ መስከረም 15 2005
ኬንያ መራሹ ጦር ባለፈዉ ሳምንት ከኪስማዮ አርባ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ቢያስታዉቅም እስካሁን ሥልጣዊቱን የወደብ ከተማ ከአሸባብ እጅ አላስለቀቀም።ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮጵያ ጦር ግን በኪስማዩዉ ዘመቻ በቀጥታ አልተካፈለም።አሸባብ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፅመዉ ጥቃትም እንደቀጠለ ነዉ። የሶማሊያን ወቅታዊ ሁኔታና የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ ነጋሽ መሐመድ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን አነጋግሮ ያጠናቀረዉ ዘገባ አለ።
የኬንያ ጦር አምና ጥቅምት ኪስማዮን ለመያዝ የነደፈ ዕቅዱን ባመቱ ዘንድሮ ገቢር ለማድረግ ከሌሎች ሐገራት የዘመቱትን (የአሚሶም)ና የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችን አስከትሎ ወደ ወደብ ከተማይቱ መንቀሳቀሱን ካስታወቀ ሳምንቱ።
ቤይዶዎንና በለድወይንን የመሳሰሉትን የደቡብ ሶማሊያን ሥልታዊ ከተሞችን ከሐቻምና ክረምት ጀምሮ የሚቆጣጠረዉ የኢትዮጵያ ጦር ግን እንደ ኬንያ ብጤዉ በአሚሶም ዕዝ ሥር አልተጠቃለለም።በኪስማዩዉ ዘመቻም አልተከፋለም።አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት ጦሩ ላሁኑ በቀጥታ ኪስማዮ አይዝመት እንጂ አስፈላጊ ከሆነ መዝመቱ አይቀርም።
የአሚሶም ጦር ኪስማዮ ለመድረስ አርባ ኪሎ ሜርትር እንደቀረዉ ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሲነገር ከተማይቱን ለቀዉ የነበሩት የአሸባብ ተዋጊዎች ባንድ ቀን ልዩነት ተመልሰዉ ከተማይቱን ተቆጣጥረዋታል።
የአሸባብ አባላት ወይም ተባባሪዎቹ የሚባሉ አጥፍቶ ጠፊዎችና ታጣቂዎች ርዕሠ-ከተማ ሞቃዶሾ ዉስጥ የሚጥሉት አደጋም እየተደጋገመ ነዉ።ሰሞኑን በተጣሉ አደጋዎች ሰወስት ጋዜጠኞችንና አንድ የምክር ቤት እንደራሴን ጨምሮ ሃያ ሰዎች ተገድለዋል።አምባሳደር ዲና እንደሚሉት አሸባብ በወታደራዊዉም በፖለቲካዉም መስክ እየተሸነፈ ነዉ።መፍጨርጨሩ ግን ወደፊትም አይቀርም።
አምባሳደር ዲና ከሳምንት በፊት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ ሥልጣን በተረከቡበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ሆነዉ የተገኙተዉ ነበር።በሞቃዲሾዉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የበርካታ ሐገራት ተወካዮች መገኘታቸዉ አምባሳደሩ እንደሚያምኑት አዲሱ የሶማሊያ መንግሥት ሠፊ ድጋፍ እንዳለዉ ጠቋሚ ነዉ።
በሶማሊያም፥ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ጊዜ አዳዲስ መሪዎች ሥልጣን መያዛቸዉ የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት አምባሳደሩ እንደሚሉት ይበልጥ ያጠናክረዋል እንጂ አይለዉጠዉም።ኢትዮጵያም ለአዲሱ ፕሬዝዳትና ለመንግሥታቸዉ ሙሉ ድጋፏን ትሰጣለች።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳት ለዘብተኛ ከሚባሉት የአሸባብ መሪዎች ጋር ለመደራደር ማቀዳቸዉን በተመረጡ ማግሥት አስታዉቀዉ ነበር።አንድ የአሸባብ ሹም ትናንት እንዳሉት ግን የአዲሱን መንግሥት ሹማምንታት የምክር ቤት አባላትን አንድ በአንድ ይገድላል።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ