1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2003

በአውሮፓ ክለቦች ብሄራዊ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሩ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ በሄደ ቁጥር በአንድ በኩል ቀደምቱን ቦታዎች ለመያዝ በሌላም ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላለመከለስ የሚደረገው ትግል እየጠነከረ ነው።

https://p.dw.com/p/R93X
ምስል dapd

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የባርሤሎና አመራር ቡድኑ ከሤቪያ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ብቻ በመወሰኑ ከሰባት ወደ አምሥት ነጥቦች ጠበብ ሊል በቅቷል። በተቀያሪ ተጫዋቹ በቦያን ክርኪች አማካይነት በ 30ኛዋ ደቂቃ ላይ 1-0 መርቶ የነበረው ባርሣ በዚህ የውድድር ወቅት ነጥቦች አሳልፎ ሲሰጥ ገና ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ በፊናው ሄርኩለስን 2-0 በመርታት ባርሤሎናን መልሶ ሊቃረብ ችሏል። ለሬያል ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የፈረንሣዩ ብሄራዊ ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ ነበር።

የስፓኙ ሻምፒዮና ሊጠቃለል አሥር ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ባርሣ በ 75 ነጥቦች ይመራል፤ ሬያል ማድሪድ በ 70 ሁለተኛ ነው። በጣሙን ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነት የሚከተለው ቫሌንሢያ ለሻምፒዮንነት ቀድሞም ዕድል ባይኖረውም በዚህ ሰንበት በሣራጎሣ 4-0 በመቀጣቱ ደግሞ የባሰ ነው ወደታች ያቆለቆለው። ከሬያል ማድሪድ እንኳ በ 16 ነጥቦች ዝቅ ይላል። በዚሁ ታዲያ ከስፖርቲንግ ጊዮን 1-1 የተለያየው አራተኛው ቪላርሬያል በሶሥት ነጥቦች ልዩነት በመጠጋት ለሶሥተኝነት የሚደረገውን ፉክክር ማጠናከሩ አልቀረም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሣምንቱ የፌደሬሺኑ የኤፍ.ኤ. ዋንጫ ውድድር ነበር። በዚሁ የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያም ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጋው ሻምፒዮና ዋነኛ ተፎካካሪው የሆነውን አርሰናልን 2-0 በማሸነፍ አስናብቷል። ለማኒዩ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ፋቢዮ-ዳ-ሢልቫና ዌይን ሩኒይ ነበሩ። ፕሬሚየር ሊጉን በቀደምትነት የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በግማሽ ፍጻሜው የዛሬ ወር በዌምብሌይ ስታዲዮም የሚገናኘው ከከተማ ተፎካካሪው ከማንቼስተር ሢቲይ ነው። ማንቼስተር ሢቲይ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈው የሁለተኛ ዲቪዚዮኑን ክለብ ሪዲንግን 1-0 በማሸነፍ ነው። ሌላው የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ በስቶክ ሢቲይና በቦልተን ወንደረርስ መካከል የሚካሄድ ይሆናል።

Fußball 1. Bundesliga 1. FSV Mainz 05 gegen Bayer 04 Leverkusen
ምስል picture alliance/dpa

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሰንበቱ በተለይም ዘንድሮ ውድድሩ ብዙም ላልሰመረለት የብዙ ጊዜ ሻምፒዮን ለባየርን ሙንሺን ገዳም ሆኖ አልፏል። ባየርን ሃምቡርግን እንዳልነበር አድርጎ 6-0 ሲቀጣ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ሆላንዳዊ ተጫዋቹ አርየን ሮበን ነበር። በዚህ የሙንሺኑ ክለብ ፍጹም የበላይነት በታየበት ግጥሚያ የተቀሩትን ሶሥት ጎሎች ያስቆጠሩት ደግሞ የፈረንሣዩ ፍራንክ ሪቤሪይና ቶማስ ሙለር ናቸው። የሃምቡርግ ከለየለት ውርደት ላይ መውደቅ ታዲያ ለአሠልጣኙ ለአርሚን ፌህ ስንብትም ምክንያት ነው የሆነው። ባየርን ሙንሺን ከሶሥት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ሰንበቱን ያሳየው ጨዋታ እጅግ ጠንካራ ሲሆን ይህም በፊታችን ገና የሚሰናበቱትን ሆላንዳዊ አሠልጣኙን ሉዊስ-ፋን-ኸልን ጭምር ማስደነቁ አልቀረም።

“ይህን ለመሆኑ ማን አሰበው? በጣም ነው ደስ ያለኝ። በተለይም ይህን የመሰለ ጥሩ ጨዋታ ማሳየታችን ግሩም ነው። እናም ውጤቱ ነገ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከኢንተር ሚላን ለምናደርገው ግጥሚያ በሚገባ ለመዘጋጀት እንደሚረዳንም አልጠራጠርም”

ዘንድሮ ቡንደስሊጋውን በቁንጮነት መምራቱን የቀጠለው ዶርትሙንድ በአንጻሩ ሰንበቱን በሽንፈት ማሳለፉ ግድ ሆኖበታል። ዶርትሙንድ ከሆፈንሃይም ጋር ባካሄደው ግጥሚያ 1-0 ሲረታ እንደተለመደው ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ቢያሳይም ብዙ የጎል ዕድሎቹን ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። የጨዋታዋን ብቸኛ ጎል ለሆፈንሃይም ያስቆጠረው የቦስናው ተወላጅ ቬዳድ ኢቢዜቪች ነበር። የዶርትሙንድ መሸነፍ ከሁለተኛው ከሌቨርኩዝን ጋር የነበረው የ 12 ነጥቦች ልዩነት ወደ ዘጠኝ ጠበብ እንዲል ነው ያደረገው። ሌቨርኩዝን በበኩሉ የቅርብ ተፎካካሪውን ማይንስን 1-0 ሲረታ አጥቂው ሽቴፋን ኪስሊንግ እንዳለው የቡድኑ ቀደምት ዓላማ ለአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በቀጥታ ለማለፍ የሚያስችለውን ሁለተኛ ቦታ አለማስነካት ነው።

“ዛሬ ያየነው ጨዋታ እኔ እንደማምነው ከሆነ ያን ያህል ጥሩ አልነበረም። ግን በመጨረሻ ሶሥቱንም ነጥቦች መጠቅለሉ ቀንቶናል። ይሄም ቡድኑን የሚያስደስትና የሚያበረታታ ነገር ነው። እንደሚታየው ሁለተኛ ቦታችንን ለማስከበርና ለማጠናከር ችለናል። ለነገሩም ዶርትሙንድ ጉዳያችን አይደለም”

እርግጥ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ገና ስምንት ግጥሚያዎች ሲቀሩ በመሠረቱ ሌቨርኩዝንም ሻምፒዮን ሊሆን የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም። ችግሩ ምናልባት ዶርትሙንድ ዘንድሮ እጅግ ጠንካራ መሆኑ ላይ ነው። ያም ሆነ ይህ ዶርትሙንድ ከ 26 ግጥሚያዎች በኋላ በ 61 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ሌቭርኩዝን ሁለተኛ፤ ሃኖቨር ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ባየርን ሙንሺን አራተኛ በመሆን ይከተላሉ። በሌላ በኩል ሻልከና ኮሎኝ በሰንበቱ ድላቸው ወደታች ከመውረድ ስጋት ጥቂት እፎይ ሲሉ ከ 12ኛው ከብሬመን ጀምሮ እስከ 18ኛው እስከ ግላድባህ ድረስ ግን የሚቀጥሉት ሣምንታት የሞት የሽረት ይሆናሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ የሚላን ክለቦች ኤ.ሢ. እና ኢንተር ሁለቱም በየበኩላቸው ግጥሚያ በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰኑ ግድ ነው የሆነባቸው። ኤ.ሢ.ሚላን ከባሪ 1-1 ሲለያይ ኢንተርም ከብሬሺያ የተመለሰው በተመሳሳይ ውጤት ነው። በዚሁ ውጤት መሠረት ኤ.ሢ.ሚላን ሊጋውን በአምሥት ነጥቦች ብልጫ መምራቱን ሲቀጥል ኢንተር ሁለተኛ ነው፤ ፓርማን 3-1 ያሸነፈው ናፖሊ ደግሞ ከኢንተር አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል። በተቀረ ጠባብ ፉክክር በሰመረባቸው የፈርንሣይና የኔዘርላንድ ሊጋዎች ሊልና አይንድሆፈን በቁንጮነት ሲቀጥሉ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ በአሥር ነጥቦች ብልጫ ተዝናንቶ እንደመራ ነው።

Fußball Arsenal gegen Barcelona Champions League in London Van Persie freut sich
ምስል picture-alliance/dpa

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር

በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ደግሞ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር ነገና ከነገ በስቲያ የተቀሩት አራት የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት የእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ ከፈረንሣዩ ኦላምፒክ ማርሤይ የሚገናኝ ሲሆን የጀርመኑ ባየርን ሙንሺንም የኢጣሊያው ሻምፒዮን የኢንተር ሚላን ተጋጣሚ ነው። በመጀመሪያው ግጥሚያ ማንቼስተርና ማርሤይ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ባየርን በአንጻሩ ኢንተርን 1-0 ማሸነፉ አይዘነጋም።
ባየርን በውጭ በማሸነፉ የተሻለ የማለፍ ዕድል ያለው ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድም ማርሤይን በሜዳው ለማሸነፍ እንደሚችል የታዛቢዎች ዕምነት ነው። ከባየርን ቀጥሎ ሁለተኛው የጀርመን የሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳታፊ ክለብ ሻልከ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ቫሌንሢያን 3-1 በማሽነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉን ከወዲሁ አረጋግጧል። ሻልከ ከስፓኙ ክለብ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ የተለያየው 1-1 ነበር። አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት በመጨረሻ ቡድኑን በጣሙን ነው ያወደሰው።

“ቡድናችን ጠንካራ ተጋጣሚ ሲያገኝ ይበልጥ እያየለ መሄድ የሚችል ነው። ይህን ዛሬም ለመታዘብ ችለናል። በሻምፒዮና ሊጋው ውድድር ከአንድ ቀደምት የስፓኝ ቡድን ጋር ግሩም ጨዋታ ነው ያሳየነው። እና እኔም ቡድኔ ይህን የመሰለ ቆራጥነት የተመላበት ጨዋታ በማሳየቱ ደስተኛ ነኝ”

ቀደም ሲል ባለፈው ሣምንት የስፓኙ ግሩም ክለብ ባርሤሎና በመጀመሪያው ግጥሚያ በአርሰናል 2-1 ተሸንፎ ከለንደን ከተመለሰ በኋላ በመልስ ግጥሚያው 3-1 በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉን ማረጋገጡ ይታወሣል። ሌላው አስደናቂና ምናልባትም ብዙዎች ያልጠበቁት ውጤት የቶተንሃም ሆትስፐር ኤ.ሢ.ሚላንን ከውድድሩ ማሰናበት ነበር። የእንግሊዙ ክለብ የመጀመሪያና የመልሱን ግጥሚያ ያሸነፈው 1-0 በሆነ ውጤት ነበር።

በፊታችን ረቡዕ በሚካሄዱት በተቀሩት ሁለት ግጥሚያች ደግሞ ቼልሢይ ከኮፐንሃገንና ሬያል ማድሪድ ከኦላምፒክ ሊዮን ይገናኛሉ። ቼልሢይ የመጀመሪያ ግጥሚያውን 2-0 በማሸነፉ ጥሩ የማለፍ ዕድል ሲኖረው ከፈረንሣይ 1-1 ውጤት ይዞ የተመለሰው የሬያልም ዕጣ የከፋ አይደለም። ምናልባት ችግሩ ለሬያል የፈረንሣይ ክለቦች የማይቀኑት መሆናቸው ላይ ነው።

Roger Federer Hochformat
ምስል picture alliance/dpa

ቴኒስ፣ ቡጢና አትሌቲክስ

በካሊፎርኒያ ኢንዲያን-ዌልስ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር አብዛኞቹ ቀደምት ተጫዋቾች መሰናክል ሳይገጥማቸው ወደፊት መራመድ እንደቀጠሉ ነው። በወንዶች ሮጀር ፌደረር፣ ኖቫክ ጆኮቪችና ኤንዲይ ሮዲክ ትናንት በተሟላ ሁኔታ ሁለተኛ ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ልዕልናቸውን ለማሳየት ችለዋል። ፌደረር የሩሢያ ተጋጣሚውን ኢጎር አንድሬየቭን 7-5, 7-6 ሲረታ ጆኮቪችም የካዛክስታኑን አንድሬ ጎሉቤቭን በለየለት 6-0, 6-4 ውጤት አሸንፏል።
በአሜሪካውያኑ በኤንዲይ ሮዲክና በጀምስ ብሌክ መካከል የተደረገው ግጥሚያም የተፈጸመው 6-3, 7-5 ነበር። በሴቶች የቤልጂጓ ኮከብ ኪም ክላይስተርስ ሣራ ኤራኒን 2-1 ስታሸንፍ የሰርቢያዋ የለና ያንኮቪችም ጀርመናዊቱን ዩሊያ ጌኦርግስን 6-2, 6-4 ረትታለች። በተቀሩት የሴቶች ሶሥተኛ ዙር ግጥሚያዎች ዶሚኒካ ኦቡልኮቫ ስሎቫኪያ ከቬራ ዝቮናሬቫ ሩሢያ 2-1፤ አና ኢቫኖቫ ሰርቢያ ከባርባራ ስትሩይኮቫ ችክ ሬፑብሊክ 2-0፤ ማሪዮን ባርቶሊ ፈረንሣይ ከአንድሬያ ፔትኮቪች ጀርመን 2-0፤ ፍራንቼስካ ሺያቮኔ ኢጣሊያ ከአሊስ ኮሜት ፈረንሣይም እንዲሁ ሁለት ለባዶ ተለያይተዋል።

በዓለም የቡጢ ማሕበር የቀላል ሚዛን ማዕረግ ባለፈው ቅዳሜ ላስ-ቬጋስ ላይ በተካሄደ ግጥሚያ የፖርቶ ሪኮው ሚጉዌል ኮቶ የኒካራኩዋ ተጋጣሚውን ሪካርዶ ማዮርጋን በ 12ኛው ዙር ላይ በበቃኝ በማሸነፍ ሻምፒዮንነቱን አስከብሯል። ኮቶ እስካሁን ባካሄዳቸው 36 ግጥሚያዎቹ 29ኙን በመዘረር ያሸነፈ ነው። በዓለምአቀፉ የቡጢ ፌደሬሺን የቀላል ሚዛን ግጥሚያም የሜክሢኮው ተወላጅ ሚጉዌል ቫስኬስ የአውትራሊያውን ሌኦናርዶ ዛፓቪኛን በነጥብ በማሸነፍ ማዕረጉን እንደገና ለማረጋገጥ ችሏል። ቫስኬስ የሰንበቱን ድል ጨምሮ ለሰባተኛ ጊዜ በተከታታይ ማሸነፉ ነው። በአንጻሩ ለአውስትራሊያው ተወላጅ የመጀመሪያው ሽንፈት መሆኑ ነበር።

ዘገባችንን በአትሌቲክስ ነክ ዜና ለማጠቃለል የኦሎምፒክና የዓለም የምርኩዝ ዝላይ የክብረ-ወሰን ባለቤት ሩሢያዊቱ የለና ኢዚንባየቫ ያለፉት ሁለት ዓመታት አሠልጣኛን ቪታሊይ ፔትሮቭን በመተው ቀድሞ ለከፍተኛ ዕርምጃ ወዳበቃት ወደ የቭጌኒይ ትሬፊሞቭ ተመልሳለች። ሩሢያዊቱ አትሌት አሠልጣኝ ከመቀየሯ በፊት የነበሩትን ስድሥት ዓመታት አንዴም ሳትሸነፍ ማሳለፏ ይታወሣል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ